ሆንዱራስ የመጀመሪያዋን ሴት ፕሬዚዳንት ልትሾም ነው

ዢዮማራ ካስትሮ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ከዩናይትድ ኪንግደም ዘውዳዊ ሥርዓት ወጥታ የራሷን ሪፐብሊክ የመሰረተችው ሆንዱራስ የመጀመሪያዋን ሴት ፕሬዚዳንት ልትሾም ነው።

ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሾሙት ዢዮማራ ካስትሮ ናቸው።

የግራ ክንፍ ሊብሬ ፓርቲ እጩ የሆኑት ዢዮማራ ከተቀናቃኛቸው ገዢ ፖርቲ 20 በመቶ ነጥብ ቀድመው ይመራሉ።

የግለሰቧ ድል በቅሌት እና በሙስና ውንጀላ ሲታመስ የቆየው የቀኝ ክንፍ ብሄራዊ ፓርቲ የ12 ዓመት የስልጣንን ዘመን ያከትማል።

ዢዮማሮ ካስትሮ ከፋፋይ የሆኑትን የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ሁዋን ኦርላንዶ ሄርንንዴዝን ይተካሉ።

የፕሬዚዳንቱ ወንድም አንቶኒዮ በአደንዛዥ ዕፅ በማዘዋወር ወንጀል ከታሰረ በኋላ ፕሬዚዳንቱ ከአደንዛዥ ዕፅ ንግድ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ይወቀሳሉ።

እጩ ፕሬዚዳንቷ ሆንዱራስን ከ አደንዛዥ ዕፅ አምባገንነት እና ሙስና አዘቅት ለማውጣት ቃል ገብተዋል።

ባለቤታቸው ማኑኤል ዘላያ ከአውሮፓውያኑ 2006 እስከ 2009 ድረስ በመፈንቅለ መንግሥት ከስልጣን እስከተወረዱበት ጊዜ ድረስ ሀገሪቱን መርተዋል።

ባለቤታቸው ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ በነበሩት አመታት ሁለት ጊዜ ለምርጫ ተወዳድረዋል።

ድምፅ አሁንም እየተቆጠረ ሲሆን የምርጫ ቦርዱ አሸናፊውን በይፋ ማሳወቅ አለበት። ሆኖም በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ እለት የገዥው ፓርቲ ሽንፈት እንዳጋጠመው ተነግሯል።

ዋና ተቀናቃኛዋ ናስሪ አስፉራ ዢዮማራ ካስትሮን እና ቤተሰቧን እንደጎበኙ በአገር ውስጥ የቴሌቪዥን ስርጭት ላይ ተናግረዋል።

"አሸናፊ በመሆንዎ እና በእጩ ፕሬዚዳንትነትዎ በይፋ እንኳን ደስ ያለዎት ማለት እፈልጋለሁ" ያሉት አስፉራ አክለውም "አስተዳደራቸው ለሁላችንም የሆንዱራስ ዜጎች የሚቻለውን እንዲያደርግ አምላክ መንዱን እንዲያሳያቸውእመኛለሁ።" ብለዋል

የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ትልቅ ለውጥ እንደሚመጣ ቃል ገብተዋል።

በወንጀል፣ አደንዛዥ ዕፅ ዝውውር እና ወደ አሜሪካ መጠነ ሰፊ ፍልሰት ባሉ ችግሮች እየታመሰች ያለችን ሃገርን ነው የሚወርሱት።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ለእጩ ፕሬዚዳንቷ የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት የላኩ ሲሆን መንግሥታቸውም ከእርሳቸው ጋር ለመስራት በጉጉት እየጠበቁ ነው ብለዋል።