የእስራኤሏ ቴልአቪቭ በዓለም ላይ በጣም ውድ ከተማ ተብላ ተሰየመች

ቴልአቪቭ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የእስራኤሏ ከተማ ቴልአቪቭ በዓለም ካሉ ውድ ከተሞች የአንደኛነቱን ሰፍራ ያዘች።

እየጨመረ ያለው ግሽበትና የአቅርቦት ሰንሰለት ችግር በዓለም አቀፍ ደረጃ ንረትን ከፍ ባደረገው ወቅትም ነው ቴልአቪቭ ለሰው ልጅ መኖሪያነት ውድ ከሆኑ ከተሞች የቁንጮነቱን ስፍራ የያዘችው።

የእስራኤሏ ከተማ በአንደኛነት ስፍራ ስትቀመጥ የመጀመሪያ ሲሆን ፓሪስና ሲንጋፖር ተከታታዩን ስፍራ እንደያዙ ኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒት ያደረገው ጥናት ይፋ አድርጓል ።

በዚሁ ተቋም መረጃ መሰረት ቴልአቪቭ ባለፈው አመት አምስተኛ ስፍራ ላይ ነበረች።

በጦርነት የምትታመሰው የሶሪያ መዲና ደማስቆ በዓለም ላይ በጣም ርካሹን ስፍራ በመያዝ ደረጃዋን አስጠብቃለች።

የዳሰሳ ጥናቱ በ173 ከተሞች ለሸቀጦች እና አገልግሎቶች የሚውለውን ወጪ በአሜሪካ መገበያያ ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነ አወዳድሯል።

ተቋሙ በአውሮፓውያኑ ነሐሴና መስከረም ባሉ ወራት የሰበሰበው መረጃ እንደሚያሳየው በአገራቱ ውስጥ የምንዛሬ ዋጋ በአማካይ በ 3.5 በመቶ የጨመረ ሲሆን ይህም ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የተመዘገበ ፈጣን የዋጋ ግሽበት አድርጎታል።

የትራንስፖርት አገልግሎት ከፍተኛ የዋጋ ጭማሬ የታየበት ዘርፍ ሲሆን ጥናት በተካሄደባቸው ከተሞች የአንድ ሊትር ቤንዚን ዋጋ በአማካይ 21 በመቶ ጨምሯል።

በተቋሙ የዓለም የኑሮ ውድነት ደረጃ ላይ አንደኛ የሆነችው ቴል አቪቭ በዋነኛነት የእስራኤል መገበያያ ገንዘብ ሸከል ከዶላር ጋር ሲነፃፃር ማሽቆልቆል አሳይቷል።

የአገር ውስጥ 10 በመቶ የሚሆነው የሸቀጦች ዋጋም በከፍተኛ ሁኔታ መናር ያሳየ ሲሆን ይህም በተለይ በምግቦች ላይ ታይቷል።

ጥናቱ እንደሚያመለክተው ቴል አቪቭ በአልኮል እና ትራንስፖርት ዋጋ ከአለም ሁለተኛ ውድ፣ ለግል እንክብካቤ እቃዎች አምስተኛ እናም በመዝናኛ ዘርፉ ስድስተኛ ውድ ከተማ ሆና ተቀምጣለች።

የቴል አቪቭ ከንቲባ ሮን ሁልዳይ ከሃሬትዝ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በተቋሙ ስሌት ውስጥ ያልካተተው የቤቶች ዋጋ መናር ከተማዋ ወደማትቋቋመው ደረጃ ላይ እያደረሳት እንደሆነም አስጠንቅቀዋል።

"አገሪቱ በሙሉ በጣም ውድ እየሆነች እንደመጣች ሁሉ ቴል አቪቭ በጣም ውድ ሆናለች" ብለዋል።

"በእስራኤል ውስጥ መሰረታዊው ችግር ሌላ አማራጭ ሁሉን ያሟላና ማእከል የሆነ ከተማ የለም። በአሜሪካ ኒውዮርክ፣ ቺካጎ፣ ማያሚ እና የመሳሰሉት አሉ። በብሪታንያ ውስጥ ታላቋ ለንደን፣ ማንቸስተር እና ሊቨርፑል አሉ። የኑሮ ውድነቱ በጣም ከባድ ከሆነ አማራጭ ወደሆኑት ሌሎች ከተሞች መሄድ ይችላሉ" ብለዋል።

የዓለም ውድ ከተሞች በደረጃ

  • ቴልአቪቭ
  • ፓሪስ
  • ሲንጋፖር
  • ዙሪክ
  • ሆንግ ኮንግ

የዓለም ርካሽ ከተሞች

169 አልማቲ

170 ቱኒስ

171 ታሽከንት

172 ትሪፖሊ

173 ደማስቆ