አፍጋኒስታን፡ ታሊባን ለሴት ተማሪዎች አዲስ ሕግ አወጣ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ታሊባን የአፍጋኒስታን ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን በጾታ እንደሚለዩ እና አዲስ የአለባበስ ሥርዓትም እንደሚተዋወቅ አስታወቀ።
የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሩ አብዱል ባቂ ሃቃኒ ሴቶች ትምህርታቸውን መከታተል እንደሚፈቀድላቸው፤ ነገር ግን ከወንዶች ጋር ተቀምጠው መማር እንደማይችሉ ተናግረዋል። ሚኒስትሩ ተማሪዎቹ የሚማሯቸውን የትምህርት ዓይነቶችም አስታውቀዋል።
በታሊባን አስተዳዳር ሥር ከእአአ 1996 እስከ 2001 ባሉት ዓመታት ሴቶችና ልጃገረዶች ከትምህርት ቤትና ዩኒቨርሲቲዎች ታግደው ነበር።
አሁን ግን ታሊባን ሴቶችን ከመማርና ከሥራ አልከለክላቸውም ብሏል፤ ይሁን እንጅ ነሐሴ 15 አገሪቷን ከተቆጣጠሩ ጀምሮ የፀጥታ ሁኔታው እስከሚሻሻል ድረስ በሕዝብ የጤና ተቋማት ከሚያገለግሉት በስተቀር ሴቶች ሥራ እንዳይሰሩ ጠይቋል።
ይህ አዲስ የወጣው የከፍተኛ ትምህርት ፖሊሲ የተዋወቀው ታሊባን በፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት የአስተዳዳር ዘመናቸውን መጀመር ምልክት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ከሰቀለ በኋላ ነው።
ታሊባኖች ቤተ መንግሥቱን በምርጫ የተመረጠውን መንግሥት አስለቅቀው የያዙት ከአንድ ወር በፊት ነበር።
አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ ታሊባን አገሪቷን ሳይቆጣጠር በፊት ከነበረውና ተቀባይነት ካለው ልምድ ጋር ልዩነትን የፈጠረ ነው።
በቀድሞው ሥርዓት ሴት ተማሪዎች በአለባበስ የተገደቡ አልነበረም፤ ዩኒቨርሲቲዎችም ሴት ተማሪዎች ከወንድ ተማሪዎች ጋር ጎን ለጎን ተቀምጠው ነበር ትምህርት የሚከታተሉት።
ይሁን እንጂ ሚኒስትሩ "ተማሪዎች ተቀላቅለው የሚማሩበትን የትምህርት ሥርዓት እንዲያበቃ ማድረግ ምንም ችግር የለውም" ብለዋል። ሕዝቡም ሙስሊም በመሆኑ ለውጡን እንደሚቀበለው ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
አንዳንዶች ግን አዲሱ ሕግ ዩኒቨርስቲዎች ወንዶችና ሴቶችን ለይቶ ለማስተማር አቅም ስለሌላቸው ሴቶችን ከትምህርት ያገላል ብለዋል።
ሆኖም ሚኒስትሩ በቂ ሴት መምህራን እንዳሉ ጠቅሰው እነዚህ መምህራን መገኘት ካልቻሉም ሌሎች አማራጮች እንደሚፈሉ ተናግረዋል።
"ሁሉም ነገር በዩኒቨርሲተው አቅም ላይ የተመሰረተ ነው፤ ወንድ መምህራንም ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው አሊያም ቴክኖሎጂ ተጠቅመው እንዲያስተምሩ ማድረግም ይቻላል" ብለዋል ሚኒስትሩ።
በዚህ ሕግ አንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማሩ ሴት እና ወንድ ተማሪዎችም ለየብቻ እንዲማሩ ይደረጋል። ይህ ግን በአፍጋኒስታን የተለመደ ነው።
አለባበስን በተመለከተም ሕጉ ሴቶች ሂጃብ እንዲለብሱ የሚጠይቅ ሲሆን፤ ነገር ግን በሂጃብ ላይ ተጨማሪ የፊት መሸፈኛ ማድረግ ግዴታ ስለመሆኑ ሚኒስተሩ በግልጽ ያሉት ነገር የለም።
አዲስ የተሾሙት ሚኒስትሩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሯቸው የትምህርት ዓይነቶችም እንደሚከለሱ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ታሊባን እስልምናን ፣ ብሔራዊና ታሪካዊ እሴቶችን በጠበቀ እንዲሁም ከሌሎች አገር ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን በሚያስችል መልኩ ምክንያታዊ የሆነ እስላማዊ መርሃ ሥርዓተ ትምህርት መፍጠር ይፈልጋል ብለዋል።
ይህ ሕግ የተዋወቀው ትናንት ሴቶች የታሊባንን የሥርዓተ ጾታ ፖሊሲ የሚደግፍ ሠላማዊ ሰልፍ ካካሄዱ በኋላ ነው።
በመቶዎች የሚቆጠሩ አብዛኞቹ ኒቃብ የለበሱና የታሊባን ሰንደቅ ዓላማን የያዙ ሴቶች አዲሱን አስተዳዳር በማሞገስ ንግግር ሲያደርጉ ተደምጠዋል። ሠላማዊ ሰልፈኞቹ የሴቶች መብት እንዲጠበቅ በሚል ቀደም ሲል በአገሪቷ በተካሄዱ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ የተሳተፉትንም ነቅፈዋል።
ታሊባን እአአ 2001 ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ የአፍጋኒስታንን የትምህርት ሥርዓት በማሻሻልና በተለይ ሴቶችና ልጃገረዶች እንዲማሩ በማስቻል ረገድ በርካታ ውጤቶች ተመዝገበዋል።
በቅርብ የወጣ የዩኔስኮ ጥናት እንደሚያሳየው ከታሊባን አስተዳዳር በኋላ በነበሩት 17 ዓመታት ውስጥ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማሩ ሴት ተማሪዎች ቁጥር ከነበረበት ዜሮ ወደ 2.5 ሚሊየን አድጓል።
ሪፖርቱ አክሎም የሴት ተማሪዎች የትምህርት ምጣኔም በአስርት ዓመት ውስጥ በእጥፍ አድጎ 30 በመቶ ደርሷል ብሏል።
የታሊባን አዲስ መንግሥት የሴቶች ጉዳይ ሚኒስቴርን በግብረ ገብ ሚኒስቴር ተክቶታል።
በታሊባን የቀድሞ አስተዳዳር በብዙዎች የሚፈራው ይህ መሥሪያ ቤት፤ ሐይማኖታዊ ፖሊሲዎችንና የሸሪዓ ሕጎችን የማስፈፀም ሥልጣን ነበረው።
መሥሪያ ቤቱ ያለአግባብ የለበሱ ሴቶችን እና ከወንድ ጠባቂዎቻቸው ውጭ ከቤት ውጪ የተገኙ እንዲሁም ሌሎች ሕግ የጣሱ ሴቶችን በመደብደብ ይታወቃል።
ታሊባን ወደ ሥልጣን ይመለሳል በሚል በርካታ በሙያቸው ታዋቂ የሆኑ ሴቶች አፍጋኒስታንን ጥለው ወጥተዋል።
የአገሪቱ እውቅ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ አርያና ሳይድ በአሜሪካ እቃ ጫኝ አውሮፕላን ተሳፍራ አፍጋኒስታንን ለቃ ወጥታለች። የፊልም ዳሬክተሯ ሳህራ ካሪሚም አገሯን ተሰናብታ ወደ ዩክሬን ተሰዳለች።












