ዩ ቲዩብ የፀረ-ክትባት ሃሰተኛ መረጃዎችን ሊያስወግድ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዩቲዩብ ሁሉም ዕውቅና ያገኙ ክትባቶችን በተመለከተ የተሳሳተ መረጃን የሚያሰራጩ ማንኛውንም ይዘት ከድረ-ገጹ እንደሚያስወግድ አስታውቋል።
ፈቃድ ያገኙ ክትባቶች አደገኛ ናቸው፣ ኦቲዝም ካንሰር ወይም መካንነት ያስከትላል የሚሉና ተመሳሳይ ቪዲዮዎች ከዩቲዪብ ከሚወርዱት መካከል እንደሆነ ኩባንያው ገልጿል።
ይህ መመሪያ የፀረ-ክትባት ተፅዕኖ ፈጣሪዎች አካውንቶች መቋረጥንም ያጠቃልላል።
እንደ ዩ ቲዩብ ያሉ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በጣቢያዎቻቸው ላይ የሐሰት የጤና መረጃን ለመቃወም ብዙ ባለመሥራታቸው ተተችተዋል።
በሐምሌ ወር የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች ለበርካቶች እንዳይከተቡ የጥርጣሬ በር በመክፈት ዋነኛ ተጠያቂ ናቸው ያሉ ሲሆንም ይህንንም ለማስተካከል ኩባንያዎቹ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተማፅነዋል።
የጉግል ንብረት የሆነው ዩ ቲዩብ ስለ ኮቪድ-19 ክትባቶች የተሳሳተ መረጃን የሚያሰራጭ ይዘት ላይ እገዳን ተግባራዊ ካደረገበት ጊዜ ጀምሮ 130 ሺህ ቪዲዮዎች ከድረ-ገጹ ተወግደዋል ብሏል።
አዲሱ ፖሊስ እንደ ኩፍኝና ሄፓታይተስ ቢ ያሉ ከጸደቁ ረዥም አመታትን ያስቆጠሩ ክትባቶችንም ይሸፍናል።
"በአሁኑ ወቅት በአለም ጤና ድርጅትም ሆነ በጤና ባለስልጣናት ደህንነታቸው የተጠበቀ እና ውጤማነታቸው የተረጋገጡ የትኞቹን ክትባቶችን በተመለከተም የህክምና የተሳሳተ መረጃ ፖሊሲዎቻችን በማስፋት ሽፋን የምንሰጣቸው ይሆናል" በማለት ኩባንያው ባወጣው ፅሁፍ አስታውቋል።
ሆኖም ከክትባት ጋር የተዛመዱ የግል ምስክርነቶች ፣ ስለ ክትባት ፖሊሲዎች ይዘት ፣ ስለ አዲስ ክትባት ሙከራዎች እና ስለ ክትባት ስኬቶች ወይም ውድቀቶችን የሚያሳዩ ታሪካዊ ቪዲዮዎች በጣቢያው ላይ እንዲቆዩ ይፈቀድላቸዋል ብሏል ኩባንያው።
ከዚህ ቀደምም ፌስቡክ ክትባቶች ውጤታማ አይደሉም ወይም ኦቲዝም ያስከትላሉ የሚሉና የመሳሰሉ የተሳሰቱ መረጃዎች ላይ እገዳ ጥያለሁ ብሏል።
ነገር ግን ኩባንያው በስራ ላይ ለማዋል ፈታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውታል።
ትዊተርም እንዲሁ ስለ ክትባቶች የተሳሳተ መረጃን በተደጋጋሚ ያጋሩ ተጠቃሚዎች ከመድረክ እንደሚታገዱ አስታውቋል።












