ለህገወጥ አዳኞች ፈተና የሆኑት ውሾች

የኬንያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሙያ ከውሻው ጋር

የፎቶው ባለመብት, WWF

ፈር ቀዳጅ የተባለለት አዲስ መንገድ የሰው ልጅ ታማኝ ጓደኛን የህገወጥ አዳኞች ከባድ ፈተና ለማድረግ የታሰበ ነው።

በባህርና በተለያዩ የሟጓጓዣ መንገዶች የሚዘዋወሩ የዝሆን ጥርስ፤ የአውራሪስ ቀንድ እና ሌሎች ነገሮችን የሰለጠኑት ውሾች አነፍንፈው ማግኘት ይችላሉ።

ይህ አዲስ የመከላከል ስርአት እየተሞከረ ያለው በአለማችን ብዙ ሀገወጥ የዱር እንስሳት ውጤቶች ይዘዋወሩበታል በሚባልለት የኬንያው ሞምባሳ ወደብ ነው።

በቅርቡ የተሰራ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው በዚሁ በሞመባሳ ወደብ ብቻ እ.አ.አ ከ2009 እስከ 2014 ባሉት ዓመታት ውስጥ ከአስራ ስምንት ሺ ኪሎ ግራም በላይ ህገ-ወጥ የዝሆን ጥርስ መዘዋሩን ያሳያል።

ይህን ያህል ቁጥር ያለው የዝሆን ጥርስ ለማግኘት ከ2400 በላይ ዝሆኖች መገደላቸውንና በፍተሻ ወቅት ያልተያዘው ሲደመር ደግሞ ቁጥሩ እጅጉን ከፍ ሊል እንደሚችል ጥናቱ ያሳያል።

የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሙያው ድሪው ማክቬይ ግን ከዚህ በኋላ ቁጥሩ ሊቀንስ እንደሚችል ተስፈኛ ነው።

''ይህ መንገድ ብዙ ነገር ይቀይራል፤ በህገወጥ መንገድ ወደ ተለያዩ ሃገራት በተለይ ወደ እስያ ገበያዎች የሚዘዋወሩ የዝሆን ጥርስና ለሎች የዱር እንስሳት የሰውነት ክፍሎች በቀላሉ ለመቆጣጠር ይረዳል'' ብሏል።

''ውሻዎች ያላቸው የላቀ የማሽተት ችሎታ ላይ ተገቢው ስልጠና ሲጨመርበት ከአስራ ሁለት ሜትር በላይ ከፍታ ያለው የእቃ መጫኛ ውስጥ የተደበቁ ነገሮችን አነፍንፈው ማግኘት ይችላሉ።''

ህገወጥ አዘዋዋሪዎቹ እጅግ የተወሳሰቡና በየጊዜው የሚቀያየሩ የማዘዋወሪያ መንገዶችን ስለሚጠቀሙ፤ የውሾቹ ወደ ስራ መግባት በከፍተኛ ሁኔታ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ድሪው ማክቬይ ያስባል።

የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሙያው ውሻዎችን ሲያሰለጥን

የፎቶው ባለመብት, WWF

ፍተሻ በሚደረግባቸው ጣቢያዎች ላይ ከእቃ መጫኛዎቹ ውስጥ የአየር ናሙና ይወሰድና ውሻዎቹ እንዲያሸቱት ይደረጋል። ተፈጥሮአዊ የማነፍነፍ ችሎታቸውንና ያገኙትን ስልጠና ተጠቅመው ውሻዎቹ ምልክት ይሰጣሉ።

አሁን በሙከራ ላይ ያለው አዲሱ የቁጥጥር መንገድ በሞምባሳ ወደብ የሚያልፉ እስከ 20 ሺ የመርከብ ላይ እቃ መጫኛዎችን በአንድ ቀን መፈተሽ አስችሏል።

ከዚህ በፊት ግን የቁጥጥር ባለሙያዎቹ አንድ በአንድ እቃ መጫኛዎቹ ውስጥ በመግባት ነበር ፍተሻ የሚያካሂዱት።

እስካሁን በተደረጉ ፍተሻዎችም ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ህገወጥ የዱር እንስሳት አካላትን ጭነው የነበሩ 26 እቃ መጫኛዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል። የተገኘው መረጃም በአለማቀፍ አዘዋዋሪዎች በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሰራውን ወንጀል ባህሪ ለመረዳት እንዳስቻላቸው የሃገሪቱ ባለስልጣናት ገልጸዋል።

አለማቀፉ የዱር እንስሳት ጥበቃ ድርጅት እንደሚለው በአሁኑ ሰአት 25 ሺ የሚሆኑ ጥቁርና ነጭ አውራሪሶች የቀሩ ሲሆን፤ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ብቻ ከአንድ ሺ በላይ የሚሆኑት ባለፈው አመት በህገወት አዳኞች ተገድለዋል።

በየቀኑ 55 የአፍሪካ ዝሆኖች እንደሚገደሉም ድርጅቱ ገልጿል።