በደቡብ ኢትዮጵያ ዱራሜ ውስጥ ከአንዲት እናት 20 ኪሎ የሚመዝን እጢ ተወገደ

የፎቶው ባለመብት, Kembata Tembaro Zone Communication
ወ/ሮ ታገሰች ደሳለኝ ከሰውነታቸው 20 ኪሎ ግራም የሚመዝን እጢ እንደተወገደላቸው ቀዶ ሕክምናውን ያካሄዱት ዶ/ር አብነት አዳነ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የስድስት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ታገሰችም በቀዶ ሕክምና እጢው ከወጣላቸው በኋላ በጥሩ ጤንነት ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የተወለዱት በደቡብ ክልል፣ ከንባታ ጠንባሮ ዞን፣ ሺንሺቾ ወረዳ፣ ዋላና ቀበሌ ነው። በ1993 ዓ.ም. ትዳር ከመሠረቱ በኋላ በሀዲያ ዞን፣ ቃጫቢራ ቀበሌ መኖር ጀመሩ።
ሕመም የጀመራቸው ከአራት ዓመት በፊት እንደነበረ ያስታውሳሉ።
"ሆዴን ይቆርጠኝ ነበር። ቁርጥማትም ነበረኝ። ሆዴ በጣም ይነፋና ይቀንሳል። ከዚያ ግን ተመልሶ ይነፋል" ሲሉ ስቃዩን ይገልጻሉ።
እጢውን ያወጡላቸው ዶ/ር አብነት እንደሚሉት፤ ቀዶ ሕክምናው ሲካሄድ ወ/ሮ ታገሰች የስድስት ወር ነፍሰ ጡር ነበሩ።
"ስትመጣ መተንፈስ እና ቀና ብላ መሄድ አትችልም ነበር። ከኋላ 2 ወይም 3 ሰዎች እየገፏት ነበር የምትንቀሳቀሰው። ስለዚህ በድንገተኛ ገብታ ቀዶ ሕክምና እንዲደረግ ወሰንን" ይላሉ።
እጢው እንዴት ተገኘ?
ዶ/ር አብነት፤ በዱራሜ ከተማ በዶ/ር ቦጋለች ታቦሬ አጠቃላይ መታሰቢያ ሆስፒታል የጽንስና ማሕፀን ሐኪም ናቸው።
ኅዳር 03/2014 ዓ.ም. ሦስት ሰዓታት ከፈጀ ቀዶ ሕክምና በኋላ 20 ኪሎ ግራም እጢ እንዲሁም የታማሚዋ ማሕፀንም ሙሉ በሙሉ እንደወጣ ይናገራሉ።
ወ/ሮ ታገሰች ሕመሙ ሲጀምራቸው ጉበት ነው ተብሎ ነበር። ሲጠናባቸው ወደ ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል አቀኑ።
እጢ እንዳለባቸው እና መውጣት እንደሚገባው ሲነገራቸው ግን ፈቃደኛ እንዳልነበሩ ዶ/ር አብነት እንዲሁም ታናሽ ወንድማቸውም ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ያኔ እጢው መጠኑ ትንሽ ነበር።
ወ/ሮ ታገሰች ለቀዶ ሕክምና ፈቃደኛ ስላልነበሩ ግን ወደ ቤተ እምነት አመሩ።
"ሁለት ኪሎ የሚሆን እጢ ከወጣልኝ በኋላ ከአዲስ አበባ ተመልሼ ኑሮዬን ቀጠልኩ" ሲሉ ያስታውሳሉ።
ለተወሰነ ጊዜ ደኅና ሆነው ቆዩ። ሲያረግዙ ግን ሕመሙ በድጋሚ ተመለሰ።
እስከ አራት ወር እርግዝናቸው ድረስ ሕመም አልነበራቸውም። ከዚያ ግን ከሁለት ወራት በፊት ሆዳቸው መነፋት ጀመረ።
"ራሴን መቆጣጠር የማልችልብት ደረጃ ደረስኩ" ይላሉ።
ዶ/ር አብነት የራዲዮሎጂ ምርመራ ከተደረገ በኋላ የማሕፀን እጢ እንደሆነ እንደተደረሰበት ያስረዳሉ።
ወ/ሮ ታገሰች መተንፈስ ተስኗቸው ወደ ሆስፒታሉ ሲሄዱ እጢውን ለማውጣት እንደወሰኑም ያክላሉ።
