የመንግሥታቱ ድርጅት በኢትዮጵያ ለሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት 40 ሚሊዮን ዶላር መደበ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ ለአስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት የሚውል 40 ሚሊዮን ዶላር መመደቡን አስታወቀ።
የተባበሩት መንግሥታት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ማስተባባሪያ ጽ/ቤት (ኦቻ) ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ በኢትዮጵያ ሕይወት አድን የሰብዓዊ እርዳታዎችን ለማከናወን እና ንጹሃን ዜጎችን ለመጠበቅ ከማዕከላዊ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ፈንድ 25 ሚሊዮን ዶላር መድቧል።
ከዚህ የሰብዓዊ እርዳታ ፈንድ በተጨማሪ 15 ሚሊዮን ዶላር የቀረበ ሲሆን በዚህም በጠቅላላው በኢትዮጵያ ለሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት 40 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚሆን ተገልጿል።
በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ እንዲጠብቁ እንዳስገደዳቸው የመንግሥታቱ ድርጅት አስታውቆ አሃዙም 7.1 ሚሊዮን መሆኑን አስታውቋል።
ተመድ ለሰብዓዊ እርዳታ የ40 ሚሊዮን ዶላር መመደቡን ይፋ ባደረገበት መግለጫ፤ ሰብዓዊ ቀውስ እየተስፋፋ በሄደበት በሰሜን ኢትዮጵያ፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መራር ህይወትን እየገፉ ነው ብሏል።
በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገው የነበሩት የኦቻ ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ፤ "በመላ አገሪቱ ፍላጎቶች እየጨመሩ ነው። ይህ ገንዘብ በመመደቡ የረድኤት ድርጅቶች ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች ጥበቃ እንዲያደርጉ እና እርዳታ እንዲያደርሱ ይረዳቸዋል" ብለዋል።
በመንግሥታቱ ድርጅት የተመደበው ገንዘብ በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች በግጭቱ ምክንያት ለተጎዱ ጥበቃ እና ሕይወት አድን ድጋፍ እንዲያደርጉ ይረዳል።
ተመድ ወጪ የሚያደርገው ገንዘብ በጦርነት ለችግር ተጋላጭ ከሆኑት በተጨማሪ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች በድርቅ የተጎዱትን ለመደገፍ እንደሚውል ተመልክቷል።
በእነዚህ ሁለት ክልሎች የተሰማሩ የረድኤት ድርጅቶች ንጹህ የመጠጥ ውሃ ለማቅረብ፣ ውሃ ወለድ በሽታን ማስወገድ እና የኮሌራ ወረርሽኝን ለመከላከል ይሰራሉ ብሏል ተመድ። ከዚህ በተጨማሪም፤ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አርብቶ አደሩ እንስሳቶቹን እንዲንከባከብ ይረዳሉ።
ማርቲን ግሪፊን ይፋ ያደረጉት የ25 ሚሊዮን ዶላር ፈንድ፤ በዚህ የፈረንጆቹ ዓመት 2021፤ ከማዕከላዊ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ፈንድ ለኢትዮጵያ ወጪ የተደረገውን የገንዘብ መጠንን ወደ 65 ሚሊዮን ዶላር ከፍ ያደርገዋል።
መቀመጫው ኢትዮጵያ ከሆነ የሰብዓዊ ፈንድ ወጪ የሆነ የገንዘብ መጠን ደግሞ ወደ 80 ሚሊዮን ዶላር እንደሚጠጋ ተመድ አስታውቋል።
ይሁን እንጂ በመላው ኢትዮጵያ ለሰብዓዊ አቅርቦት የሚደረገው ጥረት ለመደገፍ 1.3 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ እጥረት እንደገጠመው ተመድ አስታውቋል።
በትግራይ ክልል ደግሞ የሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ ተጨማሪ 350 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ የመንግሥታቱ ድርጅት ገልጿል።












