የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብታዊ እመርታ ስጋት ላይ የጣለው ጦርነት

አንድ በመንገድ ላይ እቃዎችን የሚሸጥ ኢትዮጵያዊ ታዳጊ ሱዳን ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በርካቶች ጦርነቱን በመሸሽ ወደ ሱዳን ተሰደዋል
    • ፀሐፊ, በቪቪዬን ኑኒስ
    • የሥራ ድርሻ, የቢቢሲ ኒውስ የአፍሪካ ዘጋቢ

ባለፉት አስር ወራት የተደረገው ጦርነት ኢትዮጵያን ከፍተኛ ሰብዓዊ ኪሳራ ውስጥ ከቷታል። በሺዎች የሚቆጠሩ ተገድለዋል፤ ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል እንዲሁም ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው በርካቶች ናቸው።

ጦርነቱ በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ በሆነችው ኢትዮጵያ እያደረሰው ያለው ጉዳት ይህ ብቻ አይደለም። ከፍተኛ የሆነ ምጣኔ ሀብታዊ ወጪን አስከትሏል፤ ይህንንም ለመጠገን ዓመታት ሊወስድ ይችላል።

በመዲናዋ አዲስ አበባ ነዋሪ የሆነችውና ሙሉ ስሟ እንዳይጠቀስ የጠየቀችው የ26 ዓመቷ ትዕግስት ወርሃዊ ወጪዋ በሁለት ምክንያቶች በእጥፍ ጨምሯል ትላለች። እነዚህም በጥቅምት ወር ወር በሠሜናዊ ትግራይ ክልል የተቀሰቀሰው ጦርነት እና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ናቸው።

"ከኮቪድ-19 እና ከግጭቱ በፊት መሠረታዊ ሸቀጦችን ለመሸመት በየወሩ አንድ ሺህ ብር አወጣ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን ይህ ወጪ ተመንድጎ ሁለት ሺህ ብር ሆኗል" ትላለች።

አክላም "አሁን በርካታ ነገሮች ዋጋቸው የማይቀመስ ሆኗል ለምሳሌ - ስልኮች፣ ምግብ እና አልባሳት።"

ይፋዊ የሆነውን ስታቲስቲክስ በምንመለከትበትም ወቅት የመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ በእርግጥም በኢትዮጵያ ጨምሯል።

በዚህም ከአንድ ዓመት በፊት በሐምሌ ወር የነበረውና የዘንድሮው ዋጋ ሲነፃፀር በአማካይ ሩብ ያህል ውድ ሆኗል።

ትግስት ቤተሰቦቿን ለመደገፍ በትልቅ የገበያ መደብር (ሱፐርማርኬት) ውስጥ በገንዘብ ተቀባይነት ተቀጥራ ትሰራለች። ወንድሟ የቤት ኪራዩን የሚሸፍን ሲሆን የምግቡ ወጪ ደግሞ የእሷ ኃላፊነት ነው።

"የዶላር ምንዛሪ ጥሩ አይደለም ለምሳሌ ባለፈው ዓመት 1 ዶላር በ35 ብር ሲመነዘር የነበረ ሲሆን በአሁ ወቅት ግን የአንድ ዶላር ምንዛሬ ወደ 45 ብር አሻቅቧል" ትላለች።

የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ላይ ተንታኝ የሆኑትና መቀመጫቸውን በአሜሪካ ያደረጉት ፋይሰል ሮብሌ አገሪቷ በጦርነት ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰሷ "በእውነቱ ኢትዮጵያ ዶላር የማግኘት አቅሟ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል" እና የምንዛሪው ተመንም እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል ይላሉ።

ሴቶች መቀለ ውስጥ በሚገኝ ገበያ (መጋቢት ወር ላይ)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዋጋ ውድነት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል

ጦርነቱ አገሪቱን ምን ያህል እንዳስወጣ እስካሁን ግልፅ አይደለም ነገር ግን በትሬዲንግ ኢኮኖሚክስ ትንበያ መሰረት ወታደራዊ ወጪዋ በመጪው ታኅሣሥ ወር መጨረሻ ላይ ወደ 502 ሚሊዮን ዶላር ሊደርስ ይችላል ብሏል። በባለፈው ዓመት 460 ሚሊዮን ዶላር ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ባለፈው ሳምንት ጦርነቱ "ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ከአገሪቱ ካዝና አስወጥቷል" ብለዋል።

ከዓለም አቀፉ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እና ከጦርነቱ በፊት የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት በቀጠናው በፍጥነት በማደግ ላይ ከነበሩ አንዱ ነበር።

