የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የሰሞኑ ውይይትና የምሥራቅ አፍሪካ ጉብኝት

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ እና ፕሬዝደንት ሙሴቪኒ

የፎቶው ባለመብት, @KagutaMuseveni

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ እና ፕሬዝደንት ሙሴቪኒ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ጉልህ የሆኑ ጉብኝቶችና ወደ ተለያዩ አገራት በመጓዝ ያደረጉ ሲሆን ከተለያዩ አገራት መሪዎች ጋርም በስልክ ተወያይተዋል።

ይህ የጠቅላይ የሚኒስትሩ ጉብኝትና ውይይት ባለፉት ወራት ውስጥ ከተካሄዱት በተለየ ተከታታይና ኢትዮጵያ በምትገኝበት አካባቢ ከፍ ያለ ሚና ካላቸው አገራት መሪዎች ጋር ውይይት የተደረገበት ነው።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ለሁለት ቀናት በምሥራቅ አፍሪካ አገራት ያደረጉት የሥራ ጉብኝት ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 24/2013 ዓ.ም ተጠናቆ ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን ጽህፈት ቤታቸው አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ወደ ኡጋንዳ እና ሩዋንዳ ተጉዘው ከየአገራቱ ፕሬዝደንቶች ጋር ተገናኝተው ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ እሁድ ዕለት በጀመሩት ጉዞ የመጀመሪያ መዳረሻቸውን አድርገው የነበረው ኡጋንዳ ኢንቴቤ ነበር።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ካምፓላ በደረሱ ወቅትም ደማቅ አቀባበል እንደተደረገላቸው ገልጸው፤ ከኡጋንዳው ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ጋር "በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት" ማድረጋቸውን በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው ላይ አስፈረዋል።

ፕሬዝደንት ሙሴቬኒም በትዊተር ገጻቸው ላይ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጋር በሁለትዮሽ፣ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ገልጸው፤ ያደረጉት ውይይት ውጤታማ መሆኑን በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፈረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ከኡጋንዳ በመቀጠል ወደ ሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ ተጉዘው ከፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ ጋርም ተገናኝተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በሩዋንዳ ቆይታቸው ከፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ጋር "የጋራ ጠቀሜታ ባላቸው የሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መልካም ውይይት አካሂደናል" ብለዋል።

በተመሳሳይ የፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ ጽህፈት ቤት ጠቅላይ ሚንስትሩ እና ፕሬዝደንቱ የሁለቱ አገራትን ጉዳዮች የተመለከቱትን ጨምሮ በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል ብሏል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ እና ፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ

የፎቶው ባለመብት, @UrugwiroVillage

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ እና ፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ

የጠቅላይ ሚንትሩ ሰሞነኛ ውይይቶች

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ወደ ኡጋንዳ እና ሩዋንዳ ተጉዘው ከየአገራቱ መሪዎች ጋር ከመወያየታቸው ከአራት ቀናት ቀደም ብለው ከደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ጋር አዲስ አበባ ላይ ተገናኝተው ተወያይተው ነበር።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ከፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ጋር "በመሠረተ ልማት ግንባታ አማካኝነት የኢኮኖሚ ትስስር የመፍጠርን አስፈላጊነት አንስተናል" ካሉ በኋሉ "እንደየ ሁኔታው የማይለዋወጡና በወዳጅነታቸው የሚጸኑ እንደ ደቡብ ሱዳን ያሉ ወዳጆች በወሳኝ ጊዜያት እጅግ አስፈላጊ ናቸው" ሲሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

ሰኞ ነሐሴ 17/2013 ዓ.ም ጠቅላይ ሚንስትሩ ከአዲሱ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ጋር በስልክ መወያየታቸውንም አስታውቀው ነበር።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ከእስራኤል አቻቸው ናፍቲ ቤኔት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን እና የሁለቱን አገራት ትብብር ለማጠናከር ተነጋግረናል ብለዋል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ አገራት ከመጓዛቸው በፊት ከሳዑዲ አረቢያው ልዑል ሞሐመድ ቢን ሳልማን ቢን አብዱልአዚዝ ጋር በስልክ መወያየታቸው በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን የተዘገበ ቢሆንም በምን ጉዳይ ላይ እንደተነጋገሩ የተሰጠ ማብራሪያ የለም።

ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቱርክ ጉብኝት አድርገው ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ጋር የተነጋገሩ ሲሆን፤ ሁለቱ አገራት ወታደራዊን ጨምሮ የተለያዩ የትብብር ስምምነቶች መፈራረማቸው መገለጹ አይዘነጋም።