ኦብነግ ከምርጫው ራሱን ያገለለው ለቦርዱ ያቀረበው አቤቱታው መፍትሄ ባለመግኘቱ እንደሆነ ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, ONLF TWITTER PAGE
በተራዘመውና መስከረም 20 ሊካሄድ በታቀደው የሶማሌ ክልል ምርጫ ላይ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) እንደማይሳተፍ አስታወቀ።
ግንባሩ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባና ሌሎች ችግሮችን በተመለከተ አቅርቦት የነበረው አቤቱታ መፍትሄ ባለማግኘቱ እንደሆነ፣ የኦብነግ የአዲስ አበባ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አህመድ አብዱላሂ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኦብነግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በክልሏ ዋና ከተማ ጅግጅግጋ ውስጥ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ነው ከምርጫው እራሱን ማግለሉ ያሳለፈበት ውሳኔ ላይ ደረሰው።
ፓርቲው ከምርጫው ራሱን ለማግለል የወሰነበትን ሁኔታ አቶ አህመድ ሲያስረዱ "ከመራጮች ምዝገባ ጋር በተያያዘ ችግሮች እንዳሉና የምርጫ ካርድም የተሰራጨው ለሕዝቡ ሳይሆን ለገዢው ፓርቲ ካድሬዎችና ደጋፊዎች እንደሆነ እንዲሁም ገዥው ፓርቲ ለራሳቸው ወገኖች ሲያድሉ ነበር" ይላሉ።
ይህንንም በተመለከተ ለምርጫ ቦርድ ከተለያዩ ማስረጃዎች ጋር በማያያዝ ማስገባታቸውን ገልጸዋል።
በሶማሌ ክልል የመራጮች ምዝገባን አስመልክቶ በምርጫ ቦርድ አጣሪ ቡድን ተሰማርቶ የነበረ ሲሆን በክልሉ የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ብቻ ድጋሚ የመራጮች ምዝገባ እንዲካሄድ መወሰኑንና ምርጫ ቦርድም ይህንን ውሳኔ ማሳለፉን ያስረዳሉ።
"በዚህም ምርጫ ቦርድ ለችግሩ መፍትሄ የሚሆን ውሳኔ አላስተላለፈም። ያቀረብናቸው በርካታ አቤቱታዎችና ማስረጃ በመራጮች ምዝገባ ላይ የነበሩ ችግሮች መፍትሄ ያገኛሉ ብለን ነበር። ነገር ግን መፍትሄ ይሆናል የምንለውን ነገር አላገኘንም" በማለት ተናግረዋል።
ኦብነግ ውሳኔውን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ የመራጮች የምዝገባ ሂደት ማጭበርበር የተሞላበት እንደሆነ ጠቅሶ ማስረጃዎችን ማስገባቱንና አቤቱታዎችን በተደጋጋሚ ቢያስገባም አልተስተካከለም ብሏል።
በሶማሌ ክልል ነፃ እና ፍትሃዊ ምርጫ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ቀርተዋል ብሏል።
"ምርጫውን ለሦስት ወራት በማራዘም የተፈጠረው የሕዝብ ተስፋ፣ ምርጫ ቦርድ የተበላሸውን አሰራር ባለማስቆሙ ሂደቱ ጠልሽቷል" በማለት መግለጫው አስፍሯል።
ኦብነግ በዚህ ውሳኔ ማዘኑንና በቀላሉም እዚህ ላይ እንዳልደረሰ ገልጿል። ኦብነግ የትጥቅ ትግሉን ለማቆም ዋናው ምክንያት የሶማሌ ሕዝብ መብቶችን በሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማስከበር በመሆኑ ነው ቢልም ከምርጫው ተገዶ መውጣቱን ገልጿል።
መግለጫው አክሎም በኦብነግ እና በሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ የዕጩዎች ምዝገባን ማገድ፣ ዕጩዎችን እና አባላትን ማጥቃትና ማዋከብ እንዲሁም ትክክለኛ የመራጮች ምዝገባ በመደናቀፉ "ለእውነተኛ ፍትህ ምንም መንገድ ባለመኖሩ በመጨረሻ ኦብነግን ከምርጫው እንዲወጣ ተገዷል" በማለት አስፍሯል።
