መኪና ውስጥ ተደብቃ ከታሊባን ያመለጠችው ወጣቷ ከንቲባ

ለዛሪፋ ገፋሪ

ካቡል በታሊባን ቁጥጥር ስር መውደቋን ተከትሎ ከአፍጋኒስታን የመጀመሪያ ሴት ከንቲባዎች መካከል አንዷ የሆነችው ዛሪፋ ጋፋሪ ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ወደቀች።

የታሊባኖች ከ20 ዓመታት በኋላ ወደ መዲናዋ ካቡልን ሲከቡ የከንቲባዋ ህይወት በድንገት ከባድ አደጋ ላይ እንደወደቀ ስለተገነዘበች ሊያጋጥማት የሚችለውን ችግር ለማምለጥ እርምጃ ወሰደች።

ከቀናት በኋላ ከቤተሰቦቿ ጋር ሆና ወደ ጀርመን ሸሸች እናም በአስደናቂ ሁኔታ እንዴት እንዳመለጠች፤ ይህንን ታሪኳን ለቢቢሲ አካፍላለች።

የ29 ዓመቷ ዛሪፋ በአፍጋኒስታን ውስጥ በሕዝቡ ዘንድ በከፍተኛ ዕውቅናን ያተረፈች እንዲሁም ለሴቶች መብት ከሚታገሉና ድምፅ ከሆኑት መካከል ስሟ ይጠራል።

የእስልምና አስተምህሮትን እንከተላለን ለሚሉትና በዚያም ትርጓሜ የሴቶችን ሚና በመገደብ ለሚታወቁት ታሊባኖች እንደ ስጋት እንደሚያዩዋት ታምናለች።

ዛሪፋ "ድምፄ የትኛውም ጠመንጃ የሌለውን ያህል ኃይል አለው" ትላለች።

ታሊባን በርካታ ግዛቶችን እየተቆጣጠረ ባለበት ወቅት ዛሪፋ ለህይወቷ ብትሰጋም በእምቢተኝነትና በፅናት እንደምትታገል ታስብ ነበር። ነገር ግን ያ ብሩህ ተስፋዋ ወዲያው ነው የመነመነው።

ዛሪፋ ጋፋሪ

የፎቶው ባለመብት, Zarifa Ghafari

ታሊባን አፍጋኒስታንን በቁጥጥሩ ስር ማድረጉን ተከትሎ በርካቶች ለህይወቷ በመስጋት ከቤቷ ለቃ እንድትወጣ ጠየቋት።

ዛሪፋ ስጋት ቢኖርባትም ቤቷን የሚያስለቅቅ እንደሆነ አላሰበችም ነበር። ነገር ግን የታሊባን ተዋጊዎች ቤቷ መምጣት ብቻም ሳይሆን የጥበቃ ሠራተኛዋን ሲደበድቡት ሁኔታው ሌላ መልክ እንደያዘ ተረዳች።

የዛሪፋ የደኅንነት ጥያቄ በአሁኑ ወቅት የተነሳ ብቻ ሳይሆን በቅርብ ዓመታትም በርካታ ነገሮች ገጥመዋታል። በተለይም ታሊባኖች ሰፊ ድጋፍ ባላቸውና በርካታ ወግ አጥባቂዎች የሚኖሩባት ማይዳን ሻር ከንቲባ መሆኗን ተከትሎ ከአውሮፓውያኑ 2018 ጀምሮ ተደጋጋሚ የግድያ ሙከራዎች ተቃጥቶባታል።

ዛሪፋ ጋፋሪ ከተማዋን ለማስተዳደር ከንቲባ ሆና ተሾመችው በ26 ዓመት ዕድሜዋ ነበር።

ለእሷ የተቃጣው የግድያ ሙከራም አባቷ ባለፈው ዓመት እንዲገደሉ ምክንያት ሆኗል። አባቷ የአፍጋኒስታን ጦር ሠራዊት ከፍተኛ አባል ሲሆኑ ዛሪፋ በታሊባን ውስጥ ጠላቶች እንደነበሯቸው ትጠረጥራለች።ሰኔ 14 ምርጫ ባልተካሄደባቸው ስፍራዎች መስከረም 20 ምርጫ እንዲካሄድ ተወሰነ

ታሊባን መዲናዋን ካቡልን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ዛሪፋ ከአገሪቷ መውጣት እንዳለባት ወሰነች።

ዛሪፋ ጋፋሪ

የፎቶው ባለመብት, Zarifa Ghafari

ዛሪፋ ከተደቀነባት አደጋ ለማምለጥ ነሐሴ 12/2013 ዓ.ም እሷን እና ቤተሰቦቿን ወደ ካቡል አውሮፕላን ማረፊያ የሚወስድ መኪና አመቻቸች።

ወደ አውሮፕላን ማረፊያ በሚደረገውም ጉዞ ቀላል አልነበረም። መኪናው ውስጥ ራሷን ዝቅ በማድረግም የእግር ማሳረፊያ ላይ ተደብቃ ነበር የተጓዘችው። መተንፈስ ስትፈልግ ቀና ብትልም በርካታ የታሊባን ኬላ በመኖሩ ራሷን መደበቅ ነበረባት።