ከዓለም ባንክ የተገኘውም መረጃም አገሪቱ ከሁለት ዓመት በፊት በነበረው አስር ዓመታት ውስጥ እድገቷ በዓመት በአማካይ 10 በመቶ ነበር።

ትዕግስት የጠቀሰቸው በባንኮች የሚመነዘረውን የውጭ ምንዛሪ ሲሆን መደበኛ ባልሆነው ገበያ ውስጥ ግን የብር ዋጋ በእጅጉ አሽቆልቁሎ ወደ አንድ ዶላር 65 ብር እንደሚመነዘር ፋይሰል ተናግሯል።

ጨምሮም በአገሪቱ ያሉ የነጋዴዎች ጦርነቱ ከትግራይ ተሻግሮ ወደ አጎራባቾቹ የአፋርና የአማራ ክልሎች በመስፋፋቱ እያሽቆቆለ ያለው የደኅንነት ሁኔታ በእጅጉ ያሳስባቸዋል።

በርካቶቹም ከአካውንታቸው ገንዘባቸውን እያወጡ እራሷን ነጻ አገር አድርጋ ወዳወጀችው ሶማሌላንድ በማሻገር በመቀየር የብር የመግዛት አቅምን የበለጠ እንዲዳከም እያደረገው መሆኑን ፋይሳል ይገልጻል።

በትግራይ የባንኮች መዘጋት

የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ መክሰምና የምርጫ መራዘምን ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሚመራው አስተዳርና በህወሓት መካከል የነበረው አለመግባባት ተካሮ በነበረበት ጊዜ በፌደራሉ ወታደራዊ የጦር ሰፈር ላይ ትግራይ ውስጥ ጥቃት ሲሰነዘር ነበር ጦርነቱ የተቀሰቀሰው።

ከጥቅምት ወር ማብቂያ ጀምሮ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርታራ ወታደሮች፣ የክልል ልዩ ኃይልና ሚሊሻዎች ከትግራይ ኃይሎች ጋር ደም አፋሳሽ ጦርነት አካሂደዋል።

በዚህም ጊዜ አስገድዶ መድፈርና የሰላማዊ ሰዎች የጅምላ ግድያን ጨምሮ ጭፍጨፋዎችን በመፈጸም ሁሉም ወገኖች ሲከሰሱ ቆይተዋል።

ባለፈው ሰኔ ወር አማጺያኑ የክልሉን ዋና ከተማ መልሰው ከያዙ በኋላ በትግራይ ውስጥ የፌደራል መንግሥቱ የቴሌኮሚዩኒኬሽንና ባንኮችን አገልግሎቶችን ጨምሮ መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዲቋረጡ አድርጓል። ትግራይ ሙሉ በሙሉ ተዘግታለች።

በትግራይ ከ 400 ሺህ በላይ ሰዎች በረሃብ አፋፍ ላይ ናቸው። የእርዳታ ስርጭቱ በከፍተኛ ሁኔታ ተመናምኖ የኤሌክትሪክ እና የነዳጅ አቅርቦቶች ባለመኖሩም የሸቀጦች ዋጋ እንዲንር አድርጎታል።

ጦርነቱ ካስከተውለው ውድመት ውስጥ በከፊል

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ጦርነቱ ካስከተውለው ውድመት ውስጥ በከፊል

የመቀለ ነዋሪ የሆነው ፊልሞን ብርሃኔ ለቢቢሲ ትግርኛ እንደተናገረው ምግብና ኪራይ ሰሞኑን በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተናግሯል።

"ሁሉም ባንኮች ተዘግተው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ደመወዝ ስለማይከፍሉ ገንዘብ የለም" ይላል።

የቴሌኮም ጨረታ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ጦርነቱ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ባላት ስም ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እያሳደረ ነው ሲሉ የኤን.ኬ.ሲ የአፍሪካ ኢኮኖሚ አማካሪ ቡድን የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ኢርማጋርድ ኢራስመስ ይናገራሉ።

"ሸማቾ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ጫና ካጋጠማቸው በአሜሪካ ወይም በዩሮ ዞን እንደምናየው በሸማቾች የሚመራ ዕድገት አያዩም" ይላሉ።

"ይህም ማለት በአጠቃላይ የምጣኔ ሀብት እድገቱ የሚመራው በውጭ ኢንቨስትመንት ይሆናል፤ ነገር ግን ይህ ሁኔታም ባለው የኢትዮጵያ አሉታዊ ስም እየተጎዳ ነው" በማለት ይጠቅሳሉ።

