የሶማሊያ ፕሬዝዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ውዝግብ ወዴት ያመራ ይሆን?

ፕሬዝዳንት ፋርማጆ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሮብሌ

የፎቶው ባለመብት, BBC/Reuters

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ፋርማጆ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሮብሌ

የሶማሊያ ምርጫ መራዘሙን ተከትሎ የተፈጠረው አለመግባባት በፖለቲከኞች መካከል አለመተማመንን ከፈጠረ ሰነባበተ።

የአገሪቱ የታችኛው ምክር ቤት የምርጫ ማራዘሚያ ውሳኔ በማጽደቅ የፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆን የሥልጣን ዘመን ለሁለት ዓመት ማራዘሙን ተከትሎ ነበር አለመግባባቱ የተባሰው።

የሶማሊያ ዓለም አቀፍ አጋሮች እና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች የሥልጣን ማራዘሚያውን ውድቅ ከማድረግ ባለፈ ፋርማጆን በሥልጣን ቅሚያ ከሰዋል።

ይህን ተከትሎ በርዕሰ መዲናዋ ሞቃዲሾ የሰዎችን ህይወት የነጠቀ ሁከትና ብጥብጥ ተከስቶ ነበር። ባለፈው ሚያዝያ በፌደራል መንግሥቱ ደጋፊዎችና በተቃዋሚዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ቢያንስ አስር ሰዎች ተገድለዋል።

የውዝግቡ ቁልፍ ተዋናዮች

ተቃዋሚዎች የፕሬዝዳንት ፋርማጆ የሥልጣን ዘመን ስላበቃ ከእንግዲህ እውቅና አንሰጥም ብለዋል። ይህንንም ተከትሎ ናሽናል ሳልቬሽን ፎረም የተባለ ተሰሚነት ባላቸው የተቃዋሚዎች ብሔራዊ መድረክ አቋቋሙ።

ይህም የፋርማጆ ቀንደኛ ተቃዋሚ የሆኑት የሴኔቱ አፈ ጉባኤ አብዲ ሀሺ አብዱላሂ፣ የጁባላንድ እና ፑንትላንድ መሪዎችን ያካተተ ጥምረት ነው። ሕገ-መንግሥታዊ አይደለም ያሉት የስልጣን ማራዘሚያ ላይ "አስፈላጊ እርምጃዎችን እንወስዳለን" ሲሉም ዛቱ።

የፑንትላንድ ፕሬዝዳንት ሰኢድ አብዱላሂ ዴኒ እና የጁባው አቻቸው አህመድ መሐመድ ኢስላም በሞቃዲሾ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ተገናኝተው ነበር። ተወካዮቹን "ሶማሊያን ከማይቀረው የትርምስ አዘቅት ውስጥ እንዳትገባ እንዲያድኑ" ጠይቀዋል።

የፕሬዝዳንታዊ ዕጩዎች ምክር ቤት ፋርማጆን ለመተካት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው የፕሬዝዳንታዊ ዕጩዎች ጥምረት ነው። በቀድሞው ፕሬዝዳንት ሻሪፍ ሼክ አህመድ የሚመራ ሲሆን ፕሬዚዳንቱን "የጦር አበጋዝ" ብለዋቸዋል።

በወቅቱ አሜሪካ፣ እንግሊዝ እና የአውሮፓ ሕብረት የፕሬዝዳንቱን የሥልጣን ጊዜ የማራዘሙ ውሳኔ ሶማሊያ ወደ ሠላምና መንግሥት ግንባታ የምታደርገውን ጉዞ የሚያደናቅፍ ብለዋል። ግንኙነታቸውን በድጋሚ እንደሚያጤኑትም አስጠንቅቀዋል።አሜሪካ "ሰላምን እና መረጋጋትን በማደናቀፍ" በሥልጣን ማራዘሙ በተሳተፉት ላይ ማዕቀብ እንደምትጥልም ዝታ ነበር

የአፍሪካ ሕብረት የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤት የሥልጣን ጊዜ ማራዘሙን ውድቅ አድርጎታል። የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የሶማሊያ መሪዎች በምርጫ ውዝግቡ ዙሪያ ውይይት እንዲቀጥሉ ያቀረበውን ሃሳብ እንደሚደግፍም አስታውቋል።

ፕሬዝዳንት ፋርማጆ ከፍተኛ ተቃውሞ ቢቀርብባቸውም በታችኛው ምክር ቤት የሕዝብ እንደራሴዎች እና በጋልሙዱግ፣ በሂውማሌ እና በደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ሰፊ ድጋፍ አላቸው።

