የበጋው ወቅት የበረታባቸው የቦረና ብሔረዊ ፓርክ የዱር እንስሳት በምን ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ?

በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን በተለያዩ ወረዳዎች የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ የዱር እንስሳት ጭምር ለጉዳት መጋለጣቸው ተገለፀ።
በዞኑ የተከሰተው ድርቅ በርካታ እንስሳትን ለሞት ሲዳርግ ሰዎች ደግሞ መጎዳታቸው በስፋት ሲዘገብ ቆይቷል።
የቦረና ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ አቶ ንጉሤ ዋታ ከፓርኩ እንስሳት መካከል በውሃ እና በግጦሽ ሳር ማጣት ምክንያት የተጎዱ እንስሳት መኖራቸውን ተናግረዋል።
በአካባቢው ባለፉት ወራት ምንም አይነት ዝናብ ባለመጣሉ የተከሰተው ድርቅ የዞኑ ነዋሪዎችን እና ከብቶቻቸውን ክፉኛ መጉዳቱ እንዲሁም ሰዎች ለረሃብ መጋለጣቸው ተገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ፣ የዱር እንስሳትም ለከፋ ችግር ተጋልጠዋል።
በአካባቢው በተደጋጋሚ የሚከሰተው ድርቅ፣ ለዞኑ ብቻ ሳይሆን ለቦረና ብሔራዊ ፓርክም ችግር እንደሆነ የተናገሩት ኃላፊው የቦረና ሕዝብ ራሱ ችግር ገጥሞት፣ የፓርኩን አራዊቶች ለመጠበቅ መስዋዕትነት እየከፈለ መሆኑን ገልፀዋል።
እየደረሰ ያለው ጉዳት
ረዘም ላለ ጊዜ በሚቆይ ድርቅ የቦረና ብሔራዊ ፓርክ እንስሳት ሲጎዱ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
በዘንድሮው ድርቅም የግጦሽ ሳር እና ውሃ ያጡ የቦረና ብሔራዊ ፓርክ የዱር እንስሳት ጉዳት ደርሶባቸዋል።
"ይህ ድርቅ ከጀመረ የሜዳ አህያ እና ከርከሮ ውሃ በማጣት ምክንያት በዋናነት እየተጎዱ ነው" ሲሉ የቦረና ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ አቶ ንጉሤ ዋታ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ከርከሮ የሚባለው እንስሳ ላይ ከፍተኛ የሆነ የክብደት መቀነስ ይታያል። እኛ ያላየነው የሞተም ሊኖር ይችላል። የሜዳ አህያ እስካሁን የሞተ የለም። ነገር ግን በድርቁ ምክንያት ተጋላጭ መሆናቸው የታወቀ ነው" ይላሉ አቶ ንጉሤ።
"በከፍተኛ ሁኔታ ክብደታቸው የቀነሰ ከርከሮዎች አጋጥመውናል" የሚሉት አቶ ንጉሤ "የመሞቱ ስለመኖራቸው ግን ማስረጃ የለንም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ፓርኩ ውስጥ በአፍሪካ ቀንድ በቁጥር ትንሽ የሆነ 'ግሬቨስ ዜብራ' የሚባል የሜዳ አህያ ዝርያ የሚገኝበት ቦታ መኖሩን ኃላፊው ጨምረው ተናግረዋል።
ይህ ስፍራ ሳሪቴ የሚባል ሲሆን፣ በአካባቢው በድርቁ ምክንያት ከውሃ በተጨማሪ የግጦሽ ሳርም መቀንሱም ይናገራሉ።
መስዋዕትነት እየከፈለ ያለው ሕዝብ
የቦረና ሕዝብ በዱር አራዊት ጥበቃ ላይ ጠንካራ ባህል እና ልምድ እንዳለው የሚናገሩት ኃላፊው፣ ሕዝቡ ለራሱ በድርቅ ቢጎዳም የዱር እንስሳቱን ለመጠበቅ መስዋዕትነት እየከፈለ መሆኑን ይናገራሉ።
ሕዝቡ ለከብቶቹ ከተለያዩ እርዳታ ድርጅቶች ያገኘውን ሳር ቀንሶ ለዱር እንስሳቱ ሲሰጥ እንዳዩ ኃላፊው ተናግረዋል።
ከሰሞኑም የቦረና ሰዎች ለእንስሳቱ ውሃ ሲያጠጡ የሚያሳይ ምስል የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ሲቀባበሉት ነበር።
በተለይም ሳሪቴ በሚባለው ቦታ፣ አቶ ጉራቻ ገልማ የሚባሉ ግለሰብ፣ ጉድጓድ ውስጥ የወደቀችን የሜዳ አህያ አውጥተው፣ አጥበው ወደ ፓርኩ እንድትመለስ ማድረጋቸው በሰፊው ሲገለጽ ነበር።
የቦረና ዞን ከኦሮሚያ ዞኖች ከፍተኛ የውሃ ችግር ከሚታይባቸው መካከል አንዱ ነው።
እንደ አቶ ንጉሤ ገለፃ ከሆነ የውሃ ችግር ለዓመታት ከሕዝቡ ሲነሳ የቆየ ቢሆንም፣ አሁንም ያልተፈታ ነው።
"የውሃ እጥረት ትልቁ ችግራችን እነደሆነ ስንገልጽ ቆይተናል። ይህ ደግሞ የሚፈታው እንደ አጠቃላይ የቦረና ዞን የውሃ ችግር ሲፈታ ብቻ ነው" ይላሉ የፓርኩ ኃላፊ አቶ ንጉሤ።
የዱር እንስሳቱ ስደት
የዱር እንስሳት ድርቅ በሚያጋጥምበት ወቅት ሳር እና ውሃ ፍለጋ ወደ ሌላ አካባቢ የሚሰደዱ ቢሆንም፣ በዚህ ወቅት ግን ዞኑን በሚያዋስነው የኬንያ ሰሜናዊ ክፍልም ተመሳሳይ ችግር መኖሩን ኃላፊው ተናግረዋል።
በዚህም የተነሳ የፓርኩ እንስሳት ወደ ኬንያ የመሰደዳቸው እድል አነስተኛ መሆኑን ይናገራለ።
ከቅርብ ቀናት ወዲህ በቦረና ዞን አንዳንድ አካባቢዎች አነስተኛ ዝናብ በመዝነቡ የውሃና የግጦሽ ችግሩ እንዲቃለል ተስፋ የሚሰጥ ነገር መሆኑንም አክለዋል።
ስለ ቦረና ብሔራዊ ፓርክ
ከዚህ በፊት ያቤሎ የዱር እንስሳት መጠለያ በመባል የሚታወቀው ስፍራ በ2005 ዓ.ም የቦረና ብሔራዊ ፓርክ በመባል እንደ አዲስ ተደራጅቷል።
ከ3741 ስኩዌር ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍነው ይህ ፓርክ የተለያዩ አእዋፋት እና የአጥቢ እንስሳት ዝርያዎችን በውስጡ ይዟል። በውስጡ ካሉ 286 የአእዋፋት ዝርያዎች መካከል አራቱ በቦረና ዞን ብቻ የሚገኙ ናቸው።
አንበሳ፣ ቀጭኔ፣ ዝሆን፣ እና የሜዳ አህያ (ሁለት ዓይነት) ጨምሮ 46 የአጥቢ እንስሳት በፓርኩ ይገኛሉ።

















