ታሊባን በማሕበራዊ ሚድያው 'ጦርነት' እንዴት ሊሳካለት ቻለ?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ባለፈው ግንቦት መባቻ የዩናይትድ ስቴትስና የኔቶ ኃይሎች ከአፍጋኒስታን መውጣት ሲጀምሩ ታሊባን የአፍጋን ብሔራዊ ጦርን ድል መንሳት ጀመረ።
ታሊባን በወቅቱ ከዚህ በፊት አድርጎት የማያውቀውን ድርጊት ማከናወን መጀመሩ ለብዙዎች እንግዳ ነበር።ቡድኑ ከጦርነቱ ጎን ለጎን የማሕበራዊ ድር አምባውን ጎራ በድምቀት ተቀላቀለ።
በርካታ የማሕበራዊ ሚድያ ገፆች የካቡል መንግሥትን እያጥላሉ ታሊባንን ደግሞ በተቃራኒው ያወድሱ ጀመር።
አንዳንድ የትዊተር መልዕክቶች የመሰላል [ሃሽታግን] ዘመቻውን ያጧጡፉት ያዙ። በአረብኛና እንግሊዝኛ የቃላት ጨዋታው ደራ።
ሃሽታግ ከታሊባን ጋር እቆማለሁ፤ የካቡል መንግሥት ቀውስ ላይ ነው እና ሌሎችም መልዕክቶች በቡድኑ ደጋፊዎች ይሰራጩ ገቡ።
ይህን ያስተዋሉት በወቅቱ የታሊባን ምክትል ፕሬዝደንት የነበሩት አምሩላህ ሳሌህ የጦር ኃይሉና ሕዝቡ የታሊባንን 'ቀዳዳ' ማሕበራዊ ሚድያ ላይ ተመልክቶ እንዳይዘናጋ ሲሉ ማስጠንቀቂያ ሰጡ።
አልፎም ሕዝቡ እኒህን ዜናዎች ለሌሎች ባያጋራ መልካም ነው አሉ።
ታሊባን ቀድሞ ከሚታወቅበት አሠራር ወጥቶ ጦርነቱን ከጦር ሜዳ ባለፈ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መድረክ ለማድረግ ማሰቡ እሙን ነው።
ታሊባን ለመጀመሪያ ጊዜ በፈረንጆቹ 1996 አፍጋኒስታን ውስጥ ወደ ሥልጣን ሲመጣ በይነ መረብን አግዷል፣ ቴሌቪዥኖችን ወርሷል፣ ካሜራዎችን አውድሟል።
በ2005 ታሊባን የኢስላሚክ ኤሜሬትስ ኦፍ ታሊባን ኦፊሴላዊ ድረ-ገፅ የሆነውን 'አል-ኢማራህን' ይፋ አደረገ። ይህ ድረ-ገፅ አሁን በአምስት ቋንቋዎች ይዘቶችን ለአንባቢያን ያቀርባል።
በእንግሊዝኛ፣ አረብኛ፣ ፓሽቶ፣ ዳሪ እና ኡርዱ ቋንቋዎች ይዘት ያለው ይህ ድረ-ገፅ ከፅሑፍ በተጨማሪ በተንቀሳቃሽ ምስልና በድምፅ ነው መልዕክቱን የሚያስተላልፈው።
እዚህ ዌብሳይት ላይ ለሚወጡት ሃተታዎች የይለፍ ፈቃድ የሚሰጠው የኢስላሚክ ኤሜሬትስ ኦፍ አፍጋኒስታን ባሕል ከሚሽን ቃል አቀባይ ዛቢሁላህ ሙጃሂድ ነው።
ሙጃሂድ ለመጀመሪያ ጊዜ የከፈተው የትዊተር ገፅ በኩባንያው ቢዘጋበትም በ2017 ድጋሚ ሌላ ገፅ ፈጥሮ አሁን ከ317 ሺህ በላይ ተከታዮች አፍርቷል።
ሰውዬው በሥሩ የታሊባንን ርዕዮተ ዓለም የሚያስተዋውቁ ሰዎች ያሉበት ቡድን ይመራል። የዚህ ቡድን የማሕበራዊ ድር አምባ ኃለቃ ደግሞ ቃሪ ሳዒድ ኾስቲ እንደሆነ ይታመናል።
ቃሪ ቡድኑ ትዊተር የተሰኘው ድር አምባ ላይ አተኩሮ የሃሽታግ ዘመቻውን የሚያጧጡፍ ክንፍ እንዳለው ለቢቢሲ ተናግሯል።አልፎም ዋትስአፕና ፌስቡክ ላይ መልዕክት የማስተላለፍ ሥራም ይሠራሉ።
