አሜሪካ እና ዩኬ የእስራኤልን መርከብ ያጠቃችው ኢራን ናት ሲሉ ወቀሱ

አሜሪካ እና ዩኬ የእስራኤልን መርከብ ያጠቃችው ኢራን ናት ሲሉ ወቀሱ

የፎቶው ባለመብት, JOHAN VICTOR VIA REUTERS

አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ሁለት ሰዎች ከሞቱበት የነዳጅ ጫኝ መርከብ ጥቃት ጀርባ ኢራን አለችበት፤ ይህ ደግሞ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ነው ሲሉ ከሰሱ።

ኤምቪ ሜርሴር ስትሪት የተሰኘችው የእስራኤል ንብረት የሆነች መርከብ ኦማን አቅራቢያ ጥቃት የደረሰባት ባለፈው ሐሙስ ነበር።

አንድ የብሪታኒያ ዜግነት ያለው ሰውና አንድ ሮማኒያዊ በጥቃቱ ሕይወታቸው አልፏል።

ሁለቱ አገራት መግለጫ ያወጡት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት የረዥም ጊዜ ጠላታቸው ኢራን እጅ እንዳለበት "ማስረጃ" አለን ካሉ በኋላ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለው "ለኢራን ምላሽ የምንሰጥበት የራሳችን መላ አለን" ሲሉ ቴህራን "ወቀሳው ውሃ አያነሳም" ስትል አስተባብላለች።

ኤምቪ ሜርሴር ስትሪት ላይ የደረሰው ጥቃት በኢራን እና እስራኤል መካከል ያለው ግጭት እየተባባሰ መምጣቱን የሚጠቁም ነው ተብሏል።

ከባለፈው መጋቢት ጀምሮ በእስራኤልና ኢራን መርከቦች ላይ በርካታ ጥቃቶች እየተሰነዘሩ ሲሆን የተጎጂዎች ቁጥር ደግሞ ክጥቃቱ አንፃር አነስተኛ ነው።

ይህ መሆኑ አገራቱ ያልታወጀ "ምስጢራዊ ጦርነት" ውስጥ እንደገቡ ያሳያል ይላሉ ተንታኞች።

ኢራን በበኩሏ እስራኤል የኒውክሌር መሣሪያ ማብላያ ጣቢያዎችንና ሳይንቲስቶችን ዒላማ አድርጋለች ስትል ትወቅሳለች።

እሁድ ዕለት መግለጫ የለቀቁት የዩኬው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒኪ ራብ፤ ኢራን አንድ ወይም ከዚያ በላይ ሰው አልባ አውሮፕላን [ድሮን] ተጠቅማለች ብለዋል።

ሚኒስትሩ፤ ይህ "ታቅዶ፣ ዒላማ ተደርጎ ስለተከናወነ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ነው" ብለዋል።

"ኢራን መሰል ጥቃቶችን ማቆም አለባት፤ መርከቦች እንደፈቃዳቸው በነፃነት ሊንቀሳቀሱ ይገባል" ሲሉ አክለዋል።

የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን በበኩላቸው "ኢራን ከጥቃቱ ጀርባ ስለመሆኗ እርግጠኛ ነን" ካሉ በኋላ "አስፈላጊ ምላሽ እንሰጣለን" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ኢራን ከባድ ስህተት መፈፀሟን እንዲያውቅ ያስፈልጋል ብለዋል።

ኢራን በምላሹ እስካሁን ይህ ግባ የሚባል ያለችው ነገር የለም።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ ሳዒድ ካቲብዛዴህ "ፅዮናዊው አገዛዝ [እስራኤል] ፍርሃት፣ ሽብርና ብጥብጥ ፈጥሯል" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

አክለው እስራኤል "ውሃ የማያነሱ ወቀሳዎችን ልታቆም ይገባል፤ ሁሉም የዘራውን ነው የሚያጭደው" ብለዋል።

በኢራንና በምዕራባዊያን አገራት መካከል ያለው ውጥረት ከፍ ያለው ቪዬና ውስጥ የተካሄደው የኒውክሌር ውይይት ፍሬ አልባ መሆኑን ተከትሎ ነው።

ሃያላን የሚባሉት አገራት በፈረንጆቹ 2015 ኢራን ኒውክሌር ማብላላት አቁማ በምትኩ የተጣለባት ማዕቀብ እንዲነሳላት የገባችውን ስምምነት እንደገና ተግባራዊ እንድታደርግ ይሻሉ።

ምዕራባዊያን አገራት ኢራን ኒውክሌር የጦር መሣሪያ እያበለፀገች ነው ሲሉ ይከሳሉ። ኢራን ደግሞ የኒውክሌር ፕሮግራሙ ለጥናት እና ኃይል ማመንጨት ነው ትላለች።