ኩባ በህዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት ለአነስተኛ እና መካከለኛ የግል ንግዶች ፍቃድ ሰጠች

ኩባ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ግለሰቦች ለሚያስተዳድሯቸው አነስተኛና መካከለኛ ንግዶች ለአመታት ፍቃድ ከልክላ የነበረችው ኩባ ባለፈው ወር በተካሄደው ሕዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት ይህንን ህግ ሽራለች።

የኩባ ኮሚኒስት መንግሥት ሕዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ አነስተኛና መካከለኛ የግል ንግዶችን ሕጋዊ እንዲሆኑ አድርጓል። በአዲሱ ህግ መሰረት እስከ 100 ሰራተኞች ያሉት የንግድ ድርጅቶችን ግለሰቦች እንዲያቋቁሙ ተፈቅዷል።

የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሚጌል ዲአዝ-ካኔል ኩባ የኢኮኖሚ ሞዴሏን ለማዘመን ጠንካራ እርምጃዎችን እየወሰደች ነው ብለዋል።

ሆኖም ሺዎች የኢኮኖሚውን ሁኔታ በተመለከተ አደባባይ መውጣታቸው መንግስት እዚህ ውሳኔ ላይ በፍጥነት እንዲደርስ ምክንያት ነው የሚሉ አስተያየቶች ተደምጠዋል።

ሰልፈኞቹ የሀገሪቱ መንግስት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን የያዘበትን መንገድ ያወገዙ ሲሆን የፖለቲካ ለውጥ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

ሀገሪቱ በኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ባለችበት ጊዜ በተነሳው በዚህ ተቃውሞው ምክንያት በአገር አቀፍ ደረጃ በርካቶች ለእስር የተዳረጉ ሲሆን ባስከተለው አለመረጋጋት ቢያንስ አንድ ሰው መሞቱ ተዘግቧል።

ታዲያ ባለፈው አርብ አነስተኛና መካከለኛ ንግድን በተመለከተ መንግስት ያሳለፈው ውሳኔ በሀገሪቱ የተደረገ ትልቅ የፖሊሲ ለውጥ ነው ተብሏል።

ኢኮኖሚዋ እየላሸቀ ነው የምትባለው ኩባ በሐምሌ ወር ባለሥልጣናቱ ወደ አገሪቱ የሚመጡ ተጓዦች ግብር መክፈል ሳይጠበቅባቸው ምግብ ፣ መድኃኒት እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን እንዲያመጡ ፍቅዳለች።

በሀገሪቱ አለ የሚባለውን የመድኃኒት እና የምግብ እጥረትን ለማቃለል አንዳንድ ኩባንያዎች ከውጭ የሚያስገቡበትን ግብር እስከመሻር ደርሳለች።

ለኩባ ኢኮኖሚ ወሳኝ ከሆኑት ዘርፎች አንዱ የሆነው ቱሪዝም በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት በዓለም አቀፍ የጉዞ ገደቦች ምክንያት ክፉኛ ተጎድተውባታል።

የስኳር ምርትን ወደ ውጭ መላክ ሌላኛው የኩባ ቁልፍ ገቢ ነው። ሆኖም የዘንድሮው ምርት ግን ከተጠበቀው እጅግ የወረደ ሆኗል።

የዚህም ድምር የመንግስት የውጭ ምንዛሪ ክምችት እንዲሞጠጥ ምክንያት በመሆኑ እጥረትን ለማሟላት ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎችን መግዛት ለሀገሪቱ ፈተና ሆኗል።

ኩባ በቅርቡ ለተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞው እና ለሰፊ ችግሮቿ አሜሪካን እና የጣለችባትን የኢኮኖሚ ማዕቀቦ ዋነኛ ምክንያት አድርጋ ትከሳለች።