ታሊባን በሁለት ቀናት ውስጥ ሁለተኛዋን የክልል ዋና ከተማ ተቆጣጠረ

የአፍጋን የፀጥታ ኃይሎች

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታሊባን በሰሜናዊ አፍጋኒስታን ጃውዝጃን ግዛት ውስጥ የምትገኘውን የሸበርጋን ከተማ ተቆጣጥሬያለሁ አለ።

የአፍጋኒስታን የመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በበኩላቸው ለቢቢሲ የመንግሥት ኃይሎች አሁንም በከተማው ውስጥ እንደሆኑ እና ታሊባንን "በቅርቡ" እንደሚያስወጡ ተናግረዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኒምሮዝ ግዛት ውስጥ ዛራንጅ የተባለችው ሌላኛዋ ከተማ በታሊባን ቁጥጥር ስር ከገባ በኋላ ይህ በታጣቂዎቹ የተያዘች ሁለተኛዋ የክልል ዋና ከተማ ናት።

ከፍተኛ ውጊያዎች እየተካሄዱባት ባለው አፍጋኒስታን ለመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ከፍተኛ ሽንፈት ነው ተብሏል።

በሰሜን በኩንዱዝ እና በደቡብ ላሽካር ጋህ ከባድ ውጊያዎችም እንዳሉ ሪፖርት ተደርጓል።

ለሁለት አስርት አመታት ውስጥ የቆየውን የአሜሪካና አለም አቀፍ ጥምር ኃይሎች ወታደሮቻቸውን ከአገሪቱ ማውጣት ከጀመሩ በኋላ በመላው አፍጋኒስታን ውጊያው ተባብሷል።

የታሊባን ታጣቂዎች ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የገጠር ግዛቶችን በመቆጣጠር ፈጣን በሆነ ሁኔታ እየገሰገሱ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ቁልፍ በሆኑ ከተሞች ላይ አነጣጥረዋል።

ሸበርጋን የአፍጋን ምክትል ፕሬዚዳንትና ጦር መሪ አብዱል ረሺድ ዶስት ቁልፍ ስፍራ ናት የምትባል ሲሆን ደጋፊዎቻቸውም የታሊባንን ታጣቂዎች እየተዋጉ ነበር።

የአፍጋኒስታን ወታደሮችን ለመርዳት 150 ሰዎች ወደ ከተማው መሄዳቸውን የአካባቢው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የአፍጋኒስታን የፀጥታ ኃይሎች እንደገና ከመወሰዳቸው በፊት ታሊባኖች በመጀመሪያ የገዢውን ግቢ በቁጥጥር ስር ያዋሉት አርብ ዕለት ነበር።

ሆኖም የክልሉ ምክር ቤት ኃላፊ አቶ ባቡር እሽቺ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ታጣቂዎቹ ከአንድ የጦር ሰፈር በስተቀር ከተማዋን በሙሉ ተቆጣጥረውታል። ነገር ግን አሁንም ውጊያው ቀጥሏል ተብሏል።

የአፍጋኒስታን የመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፋዋድ አማን ለቢቢሲ የመንግሥት ኃይሎች አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ አሁንም በከተማው "አብዛኛው" ውስጥ እንደሆኑ እና ሸበርጋን "ከአሸባሪዎች በቅርቡ ነፃ እንደምትሆን" ተናግረዋል።