አልጄሪያ እና የማንነት ጥያቄ፡ እነማን እንደ አፍሪካዊ ይቆጠራሉ?

የአልጄሪያ ደጋፊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአፍሪካ ጸሐፊያን የተጻፉ ደብዳቤዎችን በምናስተናግድበት ተከታታይ ፕሮግራም አልጄሪያዊ-ካናዳዊ ጋዜጠኛ ማሄር መዛሂ አህጉሪቷ ታላቅ ለተባለው የእግር ኳስ ዝግጅቷ ሽር ጉድ በምትልበት ወቅት አፍሪካዊ ማንነት ምንድን ነው? የሚለውን አጢኖታል።

Short presentational grey line

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከፓን አፍሪካኒዝም ፅንሰ ሐሳብ አራማጆች አንዱ የሆኑትና አገራቸው ጋናን በአውሮፓውያኑ 1957 ከቅኝ ግዛት ቀንበር ያላቀቁት ታላቁ ክዋሜ ንክሩማህን ጥቅስ አገኘሁ።

ይህም "አፍሪካ አንድ አህጉር፣ አንድ ሕዝብ እና አንድ አገር ነች። አገር ለመመሥረት አንድ ቋንቋ፣ የጋራ ክልል እና የጋራ ባህል እንዲኖር ያስፈልጋል የሚለው አስተሳሰብ በጊዜ ወይም በሳይንሳዊ ወይም በተጨባጭ የእውነታ ፍቺ ላይ መቆም አልቻለም" ይላል።

እኛ አፍሪካውያን ከአህጉሪቱ ቀደምት ሕዝቦች ባለፈ የምንለይበትን ባህሎችን፣ ማንነታችን እንዲሁም ሌሎች ፅንሰ ሐሳቦችን ለበርካታ ጊዜ ከማመላለሴ ጋር ተያይዞ ይህ ንባብ የተለየ እሳቤ ፈጠረብኝ።

በተለይም በባሕር ዳርቻ የሚኖሩና ከሌሎች ባህሎች እና ማኅበረሰቦች ጋር ግንኙነትን መመሥረት የቻሉ አፍሪካውያን ማንነት በተደጋጋሚ ይነሳል።

ለምሳሌ በሰሜን አፍሪካ ነዋሪ የሆኑት የማግረብ ሕዝቦች [ማግሬብ በመባል የሚታወቀው የሰሜን አፍሪካ ምዕራቡን ክፍልና የአረቡ ዓለምን የሚያጠቃልል ነው] ከሜድትራንያን ባህል ጋር የቀረበ ግንኙነት እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካ ነዋሪ የሆኑ ሕዝቦች ባህላቸውንና ልምዳቸውን ከአረብ ባሕረ ሰላጤና ከሕንድ ይመጡ ከነበሩ ነጋዴዎች ጋር ያገናኙታል።

በመጻሕፍት ላይ የተመዘገበው የኬፕ ቨርዴ ታሪክ የሚጀምረው በ15ኛው ክፍለ ዘመን በፖርቹጋል ቅኝ ግዛት መስፋፋትና ከባርነት ጋር በተያያዘ ነው።

አፍሪካዊአረብ ማንነት አጣብቂኝ

ክዋሜ ንክሩማህ ተመሳሳይ የጋራ ቋንቋ፣ ግዛት እና ባህል ለአህጉሪቷ የማይቻል መሆኑን የገለጹበት ዋነኛ ምክንያት የአፍሪካ ስፋት ነው ብዬ አስባለሁ።

በተለይም ይህንን የተረዳሁት የሰሃራ በረሃን ከጎበኘሁ በኋላ ነው።

ሰፊውን አሸዋማ በረሃ የጎበኘ ማንኛውም ግለሰብ ሕይወቱም ሆነ እሳቤው እንደሚቀየር ማስረጃ ነው።

የሰሃራ በረሃ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የበረሃው ትልቅነት የብቸኝነት ስሜት፣ ትህትና እንዲሁም ለየት ያለ የሰላም ሁኔታ ይፈጥራል።