አቶ አህመድ በበኩላቸው በአጠቃላይ የአገሪቱ ሁኔታ እንዳለ ሆኖ በሶማሌ ክልል በበለጠ የፖለቲካ ምህዳሩ ጠባብ ነበር ይላሉ። ነገር ግን ከሰሞኑ ከምርጫው ጋር ተያይዞ ችግሮች መጉላታቸውን ያስረዳሉ።
በክልሉ ዕጩዎች የሚታሰሩበትና እንዳይመዘገቡ የሚደረጉበት እንቅስቃሴዎች ነበሩ ይላሉ። ከዚህም ጋር ተያይዞ ኦብነግ ብቻ ሳይሆን ሶማሌ ክልል ላይ ሲወዳደሩ የነበሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከምርጫው ራሳቸውን ማግለላቸውን ተናግረዋል።
ምናልባት ውሳኔያቸውን አስቀልብሶ በምርጫ የሚሳተፉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችል ይሆን ወይ? ተብለው ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ አህመድ ሲመልሱ "ምርጫው አስር ቀን እንደመቅረቱ ይህ ሁኔታ የሚስተካከልበት ጊዜ ያለ አይመስለኝም" ብለዋል።
በሶማሌ ሕዝብ ላይ ሲደርስ የነበረውን ግፍና በደል ሰላማዊ በሆነ መንገድ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድርና መፍትሄም እንዲመጣ የሚገኝበትን ርብርብና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ በክልሉ በመንግሥትና ፓርቲ መካከል ልዩነት ባለመኖሩ በምርጫው ሂደት ላይ ችግሩን እንዳጎላው ይናገራሉ።
ለአስርት ዓመታት በትጥቅ ትግል የቆየ ፓርቲ እንደ መሆኑ መጠን ከዚህ በኋላ ፓርቲው ምን አይነት አካሄድ ይኖረዋል ለሚለው ጥያቄም፤ የሶማሌን ሕዝብ መብት ለማስከበር በሰላማዊ መንገድ ትግሉን እንደሚቀጥልና በእውነተኛ ብሔራዊ ውይይትም ለመሳተፍ ፈቃደኛ ነው በማለት መግለጫው የወደፊቱን አቅጣጫ አስቀምጧል።
በኢትዮጵያ መንግሥትና በኦብነግ መካከል የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ፓርቲው በርካታ ተግዳሮቶች ቢያጋጥሙትም ሰላማዊ በሆነ መንገድና በውይይት ለመቀጠል ቁርጠኝነት እንዳለው አስታውቋል።
ሆኖም በሶማሌ ክልል ውስጥ አሁን ያለውን ሰላምና መረጋጋት ለማስቀጠል ሁሉም ወገኖች ሰላሙን ለማስጠበቅ ሊሰሩ ይገባል ብሏል።
"በሌሎች የኢትዮጵያ ግዛቶች ጦርነት ባለበት ወቅት ሰላም በአንድ ግዛት ውስጥ ስለማይሰፍን፣ ኦብነግ አሁን ባለው አጥፊ ጦርነት ውስጥ ያሉ ሁሉም ወገኖች ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እና በሚቀጥሉት ጊዜያት የሚጎዱትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ለማዳን" ጥሪ አቅርቧል።
ጥቂት ስለ ኦብነግ
ለበርካታ ዓመታት በምሥራቃዊው የአገሪቱ አካባቢ የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ የነበረው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር ወደ አገር ቤት ተመልሶ በሰላማዊ ትግል ውስጥ ለመሳተፍ መወሰኑ ይታወሳል።
