የአማራ ክልል ዶክተር ይልቃል ከፋለን ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ መረጠ

ዶክተር ይልቃል ከፋለ

የፎቶው ባለመብት, Fana Broadcasting Corporate

ስድስተኛውን ብሔራዊ ምርጫ ተከትሎ የመስራች ጉባኤውን እያካሄደ የሚገኘው የአማራ ክልል ዶክተር ይልቃል ከፋለን የክልል ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ሾመ።

የአማራ ብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ዶክተር ይልቃል ከፋለን ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድርነት ዕጩ አድርጎ ካቀረበ በኋላም ነው በጉባኤው የተመረጡት።

በክልሉም ስድስተኛ መስራች ጉባኤ ዶክተር ይልቃል ከፋለ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በመሆን ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።

ዶክተር ጌታቸው ጀምበር የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ሲመረጡ ከዚህም በተጨማሪ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እንዲሁም አቶ አማረ ሰጤ ምክትል አፈ ጉባዔ ሆነው መሾማቸውንም የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ክልሉን በርዕሰ መስተዳድርነት በማገልገል ላይ ይገኙ የነበሩት አቶ አገኘሁ ተሻገር ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ መሾማቸው ይታወሳል።

በወቅቱ ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ለሌላ ኃላፊነት መታጨታቸውን ተከትሎ ለአማራ ክልል ምክር ቤት መልቀቂያ ማስገባታቸውን ተከትሎ ነበር አቶ አገኘሁ የተሾሙት።

ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በክልሉ ተፈፀመ በተባለው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የክልሉ ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶ/ር አምባቸው መኮንንና ሌሎች የአዴፓ አመራሮችና የፀጥታ አካላት ከተገደሉ አንድ ወር በኋላ አቶ ተመስገን ክልሉን እንዲመሩ መደረጋቸው ይታወሳል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ላቀ አያሌው ክልሉን በጊዜያዊነት ለጥቂት ጊዜ መርተው ነበር።

የአማራ ክልል ምክር ቤት በዛሬው ጉባኤ የክልሉ ካቢኔ አባላትን በመምረጥ ሹመት ሰጥቷል።