ዩክሬን ፡ ሩሲያ ወረራ ከፈጸመች የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመሯ ሊዘጋ እንደሚችል አሜሪካ አስጠነቀቀች

ታንክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ባለፉት ሳምንታት ሩሲያ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን በዩክሬን ድንበሮች ላይ አስፍራለች

ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች የሩሲያን ነዳጅ ወደ ምዕራብ አውሮፓ የሚያስተላልፈውን ቁልፍ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር እንዳይከፈት እንደምታደርግ አሜሪካ አስጠነቀቀች።

ኖርድ ስትሪም 2 ከሩሲያ ወደ ጀርመን የተዘረጋ ሲሆን ሐሙስ ዕለት የበርሊን ባለሥልጣናትም ሩሲያ ዩክሬን ላይ ጥቃት ከሰነዘረች ፕሮጀክቱ ላይ ማዕቀብ ሊጣል እንደሚችል ተናግረዋል።

ሌሎች የአሜሪካ አጋር የምዕራብ አገራት በበኩላቸው ሩሲያ ወረራ ከፈጸመች በኢኮኖሚዋ ላይ ጫና እንደሚያሳድሩ ገልጸዋል።

ከሰሞኑ እየተሰሙ ያሉ አስተያየቶችም በርካታ ትርፍ ሊያስገኝ የሚችለው የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ላይ አገራቱ ያላቸው አቋም እየጠነከረ መምጣቱን አመልክቷል።

ሩሲያ ግን በዩክሬን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር አቅዳለች መባሏን አስተባብላለች።

ይሁን እንጂ ባለፉት ሳምንታት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የሩሲያ ወታደሮች በዩክሬን ድንበር ላይ መስፈራቸው በአገራቱ መካከል ያለውን ውጥረት አባብሶታል። ሩሲያ ወረራ እንዳትፈጽምም ስጋት ፈጥሯል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ "በዚህ ጉዳይ ላይ ግልጽ መሆን እፈልጋለሁ። ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ኖርድ ስትሪም 2 ወደ ፊት አይራመድም" ሲሉ ለኤንፒአር ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ ፕሮጀክቱ እንዴት ሊቆም እንደሚችል እና ፕሮጀክቱን ለመሰረዝ አሜሪካ ሥልጣን ይኖራት እንደሁ ለማስረዳት ወደ ዝርዝር ጉዳዮች እንደማይገቡ ገልጸው፤ "ፕሮጀክቱ ወደ ፊት እንዳይሄድ ለማድረግ ግን ከጀርመን ጋር እንሰራለን" ብለዋል።

አሜሪካ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመሩን መከፈት ሙሉ በሙሉ እንደምታቆም ስትገልጽ፤ ጀርመን ግን በፕሮጀክቱ ላይ ማዕቀብ ልትጥል እንደምትችል አስታውቃለች።

የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ የምዕራባውያን አጋሮች ኖርድ ስትሪም 2ን የሚያካትት 'ጠንካራ ማዕቀቦች' ላይ እየሰሩ መሆናቸውን ለምክር ቤቱ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ሚኒስትሯ "ከሞስኮ ጋር የሚደረገውን ውይይት መቀጠሉን እመርጣለሁ" ብለዋል።

ሚኒስትሯ ይህንን አስተያየት የሰጡት በአሜሪካ የጀርመን አምባሳደር የሆኑት ኢሚሊይ ሃበር "ሩሲያ የዩክሬንን ሉዓላዊነት ከጣሰች ኖርድ ስትሪም 2ን ጨምሮ ከጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት የሚያልፍ ነገር የለም" ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ ካጋሩ በኋላ ነው።

1 ሺህ 225 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ አምስት ዓመታትን የወሰደ ሲሆን 11 ቢሊየን ዶላር ፈሶበታል።

በባልቲክ ባሕር ሥር የሚገነባው የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሩሲያ ወደ ጀርመን የምትልከውን ነዳጅ በእጥፍ ለማሳደግ ታስቦ የተዘረጋ ነው።

ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ ሥራ አልጀመረም። ኅዳር ወር ላይ ተቆጣጣሪዎች የጀርመን ሕግን እንደማያከብር ገልጸው፤ ፕሮጀክቱን ከመጽደቅ አግደዋል።

ዋና ዋና የአውሮፓ ቢዝነሶች በቀድሞ ቻንስለር ጌርሃርድ ሽሮደር በሚመራው በኖርድ ስትሪም 2 ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን አፍስሰዋል። ሆኖም በርካቶቹ እቅዱ ላይ ተቃውሞ አላቸው።

የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች ጀርመን የካርቦንዳ ኦክሳይድ ልቀትን ለመቀነስ እና በሰው ሰራሽ መልኩ የሚመጣ የአየር ንብረት ለውጥን ለማስወገድ ከምታደርገው ጥረት ጋር እንዴት ይስማማል ሲሉ ይጠይቃሉ።

በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር ያሉ ፖለቲከኞች በበኩላቸው አውሮፓ በሩሲያ ኃይል ላይ የሚኖራትን ጥገኝነት ይጨምራል ብለዋል።

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ቀደም ብሎ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመሩን "አደገኛ ጂኦፖለቲካዊ መሣሪያ" ሲሉ ገልጸውታል።