በዩናይትድ ኪንግደም በኦሚክሮን የተያዙ ሰዎች ከ10 ሺህ በላይ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አዲሱ የኮሮናቫይረስ ልውጥ ኦሚክሮን ወረርሽኝ ከቀን ወደ ቀን በጨመረባት ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) እስካሁን ባለው ከ10 ሺህ ሰዎች በላይ በኦሚክሮን መያዛቸው ተገልጿል።
ይህንንም ተከትሎ በለንደን 'ትልቅ ክስተተት' የተሰኘ አዋጅ ተደንግገጓል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ ባገረሸባት ዩናይትድ ኪንግደም ከቀናት ከፍተኛ የቁጥር ጭማሪ በኋላ ቅዳሜ ዕለት ብቻ 90 ሺህ 418 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን አረጋግጣለች።
የጤና ዘርፉ አማካሪዎች ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉና አዳዲስ እርምጃዎች ካልተወሰዱ በየቀኑ ሆስፒታሎች የሚተኙ ሰዎች ቁጥር 3 ሺህ ሊደርስ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
የለንደኑ ከንቲባ ሳዲቅ ካን በመዲናይቱ የታወጀው ትልቅ ክስተት "ነገሮች ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆኑ" ያሳያል ብለዋል።
ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ሚኒስትሮች ስለ አዲሱ የኮቪድ መረጃ አጭር መግለጫ ተሰጥቷቸዋል።
ከዚህ ቀደም ከነበረው ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ገደቦች እስካልተጣሉ ድረስ በሆስፒታሎች የሚተኙ ሰዎችን ቁጥር መቀነስ እንደማይቻልና እንደ ከዚህ ቀደሙም ሊያሻቅብ እንደሚችልም የመንግሥት አማካሪዎች ተናግረዋል።
በእንግሊዝ ካለው የ'ፕላን ቢ' ሕግ ውጪ ጣልቃ መግባት ካልተቻለ በሆስፒታል የሚተኙ ሰዎች ቁጥር ወደ 3 ሺህ ሊያሻቅብ ይችላል ሲሉ የድንገተኛ አደጋ ሳይንሳዊ አማካሪ ቡድን (ሴጅ) አባላት ገልጸዋል።
የቅርብ ጊዜ ዕለታዊ መረጃ እንደሚያሳየው 900 የኮቪድ-19 ህሙማን በእንግሊዝ ሆስፒታል ተኝተዋል።
የሴጅ አማካሪዎች የኦሚክሮንን ስርጭትን ለመግታት "በአንድ ላይ የሚሰበሰቡ ሰዎችን ቁጥር መቀነስ፣ አካላዊ ርቀትን መጨመር፣ አካላዊ ግንኙነቶችን ማስወገድና ከፍተኛ ስጋት ያላቸውን ቦታዎች መዝጋት" እንደ አማራጮች አቅርበዋል።
አዲሱ የኮሮናቫይረስ ልውጥ አሚክሮን በዓለም ላይ ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት እየተሰራጨ ነው ሲል የዓለም ጤና ድርጅት ከሰሞኑ አስጠንቅቋል።
ይህ ልውጥ ዝርያ በ77 አገራት ውስጥ መኖሩ ተረጋግጧል።
ኦሚክሮን የተሰኘው ልውጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በደቡብ አፍሪካ በኅዳር ወር ላይ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በአገሪቱ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር አሳይቷል።












