"የአሜሪካ ፖሊሲ ያልተጠበቀ ከመሆኑ ባሻገር ከሰብአዊ መቆርቆር ያለፈ ነው" ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አሜሪካ ከኢትዮጵያ አንጻር የምትከተለው ፖሊሲ ያልተጠበቀ ከመሆኑ ባሻገር ከሰብአዊ መቆርቆር ያለፈ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ገለጹ።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሠሜን ኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት በተመለከተ በተሳታፊዎቹ ላይ ማዕቀብ ለማመጣል የሚያስችል ትዕዛዝ መፈረማቸውን ተከትሎ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግልጽ ደብዳቤ የጻፉት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ወዳጅና የደኅንነት ስትራተጂካዊ አጋር ነች ያሏት ዩናይትድ ስቴትስ "ከቅረብ ጊዜ ወዲህ በአገሬ ላይ የምትከተለው ፖሊሲ አስገራሚ ብቻ ሳይሆን በግልጽ በሚታይ ሁኔታ ለሰብአዊነት ከመቆርቆር ያለፈ ነው" ሲሉ ተችተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ግልጽ ደብዳቤ የጻፉት በአፋርና በአማራ ክልል ንጹሃን ዜጎች "ሆን ተብሎ በህወሓት በሚሰነዘር ጥቃት እንዲፈናቀሉ፣ እንዲገደሉ፣ ንብረታቸውና ተቋማቶቻቸው እንዲወድሙ በሚደረግበት" ጊዜ መሆኑን ጠቅሰው፤ ቡድኑ የትግራይ ህጻናትን ወደ ጦርነት እየማገደ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተሳሳተ ምክንያት መላው ዓለም አይኑን በኢትዮጵያ ላይ ማተኮሩን በመጥፎ አጋጣሚነት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነገር ግን በተመሳሳይ በአገሪቱ ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀውን ቡድን "በይፋ ተጠያቂ ለማድረግ አልቻለም" ሲሉ ወቅሰዋል።

ጨምረውም ባለፉት ወራት "ለመበልጸግ ሰፊ አቅም ባላትና በማደግ ላይ ባለችው የአፍሪካ አገር [ኢትዮጵያ] ላይ ተገቢ ያልሆነ ጫና እየተደራረበባት" መምጣቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደብዳቤያቸው ላይ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ውስጥ ካካሄደችው ሕግን የማስከበር ዘመቻ ጋር በተያያዘ በአገሪቱ ላይ እየተፈጸመ ያለው ተገቢ ያልሆነ ያሉት ይህ ጫና "አድሏዊ በሆነና መሬት ላይ ያለውን እውነታ በተቀናበራ ሁኔታ ማዛባትን መሠረት ያደረገ ነው" ሲሉ ተችተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደብዳቤያቸው ህወሓት በአገሪቱ ሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ የተፈጸሙ በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን አሜሪካንን ጨምሮ ከተለያዩ ምዕራባዊያን መንግሥታት ጥቂት ወይም ምንም ተቃውሞ አልቀረበበትም ብለዋል።

አሁን ግን "ወንጀለኛው አውዳሚ ቡድን" ያሉት ህወሓት የሦስት ሺህ ዘመን ያላትን አገር ለማፍረስ የሚችለውን ሁሉ እያደረገ ዓለም አቀፉን የሰብአዊ መብቶችና የዴሞክራሲ ተቋማትን ለእራሱ ፕሮፓጋንዳ በመጠቀም ክስ እያቀረበ ነው ሲሉ በደብዳቤያቸው ላይ ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም ችግር ይከሰትበታል በማለት ማስጠንቀቂያ ሲሰነዘርበት ነበር ያሉት ያለፈው ዓመት ምርጫ 40 ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ ተሳትፎበት ከዚህ በፊት ባልታየ ሁኔታ ለዲሞክራሲ ያለውን ፍላጎት አሳይቷል ሲሉ በሰላም መጠናቀቁን አመልክተዋል።

በዚህ ወር መጨረሻ ላይ መንግሥት ለመመስረት የሚያስችለው መቀመጫ ያገኘው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲ "ተፎካካሪ ለሆኑ ፍላጎቶች እና ግፊቶች ሳይንበረከክ" ሕዝቡ የሚገባውን ክብር፣ ደኅንነት እና ልማትን እንዲያገኝ የሚቻለውን ያደርጋል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ፣ ቀጠናዊና ዓለም አቀፍ የደኅንነት ጉዳይ በብዙ የዓለም ክፍሎች ውስጥ የአሜሪካ ቁልፍ የትኩረት ጉዳይ ቢሆንም በአሜሪካ የሽብርተኛ ቡድኖች ዝርዝር ውስጥ ይገኛል ባሉት ህወሓት ላይ "ስለምን አስተዳደርዎ ጠንካራ አቋም አልያዘም" ሲሉ ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሽብርተኝነት ስጋት የሆነውን አልሻባብን በመዋጋት በኩል የአሜሪካ ዋነኛ አጋር ሆና እንደምትቀጥል የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "የአካባቢው መረጋጋት ስጋት ከሆነው ተመሳሳይ ሽብርተኛ ድርጅት አንጻር አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጎኗ እንደትቆም ትጠብቃለች" ብለዋል።

የአሜሪካ ሕዝብና ቀሪው የምዕራቡ ዓለም በተዛቡ ትርክቶች በጥቅም ትስስር ሳቢያ "ተጎጂውን ጨቋኝ፤ ጨቋኙን ተጎጂ" አድርገው እንደሚያቀርቡ ገልጸው፤ ነገር ግን "እውነት በዚህች ኩሩ አገር ላይ እንደምተገለጥ እርግጠኛ ነኝ" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ የአሜሪካ አስተዳደሮች በጥድፊያ በተወሰዱ እርደምጃዎች ምክንያት ከመፍትሄ ይልቅ በርካታ ሕዝቦችን በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንዲወድቁ ማድረጉን በመግለጽ "ኢትዮጵያ ከሚሊዮኖች ደኅንነት ይልቅ ሥልጣንን በሚያስቀድሞ ግለሰቦች ለተቀናበረ ግፊት አትንበረከክም" ብለዋል።

ባለፈው ዓመት ትግራይ ውስጥ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ አሜሪካ ግጭቱ እንዲቆምና ድርድር እንዲደረግ በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የተለያዩ ጫናዎችን ስታሰርፍ ቆይታለች።

ዛሬም ፕሬዝዳንት ባይደን በትግራይ ጦርነት ውስጥ የተለያዩ የመብት ጥሰቶችን ፈጽመዋል የተባሉ አካላት ላይ ያነጣጠረ አዲስ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ፈርመዋል።

በዚህም ማዕቀቡ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የኤርትራ መንግሥት፣ የአማራ ክልል አስተዳደር ባለሥልጣናትና የህወሓት አባላትን ተጠያቂ የሚያደርግ እንደሆነም ተገልጿል።