"የአየር ማረፊያው በር ስንደርስ በሁሉም ቦታ የታሊባን ተዋጊዎች ነበሩ። ራሴን ለመደበቅና ላለማሳወቅ እየተጋልኩ ነበር" ትላለች።

ዛሪፋ ጋፋሪ

የፎቶው ባለመብት, Zarifa Ghafari

የምስሉ መግለጫ, ዛሪፋ ጋፋሪ በዚህ መልኩ ነው ተደብቃ የወጣችው

በአውሮፕላን ማረፊያው ውስጥም በካቡል የሚገኘው የቱርክ አምባሳደር ያገዟት ሲሆን ወደ ኢስታንቡል እንድትበርም በቀላሉ አመቻቹላት። ከዚያም ከኢስታንቡል ተነስታ ወደ ጀርመን ገባች።

"አባቴን ባጣሁበት ወቅት በህይወቴ እንዲህ አይነት ጥልቅ ሐዘን የሚሰማኝ አልመሰለኝም ነበር። ነገር ግን አገሬን ለቅቄ በአውሮፕላኑ ውስጥ ስገባ አባቴን ከማጣት የበለጠ አሳዛኝ ነበር" ትላለች።

ካቡል በታሊባን ቁጥጥር ስር መሆን "በሕይወቴ ውስጥ በጣም መጥፎ ጊዜ ነው" በማለት ታስረዳለች።

አክላም "በውስጤ የሚሰማኝን ሐዘንና ህመም በጭራሽ መቆጣጠር አልችልም። አገሬን ለቅቄ በጭራሽ ለመውጣት አላሰብኩም ነበር" ብላለች።

በአሁኑ ወቅት ደኅንነቷ በተጠበቀው የጀርመኗ ዱሰልዶርፍ ከተማ የምትገኝ ስትሆን፤ ዛሪፋም በካቡል አውሮፕላን ማረፊያ በርካቶች ለመውጣት ሲያደርጉት የነበረው ግርግርና ቀውስ አደገኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንዲህ በሰላም በመውጣቷ እድለኛ መሆኗን ታምናለች።

ምንም እንኳን ከአገሯ ሩቅ ብትሆንም በታሊባን አገዛዝ ሥር ለሚኖሩ አፍጋኒስታናውያን ትኩረት ለመሳብ ከፖለቲከኞች እና ከዓለም መሪዎች ጋር ለመገናኘት ቃል ገብታለች።

ከዚህም በተጨማሪ ከታሊባን ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆኗንም አስታውቃለች፤ ምክንያቱም "እርስ በርስ መረዳዳት ስላለብን ነው" ትላለች።

"የውጭ ኃይሎች እኛን ለመርዳት አይመጡም። ከታሊባን ጋር ያለውን ጉዳይ መፍታት የእኛ ነው ። ይህንን ኃላፊነት ለመውሰድ ዝግጁ ነኝ" በማለት ታክላለች።

ዛሪፋ ጋፋሪ

የፎቶው ባለመብት, Zarifa Ghafari

ሆኖም ታሊባንን አታምናቸውም በተለይም የሴቶችን መብት ያከብራል ብላ በጭራሽ አታምንም።

ከአውሮፓውያኑ 2001 በፊት ታሊባኖች ሥልጣን በተቆጣጠሩበት ወቅት ሴቶችን ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ ወይም እንዳይሠሩ የሚከለክለውን እጅግ በጣም ወግ አጥባቂ የሆነውን የእስልምና ሕግን ተግባራዊ አደረጉ።

ባለፈው ሳምንትም እንዲሁ የታሊባን ቃል አቀባይ ዛቢሁላህ ሙጃሂድ ሴቶች "በማኅበረሰቡ ውስጥ በጣም ንቁ ተሳታፊ ይሆናሉ ነገር ግን በእስልምና ማዕቀፍ ውስጥ በሆነ መንገድ ነው" በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ነገር ግን ዛሪፋ ይህንንም ቢሆን አትቀበለውም የሚሉትን ተግባራዊ ያደርጋሉ ለሚለው ከፍተኛ ጥርጣሬ አላት "ቃሎቻቸው ከድርጊታቸው ጋር ፈጽሞ አይዛመዱም" በማለትም ታስረዳለች።

በአገሯ ያለው የደኅንነት ሁኔታ በተወሰነ መልኩ ሰላም ከሆነም አንድ ቀን አፍጋኒስታን እንደምትመለስ ተስፋ አድርጋለች።

"አፍጋኒስታን አገሬ ናት ፤ የሰራኋትና አስተዋፅኦ ያደረግኩባት አገር ናት። ለማሸነፍ ለዓመታት ታግያለሁ" በማለትም ለአፍጋኒስታን ያላትን ስሜት ታስረዳለች።

"ከአገሬ ስወጣ የወሰድኩትን አሸዋ እንደገና ስመለስ ወደ አገሬ ወደነበረበት ስፍራ መመለስ እፈልጋለሁ" ብላለች።