የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አሰልጣኞች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዙሪያ ሊወያዩ ነው ተባለ

አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ

ሐሙስ ዕለት የፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ውይይት እንደሚያደርጉ የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ አስታወቁ።

በፕሪምየርሊ ሊጉ ሊደረጉ ከነበሩ 20 ጨዋታዎች መካከል ዘጠኙ ለሌላ ጊዜ የተላለፉ ሲሆን የሊጉ ክለቦች ሰኞ ዕለት ስብሰባ ካደረጉ በኋላ በበዓል ሰሞን ጨዋታዎች ላይ ለጊዜው ምንም አይነት ላለማድረግ ተስማምተዋል።

ሊቨርፑል ትናንት ረቡዕ ምሽት በካራባዎ ዋንኛ ሌስተር ሲቲተን በፍጹም ቅጣት ምት በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈ ሲሆን፣ አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ከአርሰናል ጋር የሚኖራቸው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ በደርሶ መልስ ከሚሆን በአንድ ጨዋታ ቢወሰን ምርጫቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

"እንደሚመስለኝ አንድ ጨዋታ ብቻ ቢደረግ ጥሩ ይሆናል። ነገር ግን እንደሚታወቀው የእኔ ሃሳብ በመሆኑ ብዙም ተቀባይነት ላይኖረው ይችላል'' ብለዋል።

"ሁለት ጨዋታዎች የሚደረጉ ከሆነ ተጫዋቾቼ ሁለት ጊዜ ሊጫወቱ ነው ማለት ነው። ነገር ግን ፍልሚያው በአንድ ጨዋታ ቢወሰን መልካም ነበር።''

ሊቨርፑል ትናንት ምሽት በነበረው ጨዋታ በሌስተር ሲቲ 3 ለ1 እየተመራ የነበረ ቢሆንም ከኋላ ተነስቶ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር አቻ ለመሆን ችሏል። ጨዋታው በዚያ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ሊቨርፑል በፍጹም ቅጣት ምት 5 ለ 4 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

ይህን ተከትሎም ሊቨርፑል በግማሽ ፍጻሜው ጥር ወር ላይ ከአርሰናል ጋር የሚጫወት ይሆናል።

ቀደም ብሎ ደግሞ የሊቨርፑሉ አምበል ጆርዳን ሄንደርሰን ከቢቢሲ ስፖርት ጋር ባደረገው ቆይታ "ማንም ሰው ስለ ተጨዋቾች ደኅንነት አያስብም'' ብሎ ነበር።

"ስለተጫዋቾች ደኅንነት የምናገረው አሁን ብቻ አይደለም፤ ላለፉት ስድስት ዓመታት በሙሉ የተጫዋቾች ደኅንነት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ሳሳስብ ነበር'' ብሏል።

"የእኔ አስተያየት እንደ ጠቃሚ ነገር ቢቆጠር ኖሮ በተደጋጋሚ እናገር ነበር። ነገር ግን እንደዚያ አይሰራም። ብቸኛው ማድረግ የምችለው ነገር ቢኖር ሰዎች እንዲነገጋገሩበት ማድረግ ነው።"

ትናንት ምሽት በካራባዎ ዋንጫ ዌስት ሃምን 2 ለ 1 ያሸነፈው ቶተንሀም አሰልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴም ቢሆኑ ተመሳሳይ አቋም እንዳላቸው አስታውቀዋል።

"ከሁለት ጨዋታዎች ይልቅ ውጤቱ በአንድ ጨዋታ ቢወሰን እመርጣለው። በተለይ ደግሞ አሁን ላይ ከምንኖርበት ሁኔታ አንጻር ጠቃሚ ይሆናል።"

በሌላ በኩል ደግሞ የሌስተር ሲቲው አሰልጣኝ ብሬንዳን ሮጀርስ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ እስከ 5 ተጫዋቾችን መቀየር እንዲችሉ በድጋሚ ሊፈቀድ ይገባል ብለዋል።