የኢትዮጵያ መከላከያ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ አማፅያን ተገድለዋል አለ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል እተደረገ ባለው ጦርነት ከ5 ሺህ 600 በላይ የትግራይ አማፅያንን ገድያለሁ ብሏል።
ቅዳሜ እለት በሰጡት መግለጫ ይህንን የተናገሩት የመከላከያ ሚኒስቴር የሰራዊት ግንባታ ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ የሞቱት ተዋጊዎች መቼ እንደሆነ ጊዜውን አልጠቀሱም።
አንዳንዶች ግን ይህ የሆነው በቅርብ ጊዜ በተካሄዱ ውጊያዎች ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።
ጄኔራሉ በተጨማሪ 2 ሺህ አማፅያን መቁሰላቸውን እና 2 ሺህ መማረካቸውን ተናግረዋል።
በጥቅምት ወር መጨረሻ የጀመረው ደም አፋሳሽ ግጭት አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ለረሃብ እንደሚጋለጡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስጠንቅቋል።
ጄኔራል ባጫ ህወሓት በአጎራባቾቹ አማራና አፋር ክልሎች ጦርነት ማስፋቱን ተከትሎ ኢትዮጵያን ለመበታተን ሞክሯል ሲሉ ወንጅለውታል።
አንድ የህወሓት ክፍለ ጦር በትግራይ እና በአማራ ድንበር ላይ ሁመራን ለመቆጣጠር ሞክሮ የነበረ ቢሆንም "ሙሉ በሙሉ ተደምስሷል" ብለዋል።
በተመሳሳይም በትናንትናው ዕለት በትግራይ ክልል ሚዲያ በተሰጠው መግለጫ የትግራይ ኃይሎች በአፋር ግንባር ሰሜን ወሎ ሃሩ ልዩ ስሙ ሰዶማ በተባለ ቦታ ከ5460 በላይ የሆነ የፌደራሉን ኃይል ከጥቅም ውጭ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በወልድያ ግንባር እንዲሁ 2 ሺህ 143 የፌደራሉ ጦር ኃይል አባላት ተደምስሰዋል ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግሥት እና በትግራይ ክልል ዋነኛ የፖለቲካ ፓርቲ በሆነው ህወሓት አመራሮች መካከል የነበረው መሻከር ወደማይታረቅ ደረጃ ደርሶ ወደ ጦርነት ያመራው በዚህ ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክልሉ ላይ ባለው ወታደራዊ ካምፕ ጥቃት ፈፅሟል በሚል ህወሓትን ከከሰሱ በኋላ የክልሉን መንግሥት ለማስወገድ ወታደሮችን ወደ ትግራይ ልከዋል።
በዚህ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ ተፈናቅለዋል ከነዚህም መካከል በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ ሱዳን ተሰድደዋል።
በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁለቱም አካላት መድፈር፣ የጅምላ ሲቪሎች ግድያና ሌሎች አሰቃቂ የመብት ጥሰቶችን በመፈፀም ይከሰሳሉ።

የጦርነቱ አሳዛኝ ውጤቶች
ቃልኪዳን ይበልጣል፣ የቢቢሲ ኢትዮጵያ ዘጋቢ
በመከላከያ ተገድለዋል ተብሎ የቀረበው የትግራይ አማፅያን አኃዝ ከፍተኛ ሲሆን እሱንም በተናጥል ማረጋገጥ ከባድ ነው።
ነገር ግን በዚህ ጦርነት ላይ አንድ ጉዳይ ግልፅ ነው። በዚህ አስር ወራት ባስቆጠረው ጦርነት አሳዛኝ ውጤቶችን አስከትሏል።
ጄኔራል ባጫ ደበሌ ቅዳሜ ዕለት በሰጡት መግለጫ በአየር ድብደባ የታገዘ ከባድ ውጊያ መደረጉን ገልጸዋል። ነገር ግን ውጊያው መቼ እንደተከናወነ ጊዜውን አልጠቀሱም።
ህወሓት ባልተጠበቀ ሁኔታ ሰኔ ወር ላይ ትግራይን ከፌደራል ሠራዊቱ እና ከአጋር ኃይሎቹ እጅ ከተቆጣጠረ በኋላ ወደ አጎራባቾቹ አማራና አፋር ክልሎች የዘመተ ሲሆን ይህም ሁኔታ የጦርነቱን መስፋት ያመላከተ ነው።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ የፌደራል ሠራዊቱ እና አጋሮቹ የትግራይን ኃይሎች ወደ ኋላ በመግፋት አንዳንድ ስትራቴጂካዊ ቦታዎችን ተቆጣጥረዋል።
ነገር ግን በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበችውን የላሊባላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት መገኛ ታሪካዊዋ የላሊበላ ከተማም ሆነ ሌሎች በአፋርና በአማራ የሚገኙ ቁልፍ ከተሞች አሁንም በህወሓት ቁጥጥር ስር ናቸው።
በያዝነው ሳምንት አርብ የተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ መንግሥት ለትግራይ የእርዳታ አቅርቦቶችን በጠበቀ መንገድ ዘግቷል ሲል ከሷል። በዚህም ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለአደጋ እየተጋለጡ መሆኑን አስጠንቅቋል።
ድርጅቱ "በአስርት ዓመታት ውስጥ በዓለም ላይ አስከፊው የረሃብ ሁኔታ" እንዲቀለበስ ከተፈለገ 5.2 ሚሊዮን ሰዎች አስቸኳይ እርዳታ ሊቀርብላቸው እንደሚገባ አስታውቋል።
ነገር ግን ቅዳሜ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ በክልሉ የደረሱትን 152 የጭነት መኪኖችን ጨምሮ 500 እርዳታ የጫኑ መኪኖች ወደ ክልሉ መግባታቸውን ገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ የፍተሻ የደኅንነት ኬላዎች ቁጥርም ቀንሷል ብሏል።
ለዚህ መግለጫ ገለልተኛ ማረጋገጫ አልተገኘም።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከነሐሴ 16 ጀምሮ አንድም እርዳታ የጫነ መኪና ወደ ትግራይ አልደረሰም ሲል ቅሬታ ያቀረበ ሲሆን በየቀኑም 100 የእርዳታ መኪኖች ያስፈልጋሉ ብሏል።














