በሙስና ተፈርዶባቸው የነበሩት የቀድሞው የዓለም አትሌቲክስ ኃላፊ አረፉ

ላሚን ዲያክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቀድሞ የዓለም አትሌቲክስ ኃላፊ ላሚን ዲያክ በ88 ዓመታቸው ሴኔጋል ውስጥ ማረፋቸው ተሰማ።

ባለፈው ዓመት በሙስና ወንጀል ተከሰው የነበሩት ዲያክ ከአውሮፓውያኑ 1999 እስከ 2015 የዓለም አትሌቲክስ (የቀድሞው የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር-አይኤኤፍ) ፕሬዝዳንት ነበሩ።

በአውሮፓውያኑ 2020 ከሩሲያ አበረታች መድኃኒት ቅሌት ጋር ተያይዞ በሙስና እና በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።

የፈረንሳይ ፍርድ ቤት በአራት ዓመት እስራት እንዲቀጡ የበየነባቸው ሲሆን ሁለት ዓመቱ ተቀንሶላቸዋል።

ነገር ግን ሳይታሰሩ ወደ ሴኔጋል ተመልሰው እንዲሄዱ ተፈቅዶላቸው በቁም እስረኛነት ቆይተዋል። በኋላም በዋስ ተለቀዋል።

ልጃቸው ፓፓ ማሳታ ዲያክ "በተፈጥሯዊ ምክንያት ቤት ውስጥ ህይወቱ አልፏል" በማለት ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።

የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው በዛሬው ዕለት እንደሚፈጸም ተነግሯል።

ቀደም ሲል ዲያክ ጠበቆች በጤና እጦት ላይ እንዳሉ እና ከታሰሩ እንደሚሞቱ ተናግረው ነበር።

የቀድሞው ኃላፊ ጥፋተኛ ቢባሉም በሴኔጋል ድጋፍ አላቸው።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ዲያክ ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ ያስቻለውን 565 ሺህ ዶላር ዋስትና የከፈሉት ጃራፍ የተባለው የሴኔጋሉ እግር ኳስ ክለብ ባለቤት ቼክ ሴክ ናቸው።

ሴክ የቀድሞ የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ሲሆኑ አሁን በንግድ ሥራ ይተዳደራሉ።

"ጥሩ ሰውና ታላቅ መሪ ነበር። ወደ አገሩ እንዲመለስ እንፈልጋለን። 565 ሺህ ዶላር ለመሰብሰብ አንድ ወር ፈጅቶብናል" ሲሉ ከዲያክ ህልፈት በኋላ ተናግረዋል።

"ህይወቱ ሌላ ቦታ እንዲያልፍ አስበን አለማወቃችን በጣም አስፈላጊ ነበር።"

"ተወዳጅ የአገሩ ልጅ፣ ሁለንተናዊ አስደናቂ ዜጋ" ሲሉ ሴክ ቀደም ሲል ዲያክን ገልጸዋቸው ነበር።