የፌዴራል መንግሥት ፈተና

የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሥርዓት ሥር የሰደደውን የጎሳ ግጭት ለማስቆም እና አሃዳዊ መንግሥት ለመመስረት የሚደረገው ጥረት በመሰናከሉ የተመሠረተ ነው። የተከፋፈለና ደካማ ቢሆንም የብሔራዊ ደኅንነት ግንባታው እያዘገመም እንዲጓዝ መንገዱን ጠርጓል።

አገሪቱ ከ30 ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ዓለም አቀፉ የምጣኔ ሃብት ሥርዓት ለመቀላቀልም የፋይናንስ ተቋማቷን እንደገና አደራጅታለች።

ምርጫው ያስከተለው አለመረጋጋት በማዕከላዊ መንግሥት እና ቀድሞውንም የፋርማጆን ሥልጣንን 'በሚያኮስሱት' አንዳንድ የክልል መንግሥታት መካከል ውዝግቡን አጡዞታል።

እአአ መስከረም 2018 አምስት የአገሪቱ የክልል ፕሬዚዳንቶች በሥልጣን እና በሃብት ክፍፍል አለመግባባት ምክንያት ከፌዴራል መንግሥት ጋር እንደማይተባበሩ አስታውቀዋል።

ፕሬዝዳንት ፋርማጆም ለምላሽ አልዘገዩም። ክልሎችን በራሳቸው ቁጥጥር ስር ማድረግ ጀመሩ። ተቀናቃኝ ሊሆኑ የሚችሉትን በማንሳት አጋሮቻቸውን በጋልሙዱግ እና በደቡብ ምዕራብ ግዛቶች አስቀምጠዋል።

የፌዴራሉ መንግሥት በፑንትላንድ እና በጁባላንድ ባሉ ምርጫዎች ላይ ተመሳሳይ ተጽዕኖ ማሳደር ግን አልቻለም። የእነዚህ አካባቢ መሪዎች ፋርማጆ እንደገና እንዳይመረጡ እየሠሩ ነው።

ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ ሞቃዲሾ ውስጥ ግጭት ባጋጠመበት ጊዜ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ ሞቃዲሾ ውስጥ ግጭት ባጋጠመበት ጊዜ

መስከረም ላይ የተደረገው ስምምነት

ፕሬዝዳንት ፋርማጆ የሥልጣን ጊዜ በይፋ ያበቃው በፈረንጆቹ የካቲት ወር ላይ ቢሆንም አዲስ ፕሬዝዳንት እንዴት እንደሚመረጥ በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት ምርጫው ተራዝሟል።

ለምርጫው መስተጓጎል ፕሬዝዳንቱ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ እርስ በእርሳቸው እየተወነጃጀሉም ነው።

ብሔራዊው የምርጫ ኮሚሽን ቀጥተኛ ተሳትፎ ያለው ሕዝባዊ ምርጫ ለማድረግ እንደማይቻል አስታወቀ። ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ለማዘጋጀት እስከ 13 ወራት ድረስ እንደሚያስፈልገው እአአ ሰኔ 2020 ለሕዝብ እንደራሴዎች ገለጸ።

የጁባላንድ፣ ፑንትንትላንድ እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች የምርጫውን መዘግየት ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ እአአ ሐምሌ 2020 አስደንጋጭ ነበር የተባለለት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሐሃሰን አሊ ኬይሬ ከሥልጣን መነሳት በምርጫው ሂደት ላይ ያላቸውን እምነት ይብስ ሸረሸረው።

የጁባላንድ እና የፑንትላንድ መሪዎች በማዕከላዊው ዱሳማሬብ ከተማ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ አልነበሩም። በስብሰባው ከምርጫ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ የመጀመሪያ ስምምነት ተደርሷል።

እአአ መስከረም 17 ቀን 2020 ከሳምንታት የዓለም አቀፍ ግፊት በኋላ በምርጫ ሁኔታዎች ላይ ስምምነት ተፈረመ።

በስምምነቱ መሠረት ሁለት የምርጫ ክልሎች በእያንዳንዱ ክልል ይኖራሉ። ምርጫዎች የሚካሄዱት በየክልል ተሰብሳቢዎች ላይ የተመሠረተ ሲሆን በእያንዳንዱ የምርጫ ክልል ውስጥ 101 የምርጫ ልዑካን ድምጽ ይሰጣሉ። በአማጽያን ጥያቄ መሠረት ምርጫውን በበላይነት የሚቆጣጠር ብሔራዊ እና ክልላዊ የምርጫ ኮሚቴዎች እንዲቋቋሙ ተወሰነ።