"ቤተሰቧን አማከርን። በሐሳባችን ተስማሙ። በተስማሙት መሠረትም አስፈረምን። ስትመጣ የቀዶ ሕክምና አልጋ ላይ ለማስተኛት እንኳን አይቻልንም ነበር። አልጋውን ለእሷ በሚስማማ አቅጣጫ ባለሙያዎች ካስተካከሉ በኋላ ነው ወደ ሕክምና የገባነው።"

የፎቶው ባለመብት, Kembata Tembaro Zone Communication
የቀዶ ሕክምና ሂደቱ
የሐዋሳ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተማሪው ዶ/ር አብነት ወደ ማሕፀንና ጽንስ ሕክምና ከገቡ ገና ሁለት ዓመታቸው ነው።
ወ/ሮ ታገሰች የገጠማቸው ዓይነት ሕመም ለሆስፒታሉ እንዲሁም ለእሳቸውም አዲስ እንደሆነ ይናገራሉ።
የሕመሙ መነሻ በትክክል የማሕፀን እጢ መሆኑ በአልትራሳውንድ ስላልተረጋገጠ የራድዮሎጂ ክፍል የሰጠው አማራጭ ኤምአርአይ ይነሱ የሚል ነበር።
ነገር ግን ሕመማቸው አጣዳፊ ስለነበር ወደ ቀዶ ሕክምና ለመግባት መገደዳቸውን ያስረዳሉ።
"ሕመሟ ጊዜ አሳጣን። አጣዳፊ ነበር። በጣም ታፍና መተንፈስ አቃታት። ኦክስጅን ተደርጎላትም መተንፈስ አልቻለችም።"
ወ/ሮ ታገሰች ሕመሙ እጅግ ሲበረታባቸው "በቃ! አልሞትም። እዚሁ [ቀዶ ሕክምና] ሥሩልኝ" ብለው መማጸናቸውን ዶክተሩ ይናገራሉ።
ከዚያም ከቀዶ ሕክምና፣ ከጽንስና ማሕፀን፣ ከራድዮሎጂ እና ከሌሎችም ክፍሎች ባለሙያዎች ተሰባስበው ቀዶ ሕክምናውን አካሄዱ።
"ያገኘነው በጣም ትልቅ እጢ እና የስድስት ወር ጽንስም ነበር። የማሕፀን እጢ ወደ ካንሰር ስለሚቀየር ወደ 20 ኪሎ ግራም የሚመዝነውን ሙሉ እጢ አውጥተናል። እጢው ላይ የተቋጠረ ፈሳሽ፣ ጽንሱ እና ማሕፀኗም ወጥቷል። ጽንሱ 650 ግራም ነው።" ብለዋል።
ዶክተሩ እንደሚያስረዱት፤ ወ/ሮ ታገሰች ከዕድሜያቸው አንጻር ለወደፊት ማሕፀናቸው ለበሽታ የመጋለጥ ስጋት እንዳይደቅን ሲባል ማሕፀናቸው እንዲወጣ ተወስኗል።
እርግዝናው ሌላ የጤና ስጋት ስለሚፈጥርም ጽንሱን ለማውጣት ተገደዋል።
"እርግዝናው የእጢው እድገት እንዲጨምር አድርጎታል። ይገፋው ነበር። ሆዷን ወደላይ ገፍቶ፣ ወጥሮ ስለያዘ ለስድስት ሳምንት አልታኝችም። እንቅልፍ አልነበራትም" ሲሉ ያስረዳሉ።
ቀዶ ሕክምናውን ሲጀምሩ የወ/ሮ ታገሰች አንጀት ተገፍቶ ወደ ጀርባቸው ዞሮ ስለነበር እንደማይታይ ዶክተሩ ይገልጻሉ።
እጢው ከወጣ በኋላ ወደ ማሕፀናቸው ወርደው፣ ጽንሱን እንዲሁን ማሕፀናቸውንም ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ ተደርጓል።
ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ለ10 ቀናት ሆስፒታል ቆይተው ደኅና መሆናቸው ሲረጋገጥ ወደ ቤት እንዲመለሱም ተደርጓል።

የፎቶው ባለመብት, Kembata Tembaro Zone Communication
"እየተራመደች ወደ ቤት ተመለሰች"
ወ/ሮ ታገሰች ቀዶ ሕክምና ከማድረጋቸው በፊት መተንፈስ ተስኗቸው፣ ለመንቀሳቀስም ተቸግረው እንደነበር ይናገራሉ።
"ካረገዝኩበት ከአራተኛው ወር ጀምሮ ሆዴ ተነፍቶ ነበር። ከአራተኛው ወር እስከ ስድስተኛው ወር ድረስ ከባድ ስቃይ ነው ያሳለፍኩት" ይላሉ።
