ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትግራይን ከበረራ ነጻ ቀጠና እንዲያደርግ የህወሓት ቃለ አቀባይ ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በትግራይ ክልል ላይ የተዋጊ አውሮፕላን በረራ እገዳን ጨምሮ ሌሎች ተገቢ እርምጃዎችን እንዲወስድ የህወሓት ቃለ አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ጠየቁ።
አቶ ጌታቸው ረዳ ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮኖች) ጨምሮ የአየር ኃይሉ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት እያደረሰ እንደሆነ ተናግረዋል።
በጦርነቱም ተሳታፊ ያሏቸው ወገኖች እየጨመሩና ጦርነቱም ቀጣናዊ (ዓለም አቀፋዊነት) መልክ መያዙን ጠቁመው ከዚህም ጋር ተያይዞ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኃላፊነት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ሠራዊቱ የሚፈጽመው የአየር ጥቃት ኢላማ የሚያደርገው የህወሓት የማሰልጠኛ ቦታ ወይም የጦር መሳሪያ መከማቻ መሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል።
ትግራይን ለሲቪል አገልግሎትና ለእርዳታ አቅርቦት ከሚደረጉ በረራዎች ውጪ ከበረራ ነጻ የሆነ ክልል ይደረግም ሲል ህወሓት በሊቀ መንበሩ ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ለተባበሩት መንግሥት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከቀናት በፊት መጻፋቸው ይታወቃል።
ለተመድ በተጻፈው ደብዳቤ ላይ ከአንድ ዓመት በላይ ባስቆጠረው የእርስ በርስ ጦርነት ህወሓት አስቸኳይ የሆነ የተኩስ አቁም ማወጁን አስታውቆ በአስቸኳይ ግጭቱ እንዲቆምና የሰላም ድርድር እንዲጀመር ጥሪ አቅርበዋል።
ከወራት በፊት የህወሓት ኃይል ሚዛን የበላይ የሆነ በመሰለበት ወቅት ወደ መዲናዋ አዲስ አበባም እያቀኑ መሆናቸውን ተናግረው ነበር።
የህወሓት ኃይሎች ካለፈው ዓመት ሰኔ መጨረሻ ወዲህ ከትግራይ አልፈው በአማራ እና በአፋር ክልሎች በርካታ ስፍራዎችን ተቆጣጥረው ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ፋኖ ጥምር ኃይል ባደረጉት መጠነ ሰፊ ጥቃት በህወሓት ተይዘው የነበሩ አካባቢዎችን ማስለቀቅ እንደተቻለም ተገልጿል።
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ታሪካዊቷን የላሊበላ ከተማን ጨምሮ በርካታ የሰሜን ወሎ አካባቢዎችን ከህወሓት በማስለቀቅ መንግሥት በቁጥጥሩ ስር ማድረጉን ያስታወቀ ሲሆን፤ የቀሩ አካባቢዎችን መልሶ ለመያዝ ዘመቻው ቀጥሏል ብሏል።
መንግሥት ከፍተኛ ሽንፈት ገጥሞት ነው ህወሓት የወጣው ቢልም ህወሓት በበኩሉ ወታደሮቹን ከአማራና ከአፋር ክልል ያስወጣው "ለሰላም ዕድል ለመስጠት" እንደሆነ እሁድ ዕለት ታኅሣሥ 10/2014 ዓ. ም በጻፈው ደብዳቤ አስፍሯል።
ድሮኖችን በሚመለከት አቶ ጌታቸው ምን አሉ?
በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች እየጨመሩ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ጌታቸው ይህም ወደ ሌላ ዙር እልቂት እንደሚያመራ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሊያሳስበው ይገባል ብለዋል።
"ትግራይ ለባለፉት 13 ወራት የዘር ማጥፋት ዘመቻ ተካሂዶባታል። አሁንም ለሌላ ዙር ዘር ማጥፋት እየተዘጋጁ ነው ስለዚህ ዓለም አቀፉ ማኅበሰብ የበረራ እግድን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ እርምጃዎች ሊወስድ ይገባል" ብለዋል።
ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) ሲቪል ዜጎችን ጨምሮ ያደረሱትን ውድመት ሪፖርት ይደረጋል። እነዚህንም ድሮኖች በማቅረብ በርካታ አገራት ሲጠቀሱ ይሰማሉ። ለመሆኑ እነዚህን ድሮኖች ለኢትዮጵያ መከላከያ የሚያቀርበው ማን ነው? የሚል ጥያቄ ቢቢሲ አቶ ጌታቸውን ጠይቋቸዋል።
አቶ ጌታቸው በበኩላቸው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በርግጠኝነት ድሮን እያቀረበች እንደሆነ ፈርጠም ብለው ተናግረዋል።
ከ13 ወራት በፊት ጦርነቱ ሲጀመርም የኤምሬትስ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በህወሓት መሳሪያዎች ላይ ጥቃት እንዳደረሱና ይህም ለኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል በጊዜያዊነት የአሸናፊነት ሚዛኑን አስጠብቋል ብለዋል አቶ ጌታቸው።
"ድሮን ለኢትዮጵያ በመስጠት ሌሎች አገራት እንዳሉ መረጃዎችን ያመላክታሉ" የሚሉት አቶ ጌታቸው ከነዚህም ውስጥ ቻይና ሚሳኤልና ድሮን በመሸጥና በማቅረብ እንዲሁም የኢራን እጅ እንዳለበት ይናገራሉ። ሌሎች አገራትም ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቆም አድርገዋል።
ከአስራ ሦስት ወራት በላይ ባስቆጠረው በዚህ ጦርነት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፣ ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በረሃብ አፋፍ ላይ ናቸው።
ከአሁኑ የህወሓት የሰላም ጥሪ ጋር ተያይዞ ቢቢሲ ለአቶ ጌታቸው ያቀረበላቸው ጥያቄ እንዲህ አይነት እልቂት ከመፈጠሩና ጦርነቱ ከመባባሱ በፊት የእንወያይ ጥያቄ ለምን አላቀረባችሁም፤ የህይወት መጥፋቱስ ይጸጽትዎታል ወይ የሚል ነው።
አቶ ጌታቸው ለዚህ ሲመልሱ "በሰዎች ህይወት መጥፋት፣ በሰላማዊ ሰዎች ይሁን ከየትኛውም ወገን ቢሆን የወታደሮች ህይወት መጥፋት ይቆጨኛል" ካሉ በኋላ ለድርድር በተቃራኒ የቆሙት እነሱ እንዳልሆኑም ጠቁመዋል።
የትግራይ ሕዝብ በከበባ ላይ እንዳለና የቴሌኮም አገልግሎትን ጨምሮ መብራትና መሰረታዊ የልማት አገልግሎት እንደሌለውና ሰብዓዊ እርዳታም ተቋርጦበታል ብለዋል።
"የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀሙበት ነው። ጦርነት አላማችን አይደለም። ይህንን ሁኔታ በወታደራዊ መንገድ ለለፍታት ፍላጎት ስላላቸው እና የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡም ችላ ማለትና ምላሽ ባለመስጠቱ" ወደ ጦርነቱ ተገደው እንደገቡ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም የሰብዓዊ እርዳታ ክልከላ ይፈፅማል የሚለውን ክስ እንደማይቀበልና ህወሓት ለእርዳታ እክል እንደፈጠረ ሲናገር ቆይቷል።
ከዚህ ቀደም ውይይት እንዲጀመር የአሜሪካ መንግሥትን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከአማራና አፋር ክልል እንዲወጡ ሲጠይቅ የነበረ መሆኑን አስታውሰው በአሁኑ ወቅት ከነዚህ ክልሎች መውጣታቸውና የጻፉት ደብዳቤ ለሰላምና ለድርድር ዝግጁ ነን ብለዋል።
ይህንን አስመልክቶ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ምላሽ አግኝተው እንደሆነ የቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ አቶ ጌታቸውን ጠይቆ በሰጡት መልስ፡
"ምላሽ የለም። ይህንን በምናገርበት በአሁኑ ወቅት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በመቀለ ብቻ ሳይሆን በደቡበ ትግራይ አካባቢዎችም እየተፈጸመ ነው። ለዚህም ነው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህንን ጥሪ በቁም ነገር መመልከት ያለበት" ብለዋል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።
በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ያሉ ሁሉም ወገኖች እንደ ጦር ወንጀል ሊቆጠሩ የሚችሉ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግና የስደተኛ ሕግ ጥሰቶችን መፈፀማቸውን የመብት ተቆርቋሪዎች ያወጧቸው ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
ከአስራ ሦስት ወራት በላይ ያስቆጠረው ይህ ጦርነት እንዲቋጭ አሜሪካን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረት እንዲሁም የሕብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ እና ሌሎች አጋሮች ጥረት ቢያደርጉም ፍሬ አላፈራም።












