"ሳር ብቻ ይዘን ነው ወደ ወንዝ የምንወርደው፤ ፖለቲካው ለሌላ ጊዜ ይቆየን" አባ ገዳ ጎበና ሆላ

በአዲስ አበባ እና በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዴ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል የቱለማ አባገዳ የእሬቻ አከባበር አስተባባሪ አባ ገዳ ጎበና ሆላ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናገሩ።
አባ ገዳ ጎበና ሆላ አክለውም በዓሉን በሰላም ለማክበር እንዲቻል የተለያዩ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን በመግለጽ "የዘንድሮውን የኢሬቻ በዓልን የምናከብረው በሁለት ትልልቅ ችግሮች ውስጥ እያለን ነው" በማለት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እና በአገሪቱ ያለው የሰላም እጦትን ጠቅሰዋል።
በዓሉን ለማክበር ወደ አዲስ አበባ እንዲሁም ቢሾፍቱ የሚመጡ ተሳታፊዎች ራሳቸውን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመጠበቅ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሁሉ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
አባ ገዳ ጎበና አክለውም በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ የሰላምና ፀጥታ ጉዳይን በተመለከተም ኅብረተሰቡ የራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።
የዘንድሮው ኢሬቻ በዓል በአዲስ አበባ ቅዳሜ መስከረም 22/2014 ዓ.ም የሚከበር ሲሆን በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዴ ደግሞ እሁድ መስከረም 23/2014 ይከበራል።
በሁለቱም ከተሞች የኢሬቻ በዓልን ለማክበር በርካታ ቁጥር ያላቸው ተሳታፊዎች ይመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አባ ገዳ ጎበና ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኮሮናቫይረስ ጥንቃቄን በተመለከተ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከኦሮሚያ እና ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮዎች ጋር በመተባበር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሰራታቸውን አባ ገዳው ጨምረው ገልፀዋል።
ሰላም እና ፀጥታን በተመለከተ ደግሞ የፀጥታ እና ደኅንነት አካላት በዓሉ በሰላም እንዲከበር በቅንጅት ለመስራት በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን አመልከተዋል።
አባ ገዳ ጎበና ሆላ "ፀጥታን የሚያስከብር ሕዝቡ ራሱ ነው፤ ጤናውን የሚጠብቅም ሕዝቡ ራሱ ነው። ይሁን እንጂ መንግሥት ኃላፊነት ስላለበት የበዓሉ ተሳታፊዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ዝግጅት አድርጓል። ከዚህም በተጨማሪም ወጣቶች፣ ኢሬቻ በዓል ላይ ለመሳተፍ የሚመጡ ሰዎችን ደኅነንት ለመጠበቅ ዝግጅት አድርገዋል" ብለዋል።
ለበዓሉ የሚመጡ ታዳሚዎች ወደ መልካው ሲሄዱ የኢሬቻ በዓል ትውፊቶችን ከሚገልፁ ነገሮች ውጪ ሌላ ነገር ይዘው እንዳይሄዱም መልዕክት አስተላለፈዋል።
"ኦሮሞ የራሱ ትውፊት እና ባህል አለው፤ ወጣቶች፣ አዛውንቶች፣ አባገዳዎች፣ አደ ሲንቄዎች፣ ምን ምን ይዘው እንደሚወጡ ያውቁታል። ወደ ወንዙ የምንመጣው እርጥብ ሳር ብቻ ይዘን ነው" ብለዋል።
"ለሁለት ቀናት ብቻ የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል፣ ከፖለቲካ ነጻ በሆነ እና ባህሉንና ትውፊቱን በጠበቀ መንገድ ብቻ ማክበር አለብን" ሲሉም አክለዋል።
"ኢሬቻ ፖለቲካ መሆን የለበትም፤ እኛ የአባ ገዳ ባንዲራ እንኳ ይዘው እንዲመጡ አናስገድድም፤ ነገር ግን ይህንን ባንዲራ ይዛችሁ ኑ፤ ወይ ደግሞ ይህንን አትያዙ ማለት ይጨንቀናል፤ እንደዚያ ካልን ከፖለቲካ ጋር ይቀላቀላል። እንደዚህ እንዳይሆን እንደ ትውፊታችን እርጥብ ሳር ብቻ ይዘን እንምጣ" ብለዋል።
እንዲሁም "የኢሬቻን በዓል በሳር ብቻ አክብረን በሰላም ወደ መጣንበት የምንመለስበት እንጂ ለዚህ እና ለዚያ ባንዲራ ብለን የምናጋንንበት ነገር አይደለም" ብለዋል።
አባ ገዳ ሆላ በተጨማሪም "ይህ ሥርዓታችንን ያዳክማል። ኦሮሞ ሥርዓት አለው፤ የራሱን ሥርዓት ማሳመር አለበት። በአንድ ዓመት ውስጥ 365 ቀናት አሉ። እነዚህን ሁለት ቀናት በሰላም አክብረን ሌሎች ቀናትን ለፖለቲካ መጠቀም እንችላለን" ብለዋል።
የዘንድሮው ኢሬቻ በዓል ኦሮሞ የራሱ ባህል፣ የራሱ ትውፊት፣ የራሱ አገር እንዳለው የሚያሳይበት እንዲሆን እና በሰላም እንዲጠናቀቅ ሁሉም የኦሮሞ ማኅበረሰብ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት በማለት መልዕክት አስተላለፈዋል።