ከአንድ ዓመት በፊት አዲስ አበባ ወደ ሚገኙ ተለያዩ የምርመራና የሕክምና መስጫዎች በመሄድ ሕመማቸው ምን እንደሆነ ለማወቅ ጥረት አድርገው ነበር። ነገር ግን ዘለግ ላለ ጊዜ በሽታቸው አልታወቀላቸውም።
የኋላ ኋላ እጢ እንደሆነ ሲነገራቸው ወደ ቤተ እምነት ለመሄድ እንደመረጡ ታናሽ ወንድማቸው ይናገራል።
"ቤተ እምነት ከሄደች በኋላ 2 ኪሎ የሚመዝን እጢ ስለወጣላት ወደ ሥራ ተመለሰች። ስታረግዝ ግን ሕመሙ ተመለሰባት" ይላሉ።
ወ/ሮ ታገሰች የ4 ወር ነፍሰ ጡር ሆነው ሕመም ሲጠናባቸው ወደ ሦስት ሆስፒታሎች ተመላልሰዋል።
በመጨረሻ ከሼንሺቾ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ወደ ዱራሜ ሪፈር ተጻፈላቸው።
"ከሕክምናው በፊት መተኛት፣ መንቀሳቀስም አልችልም ነበር። ሁለት ሰው ተባብሮ ነበር ከተቀመጥኩበት የሚያነሳኝ። ሆዴን ይቆርጠኝ፣ ይነፋኝም ነበር። ምግብም መመገብ ተውኩ።"
በእነ ዶ/ር አብነት ቀዶ ሕክምና ከተደረገላቸው በኋላ ግን ጤናቸው መመለሱን ይናገራሉ። ሙሉ ጤናቸው እስከሚረጋገጥ ድረስ በሆስፒታል ውስጥ ክትትል እተደረገላቸውን ባለሙያዎች ገልጸዋል።
"አሁንማ ምንም ሕመም የለም። በሰላም እየተኛሁ ነው። ሁሉን ነገር ራሴን ችዬ ማድረግ ችያለሁ" ይላሉ።
"ያለ ምንም ችግር እየተራመደች፣ ከእኔም ጋርም ፎቶ ተነስታ [ወደ ቤቷ] ተመለሰች። አተነፋፈሷ ተመልሶ፣ ቁስሉ ድኖ፣ ክሩ ወጥቶ ሄዳለች። ቤተሰቦቿም አመስግነውናል" ብለዋል ዶ/ር አብነት።
ወ/ሮ ታገሰች በቀጣይ ምን ይጠብቃቸዋል?
ወ/ሮ ታገሰች የአራት ወንዶች እና ሁለት ሴቶች እናት እና የቤት እመቤት ናቸው።
ባለቤታቸው በወንጪ የስኳር ፋብሪካ የጉልበት ሥራ ይሠሩ ነበር። እሳቸው ሲታመሙ ግን ሥራቸውን አቋረጡ።
ወ/ሮ ታገሰች እና ባለቤታቸው በቆሎ በመቸርቸር ነበር ሕይወትን የሚገፉት።
አሁን ላይ እጢው ከሰውነታቸው ተወግዶ ጤናቸው ቢመለስም ምርመራ መቀጠል እንዳለባቸው ዶ/ር አብነት ይናገራሉ።
"ካንሰር ከሆነ ኬሞቴታፒ፣ የጨረር ሕህምና ወይም ሆርሞናል ቴራፒ ስለሚያስፈልግ ስለ ቀጣዩ ሕክምና ከቤተሰብ ጋር ተነጋግረናል" ይላሉ።
ቀዶ ሕክምናው በቂ የሚሆንበት ወይም ሌላ ሕክምና የሚያስፈልግበትም ዕድልም እንዳለ ያክላሉ።
እጢን መከላከል ይቻላል?
ዶ/ር አብነት እንደሚሉት፤ በርካቶች የጤና ክትትል ስለማያደርጉ እጢ በእንጭጩ የሚወጣበትን ደረጃ ያሳልፋሉ።
እጢው ሳያድግ ይውጣ ሲባልም ብዙዎች ያንገራግራሉ።
እጢ በዘር፣ በሕዋስ ርቢ (ሴል ሚውቴሽን) እንዲሁም በሌሎችም ምክንያቶች ይከሰታል።
በተለይም የሴቶችን ጤና በተመለከተ "ሁሉም ሴት ለእጢ ተጋላጭ ስለሆነች 'ጤነኛ ነኝ' ሳይሉ የማሕፀን ሐኪም ጋር በ6 ወር ወይም በዓመት መሄድ ያስፈልጋል። አልትራሳወንድ ምርመራ ማድረግ እና ሕክምና መከታታልም ያሻል" ሲሉ ይመክራሉ።
እጢ እንደ ማሕፀን ጫፍ ካንሰር የማይታይ፣ ድብቅ በመሆኑ የማደግ ዕድል እንዳለው ሐኪሞች ያስረዳሉ፤ ለዚህም ነው ተከታታይ ምርመራ ማድረግን የሚያበረታቱት።