የጁባላንዱ ማዶቤ እና የፑንትላንዱ ዴኒ በፌዴራል መንግሥት የተቋቋመውን የምርጫ ኮሚሽን ባለመቀበላቸው የስምምነቱ ትግበራ ድጋሚ እንቅፋት ገጠመው። የፀጥታ አዛዦች እንዲነሱ እና ፓርላማው እንዲበተንም ጠየቁ።

የምርጫውን መዘግየት አስቀድሞ የገመተው የፌዴራልሉ ፓርላማ እአአ ኅዳር 2020 አዲስ ተመራጮች እስኪተኩ ድረስ ሁሉም የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎች ሥልጣን ላይ እንዲቆዩ ውሳኔ አስተላልፏል።

የጎሳ ፖለቲካ እና ግጭት

አለመተማመኑ እየጠነከረ ሲሄድ ፖለቲከኞች እና ከፍተኛ የደኅንነት ባለሥልጣናት ወደ ጎሳቸው መመሸግ ጀመሩ። እነዚህም በጎሳ ሚሊሻዎች፣ በጎበዝ አለቆች እና በቀድሞ የጦር መሪዎች የሚጠበቁ ናቸው።

የተወሰኑ የተቃዋሚ የፓርቲ አመራሮች ለትጥቅ ትግል መዘጋጀት ያዙ። የጦር መሳሪያዎችና ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች የገዙም አሉ።

በመዲናዋ ሞቃዲሾ የዘገየውን ምርጫ የሚቃወሙ ሰልፈኞችን በሚደግፉ ወታደሮች እና በፖሊስ መካከል መጋቢት 15 ግጭት ተፈጠረ። የፖሊስ መኮንኖቹ በቱርክ የሰለጠነው ልዩው የሃርማድ የፖሊስ ኃይል አባላት ነበሩ። ከዚህ በፊት መንግሥት ፍላጎቱን በክልል መንግሥታት ላይ ለመጫን ይህን ልዩ ኃይል ይጠቀም ነበር።

የቀድሞው የሞቃዲሾ የፖሊስ አዛዥ ሳዲቅ ኦማር ሐሃሰን (ሳዲቅ ጆን) እአአ ሚያዝያ 13 በምርጫ ውዝግብ ላይ ለመወያየት የተዘጋጀውን የፓርላማ ስብሰባ በማገድ ፊታቸውን መንግሥት ላይ አዞሩ። ከኃላፊነት ተነስተው ማዕረጋቸውም ተገፈፈ።

የቀድሞው የፖሊስ አዛዥ ከቀናት በኋላ በጎበዝ አለቆች እና ከጎሳቸው በተገኙ ሚሊሺያዎች እየተጠበቁ በከተማው ዳይናል አካባቢ ካምፕ መሠረቱ።

መንግሥት የታጠቁ የፀጥታ ኃይሎችን በአቅራቢያው ወደሚገኙ አካባቢዎች በማሰማራቱ ውጥረቱ ዋና ከተማዋን አዳርሷል።

በኋላ ላይ ሁኔታው ተረጋጋ።

ምርጫው መፍትሔ ያገኘ መሰለ

ሚያዝያ ላይ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ የሥልጣን ዘመናቸውን ለሁለት ዓመታት ለማራዘም ያደረጉትን ሙከራ ማቆማቸውን ይፋ አደረጉ።

ለሕዝቡ ባደረጉት ንግግርም አዲስ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዲካሄድ ጥሪ አቅርበው ጠቅላይ ሚኒስትራቸው ያደረጉትን ጥረት አድንቀዋል።

በቀጣይ ቀናትም የሶማሊያ የፖለቲካ መሪዎች ምርጫ ለማካሄድ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ተስማሙ።

ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ ሁሴን ሮብሌ እና የክልል ፕሬዝዳንቶች በ60 ቀናት ውስጥ ሂደቱን ለመጀመር የሚያስችል ስምምነትም ተፈራርሙ።

