የዋየር ፊልም ተዋናዩ ማይክል ኬ ዊልያምስ ሞቶ ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኤች.ቢ.ኦ. ቴሌቪዥን ተከታታይ ፊልም የሆነው 'ዘ ዋየር' ዋነኛ ተዋናይ የሆነው አሜሪካዊው ተዋናይ ማይክል ኬኔት ዊልያምስ በኒውዮርክ አፓርታማው ውስጥ ሞቶ ተገኝቷል። ተዋናዩ ዕድሜው 54 ነበር።
የአሜሪካ ሚዲያዎች የአሟሟቱን ምክንያት በተመለከተ የሕግ አስከባሪ ምንጮችን ጠቅሰው እንደዘገቡት ከመጠን በላይ የአደንዛዥ ዕፅ ከመውሰድ ጋር ጥርጣሬ ቢሆንም ይህ ግን በይፋ አልተረጋገጠም።
ስመ ጥር በሆነው የኤሚ ሽልማት ሶስት ጊዜ በእጩነት የቀረበው ሚካኤል ባለፉት ዓመታት ከአደንዛዥ ዕጾች ጋር ስለነበረው ትግል በግልፅ ሲናገርም ነበር።
ከፍተኛ አድናቆትን ባተረፈው 'ዘ ዋየር' ተከታታይ ፊልም ኦማር ሊት የተባለ፣ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ፣ የጎዳና ላይም የዕፅ አዘዋዋሪ ዋነኛ ሰውን የወከለ ገፀ ባህርይ ተጫውቷል።
ከዚህም በተጨማሪ በአውሮፓውያኑ 2010 'ብሮድ ዋክ ኢምፓየር' በሚለው ተከታታይ የቴሌቪዥን ፊልም አልበርት 'ቻኪ' ዋይት የተባለ ኃይለኛ ወንበዴን ወክሎ ተጫውቷል።
የኒውዮርክ ፖሊስ መምሪያ ቃል አቀባይ ጆን ግሪምፕል ሰኞ ዕለት በአገሬው አቆጣጠር ስምንት ሰዓት ላይ ከተዋናዩ ማይክል ቤት የአደጋ ጊዜ ጥሪ ከደረሳቸው በኋላ ብሩክሊን የሚገኘው አፓርታማ ፖሊስ መሄዱን አስታውቋል።
ተዋናዩ ሞቶ መገኘቱንም ተከትሎ በርካታ የፊልም ኢንዱስትሪው ማህበረሰብና የስራ ባልደረቦቹ በማይክል ሞት የተሰማቸውን ኃዘን በማህበራዊ ሚዲያ እየገለጹ ይገኛሉ።
"ለዚህ ወንድሜ ያለኝ ፍቅር ጥልቀት ሊገለፅ የሚችለው በመሞቱ የደረሰብኝ ህመም ጥልቀት ጋር ተመሳሳይ ነው" ሲል በዋየር ተባባሪ ተዋናዩ ኮከብ ዌንዴል ፒርስ በትዊተር ገጹ አስፍሯል።
ዌንዴል አክሎም " የላቀ ችሎታ የነበረው ከራሱ አልፎ ለሰብዓዊነት የቆመና ለተዘነጉትም ድምፅ ለማሰማት ወደኋላ የማይል ነበር" ብሎታል።
በአውሮፓውያኑ 1966 በኒውዮርክ ውስጥ የተወለደው ማይክል ወደ ትወና ሙያው ከመግባቱ በፊት ዳንሰኛ ሆኖ ከሙዚቀኞቹ ማዶና እና ጆርጅ ሚካኤል ጋር ሰርቷል።
ከዚያም በተጨማሪ ስመ ጥር በሆኑ ናሺናል ብላክ ቲያትር ኩባንያም ሰርቷል።












