ታዋቂዋ ደራሲና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ ቤል ሁክስ ከዚህ አለም በሞት ተለየች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በርካታ የፌሚኒስት፣ ዘረኝነት፣ ካፒታሊዝም ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ፅሁፎችን ያበረከተችው ደራሲዋና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ ቤል ሁክስ በ69 አመቷ ከዚህ አለም በሞት መለየቷን ቤተሰቦቿ አረጋግጠዋል።
ህይወቷ ያለፈው ረቡዕ ዕለት ኬንታኪ በሚገኘው ቤቷ ውስጥ ሲሆን በወቅቱም "በቤተሰብ፣ ወዳጆችና ጓደኞች" ተከባ እንደነበር መግለጫው አክሏል።
በበርካታ ዩኒቨርስቲዎች ዘንድ እንደ ማስተማሪያነት የሚያገለግሉ መፅሃፎችን ያበረከተችው ቤል ሁክስ 'ኢንተርሴክሽናል ፌሚኒዝም' በሚለው እሳቤም ጮራን ፈንጥቃለች።
ሴቶች ከፆታቸው ሌላ ማህበራዊ፣ ምጣኔ ኃብትና ሌሎች ተደራራቢ ጉዳዮች ምክንያት የሚገጥማቸውን አድሎና ጫና ሁኔታ ለመረዳት እይታ የሚሰጥ የትንታኔ ማዕቀፍ ነው።
ቤል ሁክስ በህይወቷ የተለያዩ ርእሶችን የሚዳስሱ ከ40 በላይ መፃህፍቶችን አሳትማለች።
ትክክለኛ ስሟ ግሎሪያ ዣን ዋትኪንስ የሚል ሲሆን ፅሁፏን ከጀመረች በኋላ የአያቷን ስም ቤል ብሌይር ወርሳ መጠቀም ጀመረች።
ነገር ግን ቤል ሁክስ ስሟን ስትፅፍ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ህግ መሰረት ለስም ሲሆን ካፒታል ሆሄያትን ሳይሆን ትናንሽ ሆሄያትን ነው የምትጠቀምው ይህ ከሷ ይልቅ አንባቢው በመልዕክቷ ላይ እንዲያተኩሩ እንደሆነ ትናገራለች።
"ማንነቴ ላይ ሳይሆን መፃህፍቴ ይዘት" ላይ አንባቢዎች እንዲያተኩሩ እንደምትፈልግም አስረድታለች።
ቤል ሁክስ ፌሚኒዝም፣ ዘረኝነት፣ ባህል፣ ካፒታሊዝም፣ የስርዓተ ፆታ ሚናዎች፣ ፍቅር፣ መንፈሳዊነት በተደጋጋሚ የምታነሳቸው ጉዳዮች ናቸው።
በተለይም ዘር፣ ፆታ እና መደብ እንዴት አይነት ጥብቅ ቁርኝት እንዳላቸው በፅሁፎቿ አንፀባርቃለች።
"በፌሚኒዝም የተገኙ ድሎችን ከሌሎች ትግሎች ነጥለን ማየት አንችልም" ብላለች በአንድ ወቅት
የእህቷ ልጅ ኢቦኒ ሞትሊ በትዊተር ገጿ ላይ የቤል ሁክስን የመሞቷን ዜና የሚያረጋግጥ መግለጫ አውጥታለች።
"ግሎሪያ እንደ ገጣሚ፣ ፌሚኒስት፣ ደራሲ፣ ፕሮፌሰር፣ የባህል ሃያሲ፣ እና ማህበራዊ ተሟቻችነቷ ላገኘቻቸው በርካታ ሽልማቶች፣ ክብርና ዓለም አቀፍ እውቅና ቤተሰቡ ያመሰግናል" በማለት መግለጫው አትቷል።
ቤል ሁክስ የተወለደችው በአውሮፖውያኑ መስከረም 25 1952 በሆፕኪንስቪል ፣ ኬንታኪ ሲሆን ለቤተሰቦቿም ከሰባት ልጆችም አራተኛዋ ናት።
ወደ ካሊፎርኒያ ስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ ከመግባቷ በፊት ለነጮችና ጥቁሮች የተለየው ክርስቲያን ካውንቲ ትምህርቷን ተከታትላለች።
በዊስኮንሰን ዩኒቨርስቲ በእንግሊዝኛ የማስተርስ ዲግሪዋን አግኝታለች በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ እንዲሁ በሥነ ጽሑፍ የዶክትሬት ዲግሪዋን አግኝታለች።
'ኤይንት አይ ኤ ውማን? ብላክ ውሜን ኤንድ ፌሚኒዝም' የሚለው የመጀመሪያ መፅሃፏ የታተመው በአውሮፓውያኑ 1981 ነው።
ቤል ሁክስ ለህፃናት የሚሆኑ ግጥሞችን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ 40 መፃህፍቶችን ፅፋለች።
በአንድ ወቅት ባደረገችው ቃለ መጠይቅ ላይ"የእኔ ስራ ሰፊ ጉዳዮችን የሚዳስስና ጥልቀት ያለው ነው" ብላለች።
ከአውሮፖውያኑ 2004 ጀምሮ ቤል ሁክስ በቤሪያ ኮሌጅ በመምህርነት እያገለገለች የነበረ ሲሆን በ2010ም በቤርያ ኮሌጅ የቤል ሁክስ ተቋምን አቋቁማለች።
"የእኔ ሥራ ስለ ፈውስ እንዲሆን እፈልጋለሁ። እኔ እድለኛ ጸሐፊ ነኝ ምክንያቱም በሕይወቴ በየቀኑ ማለት ይቻላል ደብዳቤ ይደርሰኛል፣ ሰዎች ስራዬ እንዴት እንደለወጧቸው እየደወሉ ይነግሩኛል" ብላለች ቤል ሁክስ
"ከምወዳቸው ጓደኞቼ አንዷ ነበረች እና እሷ በሌለችበት ሁኔታ አለም ያነሰች ቦታ ሆና ነው ያገኘሁዋት" በማለት ጓደኛዋ ሊንዳ ስትሮንግ ሊክ ተናግራለች።
ታዋቂዋ አሜሪካዊቷ ጸሃፊ ሮክሳን ጌይ በትዊተር ገጿ ላይ "ልቤ ተሰበረ! ቤል ሁክስ፤ በሰላም፣ በኃይል ላይ እረፊ፣ እሷንየ ማጣት ኪሳራ ሊነገር አይችልም" በማለት አስፍራለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images