ምርጫው በተለያየ የጊዜ ሰሌዳ እንደመካሄዱ ሐምሌ ላይ በአንዳንድ አካባቢዎች ምርጫው ተጀመረ።

የሶማሊያ የጁባላንድ ክልል ምክር ቤት ኢሊያስ ባዳል ጋቦሴን የመጀመርያው የሶማሊያ ሴኔት አባል አድርጎ መርጧል።

የጎሳ መሪዎች የፓርላማ አባላትን የሚመረጡበት የተወሳሰበው የሶማሊያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ከኅዳር ወር ጀምሮ እየተካሄደ ሲሆን ከቀናት በፊት መጠናቀቅ ነበረበት። ግን እሳካሁን አላለቀም።

የጠፋችው የደኅንነት ሠራተኛ ኢክራን ታህሊል
የምስሉ መግለጫ, የጠፋችው የደኅንነት ሠራተኛ ኢክራን ታህሊል

የደኅንነት ሠራተኛዋ መጥፋት

መስከረም ላይ ደግሞ ሌላ ውዝግብ ተከተለ።

በዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ ኢክራን ታህሊል የተባለች የደኅንነት ሠራተኛ በመጥፋቷ ምክንያት በፕሬዝዳንቱ እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ መካከል ውዝግብ አገረሸ።

የደኅንነት ቢሮው ኢክራን ታህሊል በአልሸባብ ታግታ መገደሏን ቢገልጽም፣ አሸባሪው ቡድን ጉዳዩን አስተባብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ ሁሴን ሮብሌ የደኅንነት ቢሮው ኃላፊ ጉዳዩን የያዙበት መንገድ ቅር አሰንቶኛል በማለት ከሥራ አግዷቸው።

ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ መሐመድ ደግሞ የደኅንነት ኃላፊው ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ አዘዙ።

ከጠፋችው የደኅንነት ሠራተኛ በተጨማሪ በደኅንነት ቢሮው ተጠሪነት ጉዳይ ጭምር ነው የሁለቱን አውራ ፖለቲከኞች ልዩነት ያሰፋው።

በሁለቱ መሪዎች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት የሶማሊያ የፀጥታ ኃይሎችን የመከፋፈል አደጋም አስከትለ።

ጥቅምት ላይ ሁለቱ ባለሥልጣናት የአገሪቱን ምርጫ ሊያደናቅፍ ይችላል የተባለለትን አለመግባባት ለማቆም ተስማሙ።

የጠፋችውን የደኅንነት ቢሮ ባልደረባ ጉዳይም ለፍርድ ቤት እንደሚተው ተስማምተዋል።

አዲሱ ውዝግብ

ከቀናት በፊት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ሞሐመድ ፋርማጆ የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሐመድ ሁሴን ሮብሌን ከሥልጣናቸው ማገዳቸውን አስታወቁ።

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መታገድ እንደ ምክንያት የቀረበው ሥልጣንን አላግባብ መጠቀምና የመንግሥት የሆነ መሬትን መቀራመት የሚል ነው።

ፕሬዝዳንቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሶማሊያ ብሔራዊ ሠራዊት ይዞታ የሆነን የሕዝብ መሬትን ወስደዋል እና የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር በሚያካሂደው ምርመራ ውስጥ ጣልቃ ገብተዋል ሲሉ ከሰዋቸል።

ፕሬዝዳንት ፋርማጆ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የሶማሊያ ባሕር ኃይል አዛዥ የሆኑትን ጄነራል አብዲሃሚድ ሞሐመድ ዲሪርንም ከኃላፊነታቸው አግደዋል።

ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሐመድ ሁሴን ሮብሌ የቀረበባቸውን ክስ ውድቅ አድርገው ፕሬዚዳንቱ መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ ሞክረዋል በማለት የወነጀሏቸው ሲሆን በሥልጣናቸው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

ከዚያም አልፈው የአገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች ትዕዛዝ መቀበል ያለባቸው ከፕሬዝዳንት ፋርማጆ ሳይሆን ከእሳቸው እንደሆነም አሳስበዋል።

አዲሱ ውዝግቡ በሶማሊያ ተጨማሪ አለመረጋጋት እንዳያስከትል ስጋት ፈጥሯል።

በሶማሊያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ መሪዎቹ "ከጸብ ጫሪ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ እና የኃይል እርምጃዎችን እንዲያስወግዱ" አሳስቧል።

አገሪቱ በተለያዩ ጎራ በተሰለፉ ፖለቲከኞች እና በጎሳዎች መካከል ፈተና ውስጥ የምትገኝ ሲሆን ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ካለው አልሸባብ አማጽያን ጋርም እየተዋጋች ነው።