ሱዳን ውስጥ ሐሙስ በተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች ቢያንስ 4 ሰዎች መገደላቸው ተዘገበ

ተቃዋሚ ሰልፈኞች

የፎቶው ባለመብት, AFP

ሱዳን ውስጥ በቀጠለው ፀረ መንግሥት ተቃውሞ ትናንት ሐሙስ የፀጥታ ኃይሎች በተቃዋሚ ሰልፈኞች ላይ በወሰዱት እርምጃ ቢያንስ አራት ሰዎች መገደላቸው ተነገረ።

የአገሪቱን የመሪነት ሥልጣን የተቆጣጠረው የጦር ኃይሉ ከሥልጣን ወርዶ መንግሥት በሲቪሎች እንዲመራ የሚጠይቁ ሰልፈኞች በተለያዩ የሱዳን ከተሞች የተቃውሞ ሰልፍ ማድረግ ከጀመሩ ሳምንታት ተቆጥረዋል።

የሱዳን ዶክተሮች ቡድን እንዳለው ሐሙስ ዕለት ወታደራዊ አስተዳደሩ ሥልጣን እንዲለቅ የሚጠይቁ የተቃውሞ ሰልፎችን ተከትሎ አራቱ ሰዎች የተገደሉት ኦምዱርማን በምትባለው ከተማ ውስጥ ነው።

ተቃውሞዎችን እንዲቆጣጠሩ የሱዳን መንግሥት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የፀጥታ ኃይሎችን ከማሰማራቱ በተጨማሪ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎቶች ተቋርጠዋል።

ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ላይ የተካሄደውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ እስካሁን ድረስ ከ50 በለይ ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል።

ኦማር አልበሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ የአገሪቱን ከፍተኛ ሥልጣን የተቆጣጠረውን ወታደራዊ ኃይል በመቃወም የዴሞክራሲ ለውጥ ጠያቂ ሱዳናውያን ተከታታይ የተቃውሞ ሰልፎች እያደረጉ ይገኛሉ።

በዋና ከተማዋ ካርቱምና በሌሎች የሱዳን አካባቢዎችም የጦር ኃይሉን በመቃወምና የአገሪቱ አስተዳደር ወደ ሲቪል መሪዎች እጅ እንዲመለስ የሚጠይቁ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው።

በተለይ ካርቱም ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፀጥታ ኃይል ቢሰማራም ተቃዋሚዎች ድምጻቸውን ለማሰማት ወደ አደባባይ ከመውጣት አልተቆጠቡም።

የዶክተሮቹ ቡድን እንዳለው ሐሙስ ዕለት ከካርቱም አቅራቢያ በምትገኘው የኦምዱርማን ከተማ ውስጥ በተካሄደው ሰልፍ ላይ አራት ሰዎች በተተኮሰባቸው ጥይት ተገድለዋል። በተጨማሪም በርካታ ሰልፈኞች የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል።

ተቃዋሚዎች ወደ ዋና ከተማዋ እንደይገቡ ለመከላከል በአባይ ወንዝ ላይ ያሉና ወደ ካርቱም ከሚያሻግሩ ድልድዮች መካከል ቢያንስ ሁለቱ በትላልቅ የእቃ ማጓጓዣ ኮንቴይነሮች በፀጥታ ኃይሎች እንዲዘጉ ተደርገዋል።

ነገር ግን ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ጥሰው በማለፍ ወደ ፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት ሲቃረቡ በፖሊሶች እንዲበተኑ ተደርገዋል።

ተቃዋሚዎች በጄነራል አል ቡርሐርን የሚመራው የሱዳን መንግሥት ከሥልጣን እንዲወርድ እና ጦር ሠራዊቱ ከአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ እጁን እንዲያወጣ እየጠየቁ ይገኛሉ።

ከሦስት ዓመት በፊት በተደረሰውና ባልተከበረው የሥልጣን ክፍፍል ስምምነት መሠረት የሱዳን የሽግግር መንግሥት መሪ የነበሩትና የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ጄነራል አል ቡርሐን ሥልጣናቸውን ለሲቪል ፖለቲከኞች ማስረከብ የነበረባቸው ባለፈው ኅዳር ወር ላይ ነበር።

ጄነራሉ መፈንቅለ መንግሥት ያካሄዱት ፖለቲከኞች ሰላማዊ ሰዎችን በፀጥታ ኃይሎች ላይ እያነሳሱ በመሆናቸው የእርስ በርስ ጦርነት እንዳይከሰት ለመከላከል ነው ሲሉ የእርምጃቸውን ተገቢነት ገልጸው ነበር።

ጄነራሉ ሱዳን አሁንም በሽግግር ሂደት ላይ እንደሆነችና አገሪቱን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለማሻገር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸው ከሁለት ዓመት በኋላ ምርጫ እንደሚካሄድ አመልክተዋል።

ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ ወደ ሥልጣናቸው ከተመለሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጋር በተደረሰው ስምምነት ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ የባለሙያዎች ካቢኔ እንደሚኖራቸው ተገልጿል።

ነገር ግን አዲሱ የሲቪል መንግሥት በጦር ሠራዊት ጀነራሎች የበላይ ተቆጣጣሪነት ስር ስለሚሆን አገሪቱን በሚመራበት ጊዜ የሚኖረው ሥልጣን ምን ያህል እንደሆነ ግልጽ አይደለም።

ለወራት ወታደራዊውን መንግሥት በመቃወም በሱዳን ጎዳናዎች ላይ ድምጻቸውን ሲያሰሙ የቆዩ ሱዳናውያን ግን በጦር ኃይሉ ላይ እምነት ስለሌላቸው የትኛውም አይነት የሥልጣን መጋራት ስምምነትን ፈጽሞ አይቀበሉትም።

ሰላሳ ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ሱዳንን የመሩት አልበሽር በሕዝባዊ ተቃውሞ ከሥልጣን ተወግደው እስር ቤት ከገቡ በኋላ አገሪቱን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመምራት የሽግግር መንግሥት ቢቋቋምም፣ በወታደራዊና በሲቪል መሪዎች መካከል መግባባት ሳይፈጠር እስካሁን ቆይቷል።

ጥቅምት ወር ላይ በጄነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሐን የተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት ደግሞ በአገሪቱ ያለውን ቀውስ አባብሶታል።