የፈረንሳዩ ሚኒስትር የአሜሪካ እና የአውስትራሊያ የደህንነት ስምምነት 'ቅጥፈትን' አወገዙ

የፈረንሳዩ ሚኒስትር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ፈረንሳይ በአሜሪካና አውስትራሊያ የሚገኙ አምባሳደሮቿን ወደ ሀገር ቤት እንድትጠራ ምክንያት የሆነውን አዲስ የደህንነት ስምምነትን በተመለከተ ሀገራቱ ዋሽተዋል ሲሉ የፈረንሳዩ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ተናገሩ።

ዣን-ኢቭስ ሌ ድሪያን ከፈረንሳይ ከሚገኝ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ሀገራቱ ቃላቸውን አጥፈዋል ሲሉም ተደምጠዋል።

'አውኩስ (Aukus) በመባል የሚታወቀው የሁለቱ ሀገራት ስምምነት አውስትራሊያ በኑክሌር ኃይል የሚሠሩ የባሕር ሰርጓጅ መርከቦችን ለመሥራት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ከ አሜሪካ እንደሚታገኝ የሚያሳይ ነው።

ይህ ስምንነት ፈረንሳይ ከአውስትራሊያ ጋር ቀደም ብላ የፈረመችውን በቢሊዮን ዶላሮችን የሚቆጠር ስምምነት የሻረ ነው።

ዩኬንም ያካተተው ስምምነቱ በደቡብ ቻይና ባህር ላይ የቻይናን ተፅእኖ ለመከላከል የተደረገ እንደሆነም በስፋት ተገምቷል።

ታዲያ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ይፋዊ መግለጫ ከመሰጠቱ ከጥቂት ሰዓታት በፊት ነበር ለፈረንሳይ ጉዳዩ የተነገራት።

ይህም ፓሪስን ያስኮረፈ ሲሆን ከሀገራቱ አምባሳደሮቿን እስከ መጥራት ያደረሰ ነው።

የፈረንሳዩ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሌ ድሪያን ቅዳሜ ባደረጉት ቃለ ምልልስ በአጋሮቹ መካከል "ከባድ ቀውስ" እየተከሰተ ነው ብለዋል።

"በአሜሪካ እና በፈረንሣይ ግንኙነት ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አምባሳደራችንን ለማማከር መጥራታችን ከባድ ፖለቲካዊ እርምጃ ነው። ይህም አሁን በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የቀውስ መጠን ያመላክታል" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

አምባሳደሮቹ ከአሜሪካና አውስትራሊያ "ሁኔታውን እንደገና እንዲገመግሙ" ስለመጠራታቸው የተናገሩት ሚኒስትሩ ነገር ግን "ሁሌም እድሎቿን ከመጠቀም ወደኋላ የማትል" በማለት የወቀሷትን ዩኬን ከዛ አምባሳደሯን መጥራት "አያስፈልግም" ብለዋል።

"ብሪታንያ በዚህ ሁሉ ነገር እንደ ትንሽና ሦስተኛው ጎማ ናት ሲሉም" ተደምጠዋል።

አዲስ የተሾሙት የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊዝ ትሩስ ዘ ሰንዴይ ቴሌግራፍ ላይ በወጣ ጽሁፍ ስለሀገራቱን ሀገራቱ ስምምነት የተሟገቱ ሲሆን ብሪታንያ ፍላጎቶ ለማስጠበቅ "ጠንካራ" መሆኗን ያሳያል ብለዋል።

ይህ ፓሪስን ያስቀየመው ስምምነት አውስትራሊያን በኑክሌር ኃይል ሰርጓጅ መርከቦችን በማንቀሳቀስ በዓለም ሰባተኛው ሀገር ያደርጋታል። እንዲሁም በስምምነቱ አጋሮቷ [የአውስትራሊያ] የሳይበር አቅምን፣ ሰው ሰራሽ ልህቀትን እና ሌሎች የባህር ውስጥ ቴክኖሎጂዎችን እንደሚያጋሯት ያመለከታል።

አዲሱ ስምምነት 12 መደበኛ የባህር ሰርጓጅ መርከቦችን ለመገንባት ፈረንሣይ እንደ አውሮፓውያኑ በ2016 ከአውስትራሊያ ጋር የፈረመችውን የ37 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት እንዲያከትምለት የሚያደርግ ነው።

በአውስትራሊያ የፈረንሳይ አምባሳደር የነበሩትና ቅዳሜ'ዕለት ወደ ሀገራቸው የተመለሱት ዣን ፒየር ቴባውት አውስትራሊያ የቀድሞውን ስምምነት ለመሻር የወሰደችውን እርምጃ "ትልቅ ስህተት" ብለውታል።

ቻይና በበኩሏ በዚህ የደህንነት ስምምነት ውስጥ የተሳተፉትን ሶስት ሀይሎች "የቀዝቃዛው ጦርነት አስተሳሰብ" አላቸው ስትል ወቅሳለች።

የባይደን አስተዳደር ልዩነቶቻቸውን ለመፍታት በሚቀጥሉት ቀናት ከፈረንሳይ ጋር እንደሚመክር ኋይት ሀውስ አስታውቋል።

የአውስትራሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪሴ ፔይን ፈረንሣይ የገባትን "ቅሬታ" እረዳለሁ ያሉ ሲሆን "በሁለትዮሽ ግንኙነታችን ላይ የምንሰጠውን ዋጋ" ለማረጋገጥ ከሀገሪቱ ጋር እንደምንሰራ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።