ደቡብ አፍሪካ በፀረ አፓርታይድ ጀግናው ሊቀ-ጳጳስ ዴዝሞን ቱቱ ህልፈት ሐዘን ተቀምጣለች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ደቡብ አፍሪካ በተለይም በፀረ-አፓርታይድ ትግል መሪነታቸው የሚታወቁት የ90 ዓመት እድሜ ባለጸጋ የነበሩት የሊቀ-ጳጳስ ዴዝሞን ቱቱን ህልፈት ተከትሎ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የሐዘን ሥነ-ሥርዓቶችን አዘጋጅታለች።
በመንግሥታዊ ብሔራዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት የሚሸኙት ሊቀ ጳጳሱ ከዚያ በፊት ለሁለት ቀናት በኬፕታውን የስንብት ሥነ-ሥርዓት ይደረግላቸዋል ተብሏል።
የቫቲካኑ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፣ የእንግሊዟ ንግሥት ኤልዛቤት እና ሌሎችም በርካታ የዓለም መሪዎች በሊቀ ጳጳሱ ህልፈት የተሰማቸውን ሐዘን በመግለጽ ላይ ናቸው።
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ በመግለጫቸው ዴዝሞን ቱቱ "ነጻ የወጣች ደቡብ አፍሪካን" ለማምጣት ሰርተዋል ብለዋል።
ዴዝሞን እ.ኤ.አ. በ 1984 አፓርታይድን ለመዋጋት ላደረጉት ትግል የዓለም የኖቤል ሽልማት ተበርክቶላቸው ነበር።
የቱቱ ህልፈት ደቡብ አፍሪካውያን ለአገሪቱ ብሔራዊ ጀግኖች በኬፕታውን ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል በመቆም ክብራቸውን ከገለጹ ከሳምንታት በኋላ የተከሰተ ነው።
"ዛሬ ጠዋት ህልፈታቸውን ስሰማ በጣም ስሜታዊ ሆኜ ነበር" ሲል ብሬንት ጎልያድ የተሰኘ ሐዘንተኛ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንባ እየተናነቀው ተናግሯል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን "በእውነተኛው የእግዚያብሔር ብሎም የሕዝብ አገልጋይ ህልፈት ልቤ ተሰብሯል። የቱቱ አበርክቶ ድንበርን የሚሻገር ብሎም ለዘመናት ሲስተጋባ የሚኖር ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ "አስተማሪ፣ ጓደኛ እንዲሁም የሞራል መለኪያ" ሲሉ ገልጸዋቸዋል። የእንግሊዟ ንግሥት ኤልዛቤት ዴዝሞንን አግኝተው ያነጋገሯቸውን ውድ ወቅቶች ሁሉ ብሎም ተጫዋችነታቸው እና ቀልዶቻቸውን እንደሚያስታውሱ ገልጸዋል።
“የሊቀ-ጳጳስ ዴዝሞን ቱቱ ህልፈት ከደቡብ አፍሪካዊያን አልፎ በመላው ታላቋ ብሪታኒያ፣ በሰሜን አየርላንድ እንዲሁም በኮመን ዌልዝ አገራት ባሉ በርካታ ሰዎች ዘንድ የሐዘን ስሜትን የፈጠረ ነው። በእነዚህ አገራት ዴዝሞን ቱቱ ከፍተኛ ተወዳጅነት እና ክብር ነበራቸው" ሲሉ ንግሥቲቱ ተናግረዋል።
የቫቲካኑ ፖፕ ፍራንሲስ "ለቤተሰቦቻቸው እና ለሚወዷቸው በሙሉ መጽናናትን እመኛለሁ" ሲሉ የቫቲካንን መግለጫ ልከዋል።
"ዴዝሞን ስለ አግልግሎት እና ስለወንጌል የሚጨነቁና ይህንንም የተለያየ ዘር ያላቸው ሰዎች እኩል መሆናቸውን፤ በተለይም በትውልድ አገራቸው ደቡብ አፍሪካ እርቅ እንዲመጣ ቅዱስነታቸው ነፍሳቸውን ለተወደደው የእግዚአብሔር ምህረት የሰጡ ሰው ነበሩ" ሲሉ ፖፕ ፍራንሲስ በመግለጫቸው ላይ አስፍረዋል።
እንዲሁም የኔልሰን ማንዴላ ፋውንዴሽን በቱቱ ህልፈት የተሰማውን ሐዘን ገልጿል። "ቱቱ ኢ-ፍትሃዊነትን በአገር ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም ታግለዋል። ይህም ለመጪው የሰው ዘር የነጻነት እጣ ፈንታ ካላቸው የጠለቀ አስተሳሰብ የመነጨ ነበር። የተለየ ሰው፤ አሳቢ፤ መሪ እና ጠባቂ ነበር" ሲል ፋውዴሽኑ በመግለጫው አትቷል።