ኦብነግ ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ትግል ያደርጉ ከነበሩ አማጺ ቡድኖች መካከል አንዱ ሲሆን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1984 ነበር የተመሰረተው። ቡድኑ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ መንግሥት ሽብርተኛ ተብለው ከተሰየሙ ቡድኖች ዝርዝር ውስጥ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ሦስት የፖለቲካ ቡድኖች ከሽብር ቡድን ዝርዝር ውስጥ በፓርላማው ውሳኔ እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ በውጭ የሚገኙ የታጠቁ ተቃዋሚዎች ወደ አገር ቤት መመለሳቸው ይታወቃል።
አብነግ የኦጋዴን ሕዝብ ብሎ የሚጠራውን በምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚገኘው የሶማሌ ሕዝብ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ለማስከበር በፖለቲካዊና ወታደራዊ መስኮች ትግል ሲያደርግ ቆይቷል።
ኦብነግ ከምስረታው አስራ አራት ዓመታት በኋላ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ሊግ ጋር በመዋሃድ የሶማሊ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን መስርተው ነበር።
መስከረም 20 ሶማሌ ክልልን ጨምሮ የሚካሄደው ምርጫ
ስድስተኛው አጠቃላይ ብሔራዊ ምርጫ በዋናነት ሰኔ 14/2013 ዓ.ም የተካሄደ ቢሆንም በፀጥታ ችግር፣ በመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ በታዩ ግድፈቶች፣ በመራጮች ምዝገባ ላይ የቀረቡ አቤቱታዎችን ለማጣራት ጊዜ በማስፈለጉ የድምፅ መስጫው ቀን በአንዳንድ ክልልሎችና የምርጫ ክልሎች እንዲራዘም መወሰኑ ይታወቃል።
ምርጫ የተራዘመባቸው ሶማሌ፣ ሐረሪ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል መስከረም 20 ምርጫ እንዲካሄድ ተወስኗል።
ምርጫ ያልተደረገበት የሶማሌ ክልልንም በተመለከተ የመራጮች ምዝገባ እየተከናወነ በነበረበት ወቅት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ለቦርዱ አቤቱታ ቀርቦ ነበር።
ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ ሂደቱ መጣራት እንደሚገባው አምኖ የመራጮች ምዝገባ እንዲቆም በመወሰን 10 የምርጫ ክልሎች ላይ ምርመራ ተደርጓል። ከተለያዩ ሲቪል ማኅበራት የተውጣጣ አጣሪ ቡድን በመላክ ምዝገባ ሂደቱ ላይ የቀረቡትን አቤቱታዎች አጣርቷል።
የቡድኑንም ግኝት መሰረት በማድረግ ጅጅጋ 1፣ በጅጅጋ 2 የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልሎች የመራጮች ምዝገባ ሙሉ ለሙሉ በድጋሚ እንዲከናወን ተወስኗል።
ከዚህም በተጨማሪ በቀብሪደሃር ከተማ፣ በቀብሪደሃር ወረዳ፣ በመኢሶ፣ በአፍደም የክልል ምክር ቤት ምርጫ ክልሎች እንዲሁም የመራጮች ምዝገባ ሙሉ ለሙሉ በድጋሚ የሚካሄድባቸው ስፍራዎች ናቸው ተብሏል።
በተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ እንዲደገምባቸው የተላለፈባቸው ደግሞ በዋርዴር ምርጫ ክልል ውስጥ በ2 ምርጫ ጣቢያዎች፤ በፊቅ ምርጫ ክልል በ1 ምርጫ ጣቢያ፣ በገላዴን ምርጫ ክልል በ1 ምርጫ ጣቢያ፣ በጎዴ ከተማ ምርጫ ክልል በ4 ምርጫ ጣቢያዎች ፣ በምሥራቅ ኢሜ ምርጫ ክልል በ3 ምርጫ ጣቢያዎችና በቤራኖ ምርጫ ክልል በ3 ምርጫ ጣቢያዎች እንደሆነም ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።












