በሳዑዲ የሚመራው ጥምር ኃይል የየመን አየር ማረፊያ ላይ የአየር ጥቃት አደረሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ጥምር ኃይል በየመን መዲና ሰንዓ በሚገኘው አየር ማረፊያ ላይ በትናንትናው ዕለት የአየር ጥቃት ፈጽሟል።
ጥምር ኃይሉ የአየር ማረፊያው ድንበር ዘለል ጥቃቶችን ለመፈጸም አገልግሎት ላይ እየዋለ ነው ብሏል።
የመን ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ በእስላማዊ አማፂያን እና በመንግሥት መካከል የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ትገኛለች።
የአማፂያኑ ኃይሎች አየር ማረፊያውን ለበርካታ ዓመታት ተቆጣጥረው ቆይተዋል። በተጨማሪም አየር ማረፊያው በተባበሩት መንግሥታት ለሚመራው የሰብዓዊ አገልግሎት ማዕከል ሆኖ ቆይቷል።
ጥቃቱ ከመፈጸሙ በፊት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ ሠራተኞች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ጥምር ኃይሉ ማሳሰቡን የሳዑዲ መንግሥት ሚዲያ ዘግቧል።
ጥቃቱ ወታደራዊ ኢላማ ናቸው ተብለው በሚቆጠሩ የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ያነጣጠረ መሆኑም ተገልጿል።
በዚህ ጥቃት ስድስት ኢላማዎች መመታታቸውን የጥምር ኃይሉ ቃለ አቀባዩ ብርጋዴር ጀነራል ቱርኪ አል-ማልኪ ገልፀው፣ ከእነዚህም መካከል ጥቃት አድራሽ ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮሽ) መነሻ ስፍራዎች፣ ድሮኖችን የሚያንቀሳቅሱ ሠራተኞች ማሰልጠኛ፣ የድሮኖች ማከማቻ እንደሚገኙባቸውም አስረድተዋል።
"እነዚህን ኢላማዎች ከጥቅም ውጪ ማድረግ በአውሮፕላን ማረፊያው የሥራ ማስኬድ አቅም ላይ ምንም አይነት ተጽእኖ አይኖረውም። የአየር ማረፊያውን የአየር ክልል፣ የአየር ትራፊክ እና ከአውሮፕላኖች ማረፍ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን አይጎዳም" በማለት ጄኔራል ቱርኪ አል ማልኪ በመግለጫቸው አክለዋል።
ሁሉም ወገኖች ጥቃቱ ያደረሰውን የጉዳት መጠን እና የትኞቹ ኢላማዎች እንደተመቱም ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
በአረብ አገራት ዘንድ በድህነቷ የምትታወቀው የመን የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ በዓለም የከፋ የሚባል ሰብአዊ ቀውስ ገጥሟታል።
ከቅርብ ወራት ወዲህ ደግሞ በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ውጊያ እየተባባሰ ሄዷል።
አማፂያኑ በማዕከላዊዋ ማሪብ ከተማ እና በባሕር ዳርቻ በምትገኘው ሆዴይዳ ላይ ያነጣጠሩ ሲሆን፣ ጥምር ኃይሉ ደግሞ በሰንዓ እና በሌሎች አማፂያን ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች ላይ የአየር ጥቃቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።
በአውሮፓውያኑ 2015 የሁቲ አማፅያን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለውን መንግሥት ከሰንዓ ማስወገዳቸውን ተከትሎ በሳዑዲ የሚመራ ጥምር ጦር በየመን ጣልቃ ገብቷል።
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሞቱ ሲሆን በተፎካካሪ የቀጣናው ኃይሎች መካከል የውክልና ጦርነት ሆኗል።