ይሄም ብቻ አይደለም። የበረሃው የማያልቅ የሚመስለው ስፋት በሰሜን አፍሪካና በተቀረው አህጉር መካከል እውነተኛ አጥር ይፈጥራል።

በአንድ ወቅት የአልጄሪያ ዋና ከተማ የሆነችው አልጀርስ ከሌጎስ ይልቅ ለፊንላንዷ መዲና ሄልሲንኪ፣ ከናይሮቢ ይልቅ ለዱባይ፣ ከሃራሬ ይልቅ ለኒውዮርክ ቅርብ እንደሆነች አንብቤ ነበር።

ከርቀት በተጨማሪ በቅኝ ግዛት ምክንያት የተፈጠረው ትስስር እና የጅምላ ፍልሰት የተወሰነው የአፍሪካን ክፍል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የዘመናችን የማንነት አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል።

ምንም እንኳን እሳቤው የሚረብሽ ቢሆንም አፍሪካውያን ወገኖቼ "ለምን ሰሜን አፍሪካውያን ራሳቸውን እንደ አፍሪካዊ አይቆጥሩም?" ብለው ሲጠይቁኝ ፈፅሞ አይገርመኝም።

በተለይም ወደ ካሜሮን የአፍሪካ ዋንጫን ለመከታተል ጉዞዬን ለማድረግ ስዘጋጅ ይህ ጥያቄ በተደጋጋሚ እንደሚጠብቀኝ እርግጠኛ ነኝ። የአፍሪካ ዋንጫ ሰሜን አፍሪካውያን በጉጉት የሚጠብቁት ነው። የአሁኗ ሻምፒዮንም አልጄሪያ ናት።

እርግጥ ነው፣ ጥቂት ሰሜን አፍሪካውያን ባህላቸውንና ማንነታቸውን በመጥቀስ ከሌሎች አፍሪካውያን የበለጥን ነን በሚል ስሜት ሲኮፈሱ ይታያል፤ ይህ ምን ማለት እንደሆነ ባይታወቅም።

በዚህም አመለካከታቸው የተነሳ በብዙዎች ዘንድ በንቀት ቢታዩም ምንም የሐዘኔታ ስሜት አይሰማኝም።

በተገላቢጦሽ በአህጉሪቱ ትክክለኛ አፍሪካዊ አይደላችሁም ተብለው አንዳንድ ሰሜን አፍሪካውያን ማንነታቸው ሲነጠቁ እንዲሁም በአንዳንድ አረብ አገራትም አፍሪካዊ ናችሁ በሚል ተመሳሳይ ነገር ይደርስባቸዋል።

ለምሳሌ በቅርቡ በተካሄደው የ2021 የፊፋ የአረብ ዋንጫ፣ አንዳንድ የአፍሪካ እግር ኳስ ጋዜጠኞች ባልደረቦቼ አልጄሪያ በአረብ ውድድር ውስጥ የምትጫወተው ለምን እንደሆነ ጠይቀውኛል።

ሰሜን አፍሪካዊ ማንነትን በተመለከተ ያሉትን ሁሉንም እሴቶች መቀበል ማለት አፍሪካዊ ማንነትን መተው እንደሆነ አንዳንድ አፍሪካውያን ይሰማቸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የአረቡ ዓለም በበኩሉ በአረብኛ ቋንቋ ዘዬው፣ ጨዋነት ጎድሎታል በሚሉት ባህርዩና፣ በአውሮፓ ሥነ ሕንፃው ምክንያት ሰሜን አፍሪካውያን ከማግሬብ ጋር ያለው ግንኙነት የተቋረጠ ነው ብለው ያስባሉ።