ኢርማጋርድ በቅርቡ የደቡብ አፍሪካው የቴሌኮም ግዙፍ ኩባንያ ኤምቲኤንን ጨምሮ በርካታ አገልግሎት አቅራቢዎችን ፍላጎት የሳበውን የኢትዮጵያን የቴሌኮም ዘርፍ ፈቃድ ይጠቅሳሉ።

ምንም እንኳን በመጀመሪያ ዙር በርካታ ዓለም አቀፍና ስመ ጥር ኩባንያዎች ፍላጎት ቢያሳዩም በመጨረሻ ግን ለሁለት የቴሌኮም ፈቃድ የወጣው ጨረታ አንዱ ብቻ ነው የተሳካው። በዚህም በኬንያው ሳፋሪኮም የሚመራው ጥምረት 850 ሚሊዮን ዶላር በማቅረብ ማሸነፍ ችሏል።

የሞባይል ገንዘብ ሥርዓትን እንዳይሠሩ የሚገድቡ ሕጎች ከፈቃዱ ጋር በተያያዘ አሉታዊ ጫና ነበረባቸው ቢባልም የኩባንያዎቹ ፍላጎት የቀነሰው ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ እንደሆነ የኢንዱስትሪው ምንጮች ያስረዳሉ።

በቅርቡ በተካሄደ ሰልፍ ከተሳተፉ መካከል

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, መንግሥት የሚያካሂደውን ዘመቻ በመደገፍ ሰልፍ ተካሂዷል

ጦርነቱ እንዲቆም እየተደረገ ያለ ጫና

የኢትዮጵያ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ባለፈው ዓመት በ2020 ከነበረበት 6 በመቶ በዚህ የአውሮፓውያን ዓመት በ2021 ሁለት በመቶ ብቻ እንደሚያድግ ተገምቷል።

ይህም በሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ ከታየው በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ የአይኤምኤፍ መረጃ ያሳያል።

አገሪቱ በዓመት ወደ 14 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ እቃዎችን ከውጭ የምታስገባ ሲሆን 3.4 ቢሊዮን ዶላር ብቻ የሚያወጣ ምርቶችን ወደ ውጪ ትልካለች።

ከዚህም በተጨማሪ የአገሪቱ ብሔራዊ ዕዳ በዚህ ዓመት 60 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) 70 በመቶ ይደርሳል ከመባሉ ጋር ተያይዞ በርካታ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የሚያሳስብ ነው ይላሉ።

"ይህ ዝቅ ተደርጎ በተደረገ ግምገማ የቀረበ ግምት ነው" ያሉት ባለለሙያዋ "የኢትዮጵያ ወታደራዊ ወጪ ከተገመተው በላይ ሊሆን ይችላል እና ቀደም ሲል ሪፖርት ያልተደረገ ዕዳም አለበት" ይላሉ።

አሜሪካ በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ ኢትዮጵያውያን ባለስልጣናት ላይ አንዳንድ የቪዛ ገደቦችን ስትጥል እና የተወሰነ ድጋፍን ብትከለክልም፣ እስካሁን ድረስ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በመንግሥት ላይ ከፍተኛውን የኢኮኖሚ ጫና ለማሳረፍ ወይም ከፍተኛ የእርዳታ ፕሮግራሞችን ለመቋረጥ ፈቃደኛ አይደለም።

በአገሪቱ ሩብ ገደማ የሚሆነው ሕዝብ ከብሔራዊ የድህነት ወለል በታች የሚኖር ሲሆን አማካይ ዓመታዊ ገቢ በአንድ ሰው 850 ዶላር ብቻ ነው።

"ከሁለት ዓመታት በፊት የኖቤል የሰላም ሽልማትን ያሸነፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ግጭቱን ማስቆም ካልቻሉ ማዕቀቡን የማስፋት ሁኔታ እንዳለም" በዋሽንግተን የቲንክ ታንክ ፌሎው ዊትኒ ሽኔይድማን ይናገራሉ።

የባይደን አስተዳደር አጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ የገባው ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ከዓለም ሳትገለል ጦርነቱ እንዲቆም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ላይ በቂ ጫና ማሳደር ነው ይላሉ።

"ሁሉም አማራጮች ጠረጴዛው ላይ ናቸው። ነገርን በአገሪቷ ከ110 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አለ። ከዚያም በተጨማሪ አገሪቷ ጠቃሚ፣ አስፈላጊ እንዲሁም በጣሙን ስትራቴጂካዊ ናት" ይላሉ።