አረብ ኤምሬትስ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ12 የአፍሪካ አገራት ላይ የጣለችውን የጉዞ እገዳን ልታነሳ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በቅርብ ጊዜ ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደ ሌሎች 12 አገራት ተጉዘው የነበሩ ሰዎች ወደ ግዛቷ እንዳይገቡ ጥላው የነበረውን እገዳ ልታነሳ መሆኑ ተገለጸ።
በፍጥነት የሚሰራጨውን የኮሮናቫይረስ ልውጥ ዝርያ የሆነውን ኦሚክሮን መስፋፋትን ተከትሎ ነበር የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከተወሰኑ የአፍሪካ አገራት የሚመጡ መንገደኞች ላይ እገዳ የጣለችው።
በዚህም ከኢትዮጵያ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከኬንያ፣ ከናይጄሪያ እና ከሌሎች ስምት የአፍሪካ አገራት ወደ ግዛቷ የሚጓዙ ትራንዚት አድራጊዎች እንዳይገቡባት ከልክላ ቆይታለች።
ይህንን እገዳ ከተጠቀሱት አገራት የሚነሱትን ብቻ ሳይሆን ከጉዟቸው ቀደም ብለው ባሉት 14 ቀናት ውስጥ እዚያ ያቆዩትንም ያካትት ነበረ።
በአገሪቱ የብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ ቀውሶችንና አደጋዎችን የሚከታተለው ተቋም እንዳስታወቀው በኮሮናቫይረስ መስፋፋት ስጋት ሳቢያ ለሳምንታት ተጥሎ የነበረው እገዳ ከሚቀጥለው ቅዳሜ አንስቶ ይነሳል።
ነገር ግን ከአፍሪካ አገራት ወደ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ የሚጓዙ ሰዎች ከጉዟቸው 48 ሰዓታት በፊት ከበሽታው ነጻ መሆናቸውን የሚያመለክት የኮቪድ-19 ሲፒአር ምርመራ ውጤት እንዲሁም ከሚነሱበት አየር ማረፊያ ፈጣን ምርመራ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም መንገደኞች ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ እንደደረሱ ሌላ የኮቪድ-19 ምርመራ ማድረግ ይገባቸዋል ተብሏል።
እንዲነሳ የተወሰነው እገዳ ከኢትዮጵያ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከኬንያና ከናይጄሪያ በተጨማሪ ታንዛኒያን፣ ኮንጎ ሪፐብሊክን፣ ቦትስዋናን፣ ኢስዋቲኒን፣ ሌሶቶን፣ ናሚቢያን፣ ሞዛምቢክን እና ዚምባብዌን የሚመለከት ነበር።
የእገዳውን መጣል አገራቱ ተቃውመውት የነበሩ ሲሆን፣ በተለይ ኬንያ በአጸፋው ከጭነት አውሮፕላኖች ውጪ ከዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ የሚነሱ መንገደኞች ወደ ግዛቷ እንዳይገቡ ከልክላ ነበር።












