የአልጄሪያው የቀድሞ መሪ አብደላዚዝ ቡቴፍሊካ አረፉ

ቡቴፍሊካ ለመጨረሻ ጊዜ ለሕዝብ በታዩበት ወቅት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቡቴፍሊካ ለመጨረሻ ጊዜ ለሕዝብ በታዩበት ወቅት

የቀድሞው የአልጄሪያ ፕሬዝዳንት አብደላዚዝ ቡቴፍሊካ ከረጅም ጊዜ ሕመም በኋላ በ84 ዓመታቸው አረፉ።

ቡቴፍሊካ ከ20 ዓመት በፊት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተካሄደውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ተከትሎ ሁለቱ አገራት የሰላም ስምምነት እንዲያደርጉ ጉልህ ሚና መጫወታቸው ይታወሳል።

ቡቴፍሊካ አልጄሪያን ለ20 ዓመታት ገደማ ከመሩ በኋላ ለአምስተኛ የሥልጣን ዘመን ለመወዳደር መቅረባቸው ለከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ ዳርጓቸው ነበር።

ቡቴፍሊካ ከ1940 እስከ 1950ዎቹ አልጄሪያን ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ለማላቀቅ በተደረገው ጦርነት ውስጥ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል።

በመቀጠልም በ1991 የ200 ሺህ ያህል ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው የእርስ በእርስ ጦርነት መገባደዱን ተከትሎ በመጣው ወታደራዊው ግፊት ለፕሬዝዳንትነት በቅተዋል።

ፕሬዝዳንቱ በ2005 በስትሮክ ከተመቱ በኋላ ንግግር እና እንቅስቃሴ ማድረግ ላይ ከፍተኛ እክል ስላጋጠማቸው በአደባባይ እምብዛም አይታዩም ነበር።

ቡቴፍሊካ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመሩት አገራቸው አልጄሪያ በ1954 ዓ.ም ነፃ ከወጣች በኋላ ነበር።

ገና በ20ዎቹ አጋማሽ ላይ ሳሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው በመሾማቸው በወቅቱ የዓለም ወጣቱ ሚኒስትር ተብለውም ነበር።

ለ16 ዓመታት በአልጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ያገለገሉ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ ነበራቸው።

በ1966 የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዝዳንት የነበሩት ቡቴፍሊካ የፍልስጤም መሪ የነበሩትን ያሲር አራፋት ለተባበሩት መንግሥታት ንግግር እንዲያደርጉ የጋበዙበት ሁኔት ታሪካዊ ነበር።

በተጨማሪም ቻይና የተባበሩት መንግሥታት መቀመጫ ሊኖራት እንደሚገባ በመሟገታቸው እንዲሁም በወቅቱ በደቡብ አፍሪካ የነበረውን የአፓርታይድ አገዛዝን በይፋ በመቃወማቸውም ቡቴፍሊካ ይታወሳሉ።

ለኔልሰን ማንዴላ ወታደራዊ ሥልጠና በመስጠታቸውም ይታወቁ ነበር።

ቡተፍሊካ በ1970ዎቹ በቀረበባቸው የሙስና ክሶች ምክንያት በስደት የኖሩ ሲሆን በኋላ ላይ ክሶቹ ውድቅ መደረጋቸውን ተከትሎ በ1980ዎቹ ወደ አገራቸው ተመልሰው ከሦስት አስርተ ዓመታት በኋላ የአልጄሪያ የመጀመሪያው የሲቪል መሪ ሆነው ተሹመዋል።

የአገሬው ሰው "ቡቴፍ" እያለ የሚጠራቸው የቀድሞው ፕሬዘዳንት በመከላከያው እና በእስላማዊ ታጣቂ ቡድኖች መካከል ሰላም በማምጣት የአገሪቷን የእርስ በእርስ ጦርነት በዘላቂነት ለመፍታት ችለዋል።

ቡቴፍሊካ በ2000 የፕሬዘዳንትነት ዘመንን ለሁለት ጊዜ የሚገድበውን የአልጄሪያን ሕገ-መንግሥት በማሻሻል ለተጨማሪ ሁለት የሥልጣን ዘመናት ቆይታቸውን አራዝመዋል።

በመቀጠልም የአረብ አብዮት በመላው ሰሜን አፍሪካ ሲነሳ ቡተፍሊካ ሕዝባዊ ድጎማዎችን በፍጥነት ያሳደጉ ሲሆን ለረጅም ዓመታት የቆየውን የአልጄሪያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንስተው ነበር።

ለመጨረሻ ጊዜ ለሕዝብ የታዩትም ከአራት ዓመት በፊት በአልጄርስ የተገነባውን የባቡር ጣቢያ እና እድሳት ተድርጎለት የነበረው የኬቼዋ መስጊድን ባስመረቁበት ወቅት ሲሆን ይህም በስትሮክ ከተመቱ ከአራት ዓመት በኋላ ነበር።

በወቅቱም ታናሽ ወንድማቸው ሰይድ ቡቴፍሊካ ከጀርባ አገሪቷን ይመራ እንደነበር ይታመን ነበር።

በሕመም ላይ የነበሩት ፕሬዝዳንቱ ለአምስተኛ የሥልጣን ዘመን እንደሚወዳደሩ ሲሰማ መላው አልጄሪያ በአመጽ ተቀጣጠለች።

ታይቶ በማይታወቅ መልኩም በአገር አቀፍ ደረጃ በየሳምንቱ ሰላማዊ ሰልፎች ይደረጉ ነበር። ይህንን ተከትሎም ምርጫውን ለሌላ ጊዜ በማስተላለፍ ብሎም በአንድ ዓመት ውስጥ ሥልጣን ለመልቀቅ ቃል ከገቡ በኋላ ቡቴፍሊካ ከሥልጣን ወርደዋል።

ይህም አልጄሪያዊያን ቡቴፍሊካን ለመጨረሻ ግዜ ያዩበት ጊዜ ነበር።