"ጠላቶችቻን፣ ቴሌቪዥን፣ ራድዮ ኦፊሴላዊ የማሕበራዊ ድር አምባ ገፅ አላቸው። እኛ ግን ምንም የለንም። ቢሆንም ትዊተርና ፌስቡክ ላይ ተዋግተን አሸንፈናቸዋል" ይላል ቃሪ።
እሱ እንደሚለው ሥራው "በርዕዮተ ዓለሙ ምክንያት ታሊባንን የተቀላቀሉ ሰዎችን ወደ ፌስቡክና ትዊተር መምራትን ዘመቻውን እንዲቀላቀሉ ማድረግ" ነው።
አፍጋኒስታን ውስጥ 8.6 ሚሊዮን ገደማ የበይነ መረብ ተጠቃሚዎች እንዳሉ ይታመናል። የኔትዎርክ አለመኖርና የዳታ መወደድ ለበይነ መረብ ተጠቃሚዎች ቁጥር ማነስ እንደምክንያት ይጠቀሳሉ።
ቃሪ እንደሚለው ኢስላሚክ ኤሜሬትስ ኦፍ አፍጋኒስታን ለአባላቶቹ በወር 1 ሺህ አፋጋኒስ አሊያም 11.5 ዶላር የሚያወጣ ዳታ ይገዛል።
ሰውዬው አራት ሙሉ በመሉ የተሟሉ ምስል እና ድምፅ እንዲሁም ሌሎች ይዘቶች የሚመረቱባቸው ስቱዲዮዎች እንዳሏቸዋ ይናገራል።
ከእነዚህ ስቱዲዮዎች የሚወጡ ይዘቶች ዓላማቸው የታሊባን ተዋጊዎችን ማወደስና ማሞገስ የታሊባንን መንግሥት ማንኳሰስ የዉጪ ኃይሎችን መክሰስ ነው።
በርካታ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ዩቲዩብ ላይ እንዲሁም የኤሜሬቱ ድረ-ገፅ ላይ ይገኛሉ።
ቡድኑ ትዊተርና ዩቲዩብ ላይ በነፃነት ይዘቶቹን ይለጥፋል። ነገር ግን ፌስቡክ ታሊባንን "አደገኛ ቡድን" ብሎ ስለፈረጀው ከቡድኑ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ገፆች እየተከታተለ ያጠፋል። ፌስቡክን ይህንን አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት አስታውቋል።
ቃሪ እንደሚለው ታሊባን ፌስቡክ ያለውን ተፅዕኖ መቋቋም ስላልቻለ ትኩረቱን ትዊተር ላይ ያደርጋል።
ምንም እንኳ የአሜሪካ መንግሥት ሃቃኒ ኔትዎርክና የቡድኑ መሪ አናስ ሃቃኒን ሽብርተኛ ብሎ ቢፈርጅም በርካታ የቡድኑ አባላት መዓት ሺህ ተከታዮች ያሏቸው ገፆች አሏቸው።
ታሊባን ለወትሮው የሚታወቀው የመሪዎቹንና የአባላቱን ማንነት በመደበቅ ነው። የቡድኑ መሥራች የሆነው ሙላህ ኦሜር በደንብ የሚታይ አንድ ፎቶ እንኳ የለውም።
ነገር ግን አሁን አሁን ሁኔታዎች እየተቀየሩ ይመስላሉ። ዓለም አቀፍ እውቅና ለማግኘት እየታተረ ያለው ታሊባን በማሕበራዊ ድር አምባና በመገናኝ ብዙሃን ብቅ ብቅ ማለት ጀምሯል።
ታሊባንን በማሕራዊ ድር አምባዎች ላይ ሲቃወሙ የነበሩ አፍጋኒዊያን የበቀል እርምጃን በመፍራት አሁን አሁን ገፃቸውን እያጠፉ ነው።
ታሊባን ጭካኔ የተሞላበትን መንገዱን ይተዋል ወይ የሚለው ግን አሁንም ጥያቄ ነው።












