የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንስሳትን በሕገወጥ መንገድ እያጓጓዘ ነው መባሉን አስተባበለ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, ETHIOPIAN

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሕይወት ያሉ የዱር እንስሳትን የማጓጉዘው በከፍተኛ ጥንቃቄ ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ፣ ብሔራዊ ሕጎችን እና የውስጥ አሰራርን በመከተል ነው አለ።

አየር መንገዱ ይህን ያለው ተቋሙ ለንግድ የሚውሉ የዱር እንስሳትን አስከፊ በሆነ አያያዝ ከምዕራብ አፍሪካ ወደተለያዩ መዳረሻዎች ያጓጉዛል የሚል አንድ ጥናታዊ ሪፖርት ይፋ ከሆነ በኋላ ነው።

ዎርልድ አኒማል ፕሮቴክሽን የተሰኘ ድርጅት ይፋ ባደረገው የጥናት ሪፖርት ላይ አየር መንገዱ ከዚህ ተግባሩ ተቆጥቦ ለዱር እንስሳት ተስማሚ ኩባንያ መሆን አለበት ሲል ጥሪውን አቅርቧል።

አየር መንደጉ "በበኩሉ እንደ ዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር አባልነቴ በሕይወት ያሉ እንስሳትን የማጓጓጉዘው ሰብዓዊ እና ሕጋዊ በሆነ መልኩ ነው" ሲል የቀረበበትን ክስ ውድቅ አድርጓል።

ሪፖርቱ ምን ይላል?

መነሻቸው መካከለኛው እና ምዕራብ አፍሪካ የሆኑ የዱር እንስሳት በአየር መንገዶች ወደ ተለያዩ መዳረሻዎች ተጓጉዘው ለቤት እንስሳትነት ለንግድ እየዋሉ ነው ይላል።

ሪፖርቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አጥቢ እና ተሳቢ እንስሳት በኢትዮጵያ አየር መንገድ መጓጓዛቸውን አስፍሯል።

በዱር እንስሳት ንግድ ውስጥ ከምዕራብ አፍሪካ አገራት የዱር እንስሳትን በስፋት በማጓጓዝ ጥቅም ላይ የዋለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው የሚለው ዎርልድ አኒማል ፕሮቴክሽን፤ እንስሳቱ የሚያዙበት እና የሚጓጓዙበት መንገድ አስከፊ ከመሆኑም በተጨማሪ በህይወት ያሉ እንስሳትን በማጓጓዝ ወረርሽኝ ሊከሰት ይችላል ይላል።

ብዙ ጊዜ በአየር መንገዱ ከተጓጓዙ የዱር እንስሳት መካከል የእንሽላሊት፣ የኤሊ፣ የእባብ እና የጊንጥ ዝርያዎች ተጠቃሽ ናቸው ይላል የጥናት ሪፖርቱ።

የጦጣ ዝርያ ያላት እንስሳ

የፎቶው ባለመብት, World Animal Protection

የምስሉ መግለጫ, የጦጣ ዝርያ ያላት እንስሳ

አብዛኛው የተጓጓዙት የዱር እንስሳት ለመጥፋት የተቃረቡ፣ በቂ መረጃ ያልተሰበሰበባቸው አልያም ቁጥራቸው እየተመናመነ ያሉ ናቸው ብሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዱር እንስሳቱን ካጓጓዘባቸው አገራት መካከል ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ታይላንድ፣ ሆንግ ኮንግ፣ ኦማን፣ ማሌዢያ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን እና ዩናይትድ ኪንግደም ይገኙበታል።

አየር መንገዱ ለቤት እንስሳትነት፣ ለመዝናኛ፣ ባህላዊ መድሃኒት እና ለፋሽን ተብለው ለንግድ የሚቀርቡ የዱር እንስሳትን ማጓጓዙን እንዲያቆም 'ዎርልድ አኒማል ፕሮቴክሽን' ጠይቋል።

አየር መንገዱ የዱር እንስሳቶችን ሲያጓጉዝ የዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር (አይኤቲኤ) በሕይወት ያሉ እንስሳት መመሪያን ባልጠበቀ መልኩ መሆኑ አሳሳቢ ነው ብሏል።

በሪፖርቱ ውስጥ የኤሊ ዝርያ ያላቸው የዱር እንስሳት አነስተኛ መጠን ባለው መያዣ ውስጥ ታሽገው ስለሚጓጓዙ በጉዞ ወቅት ስቃይ እንደሚገጥማቸው በሪፖርቱ ተካቷል።

