በኢትዮጵያ የኤሊ አደን ለምን አየተበራከተ መጣ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ኤሊ 'ብዙ ገንዘብ ታስገኛለች' በማለት በርካቶች ወደ ኤሊ አደን እየገቡ መሆኑ እየተነገረ ነው።
እኛም ባደረግነው ማጣራት በበርካታ የሃገሪቱ ክፍሎች ኤሊ በርካታ ሚሊዮን ብሮችን ታስገኛለች በማለት አድኖ በአንድ ቦታ ማከማቸት እና የኤሊ ሕገ-ወጥ ዝውውር እየተደረገ መሆኑን አረጋግጠናል።
አዲስ አበባን ጨምሮ፣ ሻሸመኔ፣ ሐረርጌ፣ ምዕራብ ኦሮሚያ እና አፋር ክልል ይህን መሰል ተግባር በስፋት እየተፈጸመ እንደሆነ መረዳት ተችሏል።
በኢትዮጵያ ኤሊን ጨምሮ የዱር እንስሳትን ማደንም ሆነ ማዘዋወር በሕግ የተከለከለ ነው።
የዱር እንሰሳት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 541/1999 የሚንስትር መስሪያ ቤት ወይም የክልል የመንግሥት አካል እስካልሆነ ድረስ ማንኛው አካል የአደን ፍቃድ ከሌለው የዱር አራዊቶችን ማደን አይችልም ሲል ያትታል።
በዚህ መሰል የኤሊ አደን ውስጥ ተሳታፊ የሆኑት ግለሰቦች ተግባራቸው ሕገ-ወጥ መሆኑን ስለሚረዱ ማነነታቸውን መግለጽ አይሹም።
የዱር እንስሳዋን በተመለከተ በርካታ የተሳሳቱ መረጃዎች ይሰራጫሉ። ገንዘብ እናገኛለን በሚል በተሳሳተ መረጃ ኤሊ የሚያድኑት ሰዎች ''እጅግ ተፈላጊ'' የምትባለዋን ኤሊ አድነው ካገኙ እስከ 200 ሚሊዮን ብር ድረስ ዋጋ ታወጣለች ብለው ያምናሉ።
''እጅግ ተፈላጊ'' የምትባለዋ ኤሊ የሚከተሉት ልዩ መለያዎች አሏት ተብሎ ይታመናል።
- እንደ ማግኔት ብረቶችን የመሳብ አቅም
- ንጹህ ውሃ ጎን ብትቀመጥ፤ ውሃው ይደፈርሳል።
- ጭለማ ውስጥ አንገቷ አንጸባራቂ ብርሃን ያወጣል።
- በካሜራ ምስሏ ሊነሳ አይችልም የሚሉት ይገኙበታል።
በየኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃና ባለስልጣን የዱር እንስሳት ልማት እና አጠቃቀም ባለሙያ ወ/ሮ ዘላለም ''በኤሊ ውስጥ ሜርኩሪ ይገኛል በሚል ሐሰተኛ መረጃ በመሰራጨቱ ይህ መሰሉ ተግባር እየተከናወነ እንደሆነ ሰምተናል'' ይላሉ።
ወ/ሮ ዘላለም ጨምረውም በቅርቡ በአፋር ክልል አዋሽ ብሄራዊ ፓርክ ሰዎች ወደ ፓርኩ እየገቡ ኤሊዎችን እያደኑ እንደሆነ የሚያትት ደብዳቤ ለባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ እንደደረሰ ይናገራሉ።
ባለስልጣን መስሪያ በቱ ከፖሊስ ጋር በመሆን በፓርኩ ውስጥ እየተፈጸመ ያለውን ህገ-ወጥ የኤሊ አደን ለማስቆም ወደ ስፍራው እንደሚጓዝ ለማወቅ ተችሏል።
በኢትዮጵያ ኤሊን ለመሸጥ እና ለማዘዋወር ተመዝገበው ፍቃድ ያገኙ ድርጅቶች ሁለት ብቻ መሆናቸውን የሚያስታውሱት ወ/ሮ ዘላለም፤ ኤሊን ለማደን ፍቃድ ያላቸው ግለሰቦችም ቢሆኑ፤ ፍቃድ ከማግኘታቸው በፊት ተገቢውን ስልጠና ይወስዳሉ ይላሉ።
ወ/ሮ ዘላለም ኤሊዎች በቡድን እንደሚኖሩ በመጠቆም ከአንድ የኤሊ ቡድን ስንት ኤሊዎችን መውሰድ ይቻላል? እድሜያቸው ምን ያክል ነው? የሚሉና ሌሎች ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ፍቃድ ያላቸው ሰዎች ብቻ ኤሊዎችን ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ ማንቀሳቀስ ተፈቅዶላቸዋል ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Inpho
በዱር እንስሳዋ ኤሊ ላይ ይህ መሰሉ ተግባር ይፈጸም እንጂ ከዚህ በፊት በተሳሳተ መረጃ የተለያዩ ቁሶች ብዙ ገንዘብ ያስገኛሉ በሚል መሰል ተግባራት ሲፈጸሙ ይታያል።
ለምሳሌ የዶሮ ምልክት ያለበት በከሰለ የሚሰራ ካውያ፣ ብዙ ገንዘብ ያወጣል በሚል በርካቶች ካውያውን ፍለጋ ሲባክኑ ተስተውለዋል። በተጨማሪም የአንበሳ ምልክት ያለበት ብርሌ እና መመገቢያ ትሪ በውስጣቸው 'ሜርኩሪ' አላቸው በማለት ቁሶቹን ፍለጋ በርካቶች ጊዜ እና ገንዘባቸውን ማባከናቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
















