የዓለማችን ውድ እና ርካሽ ከተሞች ይፋ ሆኑ

ፓሪስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፓሪስ፣ ሆንግ ኮንግና ሴንጋፑር የምድራችን እጅግ ለኑሮ ውድ የሆኑ ከተሞች በመሆን በአንድነት የቀዳሚነቱን ቦታ ያዙ።

በሰላሳ ዓመታት ውስጥ ሦስት ከተሞች በአንድ ላይ ተመሳሳይ የውድነት ደረጃ ላይ ሲገኙ ይህ የመጀመሪያው እንደሆነም ተነግሯል።

የኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒት በሚያደረገው ጥናት መሰረት በየዓመቱ በዓለም ላይ የኑሮ ውድነት የሚስተዋልባቸውንና በአንጻሩ ደግሞ ርካሽ የሆኑ ከተሞችን በጥናት ላይ ተመስርቶ ዝርዝራቸውን ያወጣል።

የዚህ ዓመቱ ጥናት በ133 የዓለማችን ከተሞች ላይ የተደረገ ሲሆን መሰረታዊ የሚባሉ የኑሮ ጥያቄዎችን መነሻ አድርጎ ነው የተከናወነው።

ለምሳሌ የዳቦ ዋጋ ምን ያክል ያለመዋዠቅ ይቀጥላል? ሰዎች የውበት ሳሎን ገብተው ምን ያክል ይከፍላሉ? የሚሉ ሁኔታዎችን ታሳቢ አድርጓል።

በዚህም መሰረት የፈረንሳይዋ መዲና ፓሪስ ከሲንጋፖርና ሆነግ ኮንግ ጋር የዓለማችን ውድ ከተማ ሆነዋል። ፓሪስ ባለፈው ዓመት ሁለተኛ ደረጃ ላይ የነበረች ሲሆን ከአውሮፓ ህብረት ቀጠና ውስጥ ብቸኛዋ የኑሮ ውድነት የተሰቀለባት ከተማ ያደርጋታል።

ለምሳሌ በፓሪስ አማካዩ የሴቶች የውበት ሳሎን ክፍያ 119.04 ዶላር ነው። ተመሳሳይ አገልግሎትን ግን ዙሪክ ውስጥ በ73.97 ዶላርና የጃፓኗ ኦሳካ ከተማ ውስጥ ደግሞ በ53.46 ዶላር ማግኘት ይቻላል።

በአጠቃላይ የአለማችን ውድ 10 ከተሞች የሚከተሉት ናቸው ብሏቸዋል።

1. ሲንጋፖር (ሲንጋፖር)

1. ፓሪስ (ፈረንሳይ)

1. ሆንግ ኮንግ (ቻይና)

4. ዙሪክ (ስዊዘርላንድ)

5. ጀኔቫ (ሰዊዘርላንድ)

5. ኦሳካ (ጃፓን)

7. ሴዑል (ደቡብ ኮሪያ)

7. ኮፐንሃግን (ዴንማርክ)

7. ኒው ዮርክ (አሜሪካ)

10. ቴል አቪቭ (እስራኤል)

10. ሎስ አንጀለስ (አሜሪካ)

ተቋሙ በሌላ በኩልም ዓለም ላይ በትንሽ ገንዘብ መኖር የሚቻልባቸው ርካሽ ከተሞች የትኞቹ ናቸው የሚለውንም አጥንቷል። የሚገርመው ነገር ግን በዚህኛው ዝርዝር ውስጥ የሚገኙት አብዛኛዎቹ ከተሞች በፖለቲካ እና በምጣኔ ሃብት ኪሳራ የደረሰባቸው ሀገራት ከተሞች ሲሆኑ ህንድ ሦስት ከተሞችን በማስመዝገብ ቀዳሚ ነች። እነዚህም ከተሞች

1. ካራካስ (ቬንዝዌላ)

2. ደማሰቆ (ሶሪያ)

3. ታሽኬንት (ኡዝበኪስታን)

4. አልማቲ (ካዛኪስታን)

5. ባንጋሎር (ህንድ)

6. ካራቺ (ፓኪስታን)

6. ሌጎስ (ናይጀሪያ)

7. ቦኖስ አይረስ (አርጀንቲና)

7. ቺናይ (ህንድ)

8. ኒው ደልሂ (ህንድ)