የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትራቸውንና የባሕር ኃይል አዛዣቸውን ሥልጣን አገዱ

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ሞሐመድ ፋርማጆ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሐመድ ሁሴን ሮብሌን ከሥልጣናቸው ማገዳቸውን አስታወቁ።
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መታገድ እንደ ምክንያት የቀረበው ሥልጣንን አላግባብ መጠቀምና የመንግሥት የሆነ መሬትን አላግባብ መያዝ ሲሆን የአገሪቱ ማስታወቂያ ሚኒስትር ረዳት ግን እርምጃውን "ቀጥተኛ ያልሆነ መፈንቅለ መንግሥት" ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሶማሊያ ብሔራዊ ሠራዊት ይዞታ የሆነን የሕዝብ መሬትን በመውሰድ እና የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር በሚያካሂደው ምርመራ ውስጥ ጣልቃ ገብተዋል ሲሉ ከሰዋቸል። ሌሎች ሚኒስትሮች ግን በሥራቸው ላይ ይቀጥላሉ በማለት እገዳው ሮብሌን የሚመለከት መሆኑን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሮብሌ በፕሬዝዳንቱ ውሳኔ ላይ እስካሁን አስተያየት አልሰጡም። ነገር ግን የመንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት ሞሐመድ ኢብራሂም ሞአሊሙ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ የፕሬዝዳንቱን ውሳኔ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም ሲሉ ተቃውመውታል።
ጨምሮም ጠቅላይ ሚኒስትር ሮብሌ የሚጠበቅባቸውን መንግሥታዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ይቀጥላሉ ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ እሁድ ዕለት የምክር ቤት ምርጫን በማደናቀፍ አንዳቸው ሌላኛቸውን ሲከሱ ተሰምተው ነበር።
ይህም መንግሥት ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ካለው ታጣቂ ቡድን አልሻባብ ጋር በሚያካሂደው ጦርነት ላይ የራሱ የሆነ ተጽእኖ ይኖረዋል ሲሉ ተንታኞች ያስጠነቅቃሉ።
ፕሬዝዳንት ፋርማጆ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የሶማሊያ ባሕር ኃይል አዛዥ የሆኑትን ጄነራል አብዲሃሚድ ሞሐመድ ዲሪርንም ከኃላፊነታቸው አግደዋል።
ሁለቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከኃላፊነታቸው የታገዱት እየተካሄደ ያለ ምርመራ እስኪጠናቀቅ መሆኑም ተገልጿል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ሮብሌ ጽህፈት ቤት አካባቢ የፀጥታ ሀይሎች መሰማራታቸው የተነገረ ሲሆን ረዳት የማስታወቂያ ሚስትሩ አብዲራሂም ዩሱፍ አዳል ግን ይህ ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥራቸውን ከማከናወን እንደማያደናቅፋቸው ገልጸዋል።
ረዳት ሚኒስትሩ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ "ሰኞ ጠዋት ላይ እየተካሄደ ያለው ነገር ቀጥተኛ ያልሆነ መፈንቅለ መንግሥት ነው፤ ነገር ግን አይሳካም" ብለዋል።
መስከረም ላይ አንዲት የደኅንነት ሠራተኛ መገደልን ተከትሎ ከሚደረግ ምርመራ ጋር በተያያዘ ፕሬዝዳንት ፋርማጆ የጠቅላይ ሚኒስትር ሮብሌን ባለሥልጣናትን የመሾምና ያማሰናበት ሥልጣናቸውን አግደው ነበር። በዚህም ሳቢያ በሁለቱ መካከል ከፍተኛ ውጥረት ከተፈጠረ በኋላ በስምምነት እንዲረግብ ተደርጎ ነበር።
በፕሬዝዳንቱና በጠቅላይ ሚኒስትሩ መካከል ያለው አለመገባባት የቆየ ሲሆን ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ላይ ፕሬዝዳንቱ የሥልጣን ዘመናቸውን በሁለት ዓመት ሲያረዝሙ ነበር የጀመረው።
ይህንንም ተከትሎ ለሁለቱም ባለሥልጣናት ታማኝ የሆኑ በሠራዊቱ ውስጥ ኣሉ አንጃዎች በዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ ውስጥ የሚገኙ ቁልፍ ቦታዎችን በመያዝ ግጭቶች ተከስተው ነበር።
ይህ ፍጥጫ መፍትሔ ያገኘው ፕሬዝዳንት ፋርማጆ ጠቅላይ ሚኒስትር ሮብሌን የአገሪቱ የደኅንነት ተቋም ኃላፊ ካደረጉ በኀዕላ እና እንዲዘገይ የተደረገው የምክር ቤት አባላትና የፕሬዝዳንት ምርጫ ለማካሄድ ከተስማሙ በኋላ ነበር።
በሁለቱ ዋነኛ ፖለቲከኞች መካከል የተከሰተው አለመግባባት ከቁጥጥር ውጪ እንዳይወጣና በደጋፊዎቻቸው መካከል ወታደራዊ ግጭት እንዳይከሰት ተሰግቷል።