የአየር መንገዱ ምላሽ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለዚህ ሪፖርት ምላሽ በሰጠበት መግለጫ ላይ የትኛውንም አይነት የዱር እንስሳት የማጓጉዘው ዓለም አቀፍ ሕግጋትን በተከተል መልኩ ነው በማለት እንስሳቱ የተጓጓዙት ሕጋዊ መንገድን ባልተከተለ ነው መባሉን አጥብቆ ተቃውሟል።

አየር መንገዱ የዱር እንስሳትን ከማጓጓዙ በፊት ላኪው እና ተቀባዩ ሕጋዊ ፍቃድ እንዳላቸው እንዲሁም አስፈላጊ የጤና ቅድመ ሁኔታዎች መሟላታቸውን አረጋግጣለሁ ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም አየር መንገዱ የመጥፋት አደጋ የተደቀነባቸው የዱር እንስሳትን ያለ ምንም ክፍያ እንክብካቤ ወደሚያገኙበት ስፍራ በማጓጓዝ ለዱር እንስሳት ጥበቃ ኃላፊነቱን እተወጣ መሆኑን አመልክቷል።

ጥናቱ እንዴት ተካሄደ?

ለጥናቱ ግብዓት የሆኑት መረጃዎች የተሰበሰቡት ለሽያጭ የሚቀርቡ የዱር እንስሳት ዋነኛ መነሻ በሆነችው ቶጎ ከሚገኙ ከማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ነው።

ለሪፖርቱ በዋናነት መረጃዎች የተሰበሰቡት የዱር እንስሳት ሽያጭን ከሚያስተዋውቁ እና የዱር እንስሳት እንቅስቃሴን ከሚያመቻቹ ሁለት የፌስቡክ ገጾች ላይ ነው።

ከእአአ 2016 እስከ 2020 ድረስ በፌስቡክ ገጾቹ የተለጠፉ ጽሑፎች፣ ምስሎች እና ተንቀሳቃሽ ምስሎች ለንግድ የቀረቡ የዱር እንስሳት አይነቶች፣ ብዛት፣ አያያዝ፣ የሚጓጓዙበት ሁኔታ እና በየት በኩል ወደ መዳረሻቸው እንደተጓዙ አመላክቷል ይላል የጥናት ሪፖርቱ።

ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ከተጋሩት ይዘቶች በመነሳት ምን ያህል የዱር እንስሳት በኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደተጓጓዙ በትክክል ማወቀ ባይቻልም፤ የተሰበሰቡ መረጃዎች አየር መንገዱ በተለያዩ ጊዜያት ተሳቢ፣ አጥቢ እንስሳትን ስለማጓጓዙ አመልክቷል ይላል።

አየር መንደጉ በበኩሉ ከማሕበራዊ ሚዲያዎች የሚሰበሰቡ መረጃዎችን ይዞ ከመደምደሚያ መድረስ አግባብ አይደለም ብሏል። ከዚህ በተጨማሪም ሕጋዊ የዱር እንስሳት ንግድን የሚቃወሙ ድርጅቶች ትኩረታቸውን የዱር እንስሳት ንግድን ሕጋዊ ባደረጉ አገራት ፖሊስ እና ሕግ ላይ ማድረግ አለባቸው ብሏል።

በመጨረሻም አየር መንገዱ ሕግ እና የውስጥ አሰራርን ተከትሎ ሰብዓዊነት በተሞላበት መልኩ ለደንበኞቹ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንደሚቀጥል አስታውቋል።

line

ይህንን ሪፖርት ያወጣው ድርጅት ባለፉት 55 ዓመታት እንስሳትን ከስቃይ ስጠብቅ ቆይቻለሁ ይላል። በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ እንስሳትን ደህንነት ለማረጋገጥ በ14 አገራት ቢሮ ከፍቼ እሰራለሁ ይላል ዎርልድ አኒማል ፕሮቴክሽን።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በፍጥነት እያደጉ ካሉ አየር መንገዶች መካከል አንዱ ነው። የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ተከትሎ በርካታ አየር መንገዶች ለኪሳራ ሲዳረጉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን ትርፋማነቱን ስለማስቀጠሉ ብዙ ተብሎለታል።

በቅርቡም አየር መንገዱ ባጓጓዘው የመንገደኞች ብዛት ከዓለም ምርጥ 200 አየር መንገዶች መካከል 20ኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን ዓለም አቀፍ የትራንስፖርት ማኅበር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህንን ደረጃ ያገኘው ከ16 ሚሊዮን በላይ መንገደኞች በማጓጓዝ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአምስት አህጉራት በመቶዎች ወደሚቆጠሩ መዳረሻዎች የሚጓዝ ሲሆን 130 አውሮፕላኖች አሉት። እነዚህም እጅግ ዘመናዊ የሚባሉትን 16 ኤይርባስ ኤ350-900 እና 19- ቦይንግ ቢ787-8 ይጨምራሉ።