የቦይንግ ዳይሬክተሮች ከ737 ማክስ አውሮፕላን አደጋ ጋር በተያያዘ ምርመራ ሊደረግባቸው ነው

አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካው አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ የቦርድ ዳይሬክተሮች ከ737 ማክስ አውሮፕላን ጋር በተያያዘ ክስ ሊመሰረትባቸው እንደሚገባ አንድ ዳኛ ወስነዋል።

ዳኛ ሞርጋን ዘርን እንዳሉት አውሮፕላኖቹ ከደኅንነት ሥርዓት ጋር በተያያዘ ስጋት እንዳለባቸው ቢገለጽም የቦርድ አባላቱ ግን ይህንን እውነታ ችላ ብለውታል።

በዚህ ስህተት ዋነኞቹ ተጎጂዎች አውሮፕላኖቹ ባጋጠማቸው አደጋ ሕይወታቸው ያለፈው ሰዎችና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ናቸው ያሉት ዳኛው፤ በተጨማሪ ደግሞ በቢሊየኖች የሚቆጠር ዶላር ለኪሳራ እንዲጋለጥ አድርጓል ሲሉ አክለዋል።

ብይኑን ያስተላለፉት ዳኛው "በቦይንግ ድርሻ ያላቸው ባለሀብቶች ወደዚህ ፍርድ ቤት ቀርበው የቦይንግ የቦርድ ዳይሬክተሮች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዳልተወጡ እና የአውሮፕላኑን የደኅንነት ስጋት በቸልታ ማለፋቸው ደግሞ የእነሱ ድርሻ ላይ ጫና ስለማሳደሩ ቅሬታቸውን ገልጸዋል" ብለዋል።

በአውሮፓውያኑ 2018 እና 2019 ላይ የኢንዶኔዢያ እና የኢትዮጵያ ንብረት የሆኑ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ባጋጠማቸው ችግር ተከስክሰው በውስጥ የነበሩ ሁሉም 346 ተሳፋሪዎች ሕይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ነው።

በዚህም ምክንያት 737 ማክስ አውሮፕላኖች ከበረራ እንዲታገዱ ሆኗል።

ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ ከተከሰከሱት 737 ማክስ አውሮፕላኖች ጋር በተያያዘ ቦይንግ የአውሮፕላኖችን የዲዛይን መረጃ ሆነ ብሎ በመደበቁ 2.5 ቢሊየን ዶላር ካሳ ሊከፍል እንደሆነ ተለግጾ ነበር።

የአሜሪካ ፍትሕ መሥሪያ ቤት ቦይንግ ከግልፅነት ይልቅ ትርፍን አስቀድሟል በማለት ቦይንግን ላይ ክስ ያቀረበ ሲሆን፤ በርካቶችን ለሞት የዳረጉት 737 ማክስ አውሮፕላኖች ላይ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር አላደረገም ብሏል።

ከ2.5 ቢሊየን ዶላሩ መካከል 500 ሚሊየን ዶላሩ በ737 ማክስ አውሮፕላን አደጋዎች ሕይወታቸውን ላጡ መንገደኛ ቤተሰቦች የሚከፈል ካሳ ሲሆን፤ 1.7 ቢሊየን ዶላሩ ደግሞ ለቦይንግ ኩባንያ አየር መንገዶች የሚከፈል ነው።

ነገር ግን አሁንም ቢሆን ቦይንግ ከተጎጂ ቤተሰቦች ክስ እየቀረበበት ነው። በርካቶችም ጉዳያቸውን ወደ ፍርድ ቤት ወስደው ቦይንግን እየጠየቁ ነው።

የአሜሪካው ዳኛ ሞርጋን ዘርን ውሳኔያቸውን ካስተላለፉ በኋላ የቦይንግ ቃል አቀባይ በፍጥነት ማስተባበያ ሰጥተዋል። "ፍርድ ቤቱ በወሰነው ውሳኔ በእጅጉ አዝነናል" ብለዋል።

"የቀረበውን ሐሳብ በጥልቀት ከመረመርን በኋላ በሚቀጥሉት ቀናት ምን አይነት እርምጃ እንደምንወስድ አማራጮችን እንመለከታለን።"

የ737 ማክስ አውሮፕላኖች መከስከስ እስካሁን ድረስ ቦይንግ 20 ቢሊየን ዶላር እንዲከስር አድርጎታል።