በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከ7 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች መውደማቸው ተነገረ

በመቀለ የሚገኘው ኪሮስ ገሰሰ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተማሩ ያሉ የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Jemal Countess

የምስሉ መግለጫ, በመቀለ የሚገኘው ኪሮስ ገሰሰ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተማሩ ያሉ የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች

በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ከሰባት ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉና አንዳንዶች ደግሞ በከፊል መውደማቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ የትምህርት ሚኒስትር ጌታሁን መኩሪያ (ዶክተር፣ ኢንጅነር) እንዳሉት በጦርነቱ ሳቢያ በትግራይ ከ1.4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችንና ከ48 ሺህ በላይ መምህራን ከትምህርት ሥርዓት ውጪ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አጎራባቾቹ የአማራና የአፋር ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት በትምህርት ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመትን ማስከተሉን ሚኒስትሩ በማኅበራዊ የትስስር መድረክ ላይ አስፍረዋል።

ጨምረውም በአንድ ወር ብቻ በአፋር ክልል "88 ሺህ ተማሪዎች ይማሩባቸው የነበሩ 455 ትምህርት ቤቶች" በአማጺው የህወሓት ኃይሎች መውደማቸውን እንደተናገሩ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

በተመሳሳይ በአማራ ክልል ውስጥ 140 ትምህርት ቤቶችና ሁለት የመምህራን ማሰልጠኛና ኮሌጆች ሙሉ በሙሉና በከፊል ለውድመት መዳረጋቸውን ጌታሁን መኩሪያ (ዶክተር፣ ኢንጅነር) ገልጸዋል።

በዚህም ሳቢያ በሦስቱም ክልሎች የሚገኙ ከ1.42 ሚሊዮን በላይ በተለያዩ ደረጃዎች ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ውጪ ለመሆን ይገደዳሉ ብለዋል ሚኒስትሩ።

ከዚህ ቀደም ሂውማን ራይትስ ዋች ባወጣው ሪፖርት ትምህርት ቤቶች ለጦር ሰፈርነት መጠቀሚያ መሆናቸውንና መዘረፋቸውን በሪፖርቱ ዳስሷል።

ከዚህም መካከል የመንግሥት ወታደሮች በመቀለ የሚገኘውን ታሪካዊውን የአፄ ዮሃንስ መሰናዶ ትምህርት ቤት እንደ ጦር ሰፈር መጠቀማቸውንና ሲወጡም ኮምፒውተሮችን፣ የፕላዝማ መመልከቻ ቁሳቁሶችንና ምግብ በጭነት መኪኖች አጓጉዘዋል ሲል ከሷል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ለአጭር ጊዜ ትምህርት ቤቱን ተረክቦ እንደገና ትምህርት ለማስቀጠል የጥገና ስራም ሞክሮ ነበር። ሆኖም ወታደሮቹ በየካቲት ወር አካባቢ እንደገና ተመልሰው ትምህርት ቤቱን ለሶስት ወራት ያህል በጦር ሰፈርነት ሲጠቀሙበት መቆያታቸውን ሪፖርቱ አትቷል።

አዲስ አበባ ውስጥ እየተካሄደ ባለው አገር አቀፍ የአጠቃላይ የትምህርት ዘርፍ ዓመታዊ ጉባዔ ላይ ይኸው በትምህርት ተቋማት ላይ የደረሰውን ውድመት በተመለከተ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ "ባለፉት ዓመታት ትምህርት ቤቶችን በመገንባት አገሪቱ ያስመዘገበችውን እድገት ወደኋላ የሚጎትት ነው" ብለዋል።

በጉባዔው ላይ እየተጠናቀቀ ባለው ዓመት የኮሮናቫይረስ፣ በትግራይ የተቀሰቀሰው ጦርነትና ግጭቶች፣ ጎርፍ እንዲሁም ድርቅ የትምህርቱን ዘርፍ የተፈታተኑ ዋና ዋና ተግዳሮቶች እንደነበሩ ተገልጿል።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ፡ የሦስተኛ ወገን ይዘቶች ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል

የ X ይዘት መጨረሻ

በጦርነቱ ምክንያት በትምህርት ተቋማት ላይ የደረሰውን ውድመት "አሳዛኝ" ያሉት የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶክተር፣ ኢንጅነር) ትምህርት ቤቶቹ የወደሙት በየትኛው አካል እንደሆነ ባይጠቅሱም "አማፂው ህወሃት በከፈተው ጦርነት ምክንያት የወደሙ ትምህርት ቤቶች" በማለት በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።

ባለፈው ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ በትግራይ ክልል ውስጥ በተቀሰቀሰው ጦርነት ሳቢያ ከትምህርት ተቋማት በተጨማሪ የተለያዩ የሕዝብ አገልግሎት መሠረተ ልማቶች ላይ ውድመት መድረሱን ቀደም ሲል የወጡ ሪፖርቶች አመልክተዋል።

የበርካቶችን ህይወት በቀጠፈው በዚህ ጦርነት የህክምናና የትምህርት ተቋማት ክፉኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆኑ ሌሎች የመንግሥትና የግል ንብረቶች ላይ ዘረፋና ውድመት ተፈጽሞባቸዋል።

ለስምንት ወራት ትግራይ ውስጥ የተካሄደው ጦርነት በሰኔ ወር ማብቂያ አካባቢ የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ከትግራይ ክልል ካስወጣ በኋላ የህወሓት ኃይሎች ጦርነቱን ወደ አማራና አፋር ክልሎች በማስፋት ጥቃት ፈጽመዋል።

በዚህም በጦርነቱ ሳቢያ በትግራይ ክልል ውስጥ ከተፈናቀሉትና ለችግር ከተጋለጡት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በተጨማሪ በአፋርና በአማራ ክልል ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ተነግሯል።