እነዚህን ሁሉ ጉዳዮች በማሰላስልበት ወቅት እነዚህን ሁሉ ማንነቶች ከማግለል ይልቅ አካታች አካሄድን እመርጣለሁ።

ከሜዲትራኒያን ባሕር- ጣፋጭ የባሕር ምግቦች፣ የበለፀጉ ጭማቂ የወይራ ፍሬዎች እና በአንፀባራቂ የፀሐይ ብርሃን እዝናናለሁ።

ከአረብ አገር ቅድመ አያቶቼ ሐይማኖቴን እና ወላጆቼ የሚናገሩትን ቋንቋ ተምረዋል።

ከአፍሪካ ከቁሳዊው ወይም ከመሬቱ ጋር ያለኝን ቁርኝት ወርሻለሁ፣ ግን ያ ብቻ አይደለም።

ከምንም በላይ፣ ምንም እንኳን ግልጽ ያልሆነ እና የተዘበራረቀ ቢመስልም፣ አፍሪካዊ መሆን ከምንም በላይ የነቃ ውሳኔ ይመስለኛል።

የአይቮሪኮስት ደጋፊዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

'አፍሪካ በእኔ ውስጥ ተወለደች'

ሌላው ታዋቂ የንክሩማህ ጥቅስ፣ ምን ለማለት እንደፈለግኩ በደንብ ያስረዳል።

"እኔ አፍሪካዊ የሆንኩት አፍሪካ ስለተወለድኩ ሳይሆን አፍሪካ በእኔ ውስጥ ስለተወለደች ነው"

ስለዚህ አፍሪካዊ መሆን ቀላል እና ውስብስብ ነው።

አፍሪካዊነት የሚገለጸው አንዱ ለሌላው የሚበጀውን እና ለአህጉሪቱ የሚበጀውን ለማወቅ በመፈለግ ነው።

በአህጉሪቱ ካሉ ኩሩ እኩዮቼ ጋር ስሆን፣ ዘልቆ የሚገባው በጣም ጠንካራው የጋራ መለያችን አፍሪካዊ መሆናችን ነው።

ለእኔ ይህ የአፍሪካዊ ማንነት በአፍሪካ ዋንጫ ላይ የሚንጸባረቅ ሲሆን ይህም ደጋፊዎች፣ ቡድኖች እና ጋዜጠኞች አገራቸውን የሚደግፉበት በአፍሪካዊነታቸው ከፍተኛ ደስታን የሚያገኙበትና የሚኮሩበት መድረክ ነው።

በአውሮፓውያኑ 2019 የዓለም ዋንጫ ከደቡብ አፍሪካ ወደ ግብፅ በመኪና ለመጓዝ የወሰነውን የዚምባብዌ ቀንደኛ የእግር ኳስ ደጋፊ አልቪን ዛካታንን እንደ ምሳሌ እንውሰድ።

"ድንበር የሌላት አፍሪካን" የመሻት መልዕክቱ በውድድሩ ላይ በነበሩት ሁሉ ከፍተኛ ተቀባይነትን አግኝቷል።

ውድድሮቹን በሚዘግቡት 54ቱም የአፍሪካ አገራት ጋዜጠኞችም መካከል ግንኙነታችን የተጠናከረ ነው። የተለያዩ ስልኮችን እንቀያየራለን፣ ምግብ አብረን እንበላለን፣ ያለፉ ውድድሮችንም እናስታውሳለን።

በአውሮፓውያኑ 2019 የተካሄደውን የፍጻሜ ጨዋታ ተከትሎ የአልጄሪያ አማካይ አድሌኔ ጉዲዮራ ከሴኔጋል፣ ሞሮኮ፣ አይቮሪኮስት እና ናይጄሪያ የተውጣጣ የተጋጣሚዎቹን የእግር ኳስ ማሊያዎች የያዘና በጣሪያ ላይ የተነሳውን ፎቶ ለጥፏል።

"ከአፍሪካ ወንድሞቼ ጋር በቤት ውስጥ እያከበርኩ ነው። ከደቡብ እስከ ሰሜን፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ላላችሁ ሁሉ ለዚህ አስደናቂ ድግስ መላው አፍሪካውያን እናመሰግናለን" ብሏል።