የዓለማችን ቱጃር ወደ ጨረቃ ለመጓዝ 2 ቢሊዮን ዶላር ልክፈል እያለ ነው

የፎቶው ባለመብት, Blue Origin
የዓለማችን ልጥጡ ሃብታም ጄፍ ቤዞስ ወደ ጨረቃ የሚደረገውን ጉዞ ለመቆጣጠር ለናሳ ሁሉት ቢሊዮን ዶላር ለመክፈል ማቀዱ ተሰምቷል።
ቤዞስ ዶላሩን መዥርጦ ካልሰጠሁ ያለው ወደ ጨረቃ የምትጓዘውን መንኩራኩር ለመሥራት ናሳ ኮንትራት እንዲሰጠው በማሰብ ነው።
ባለፈው ሚያዚያ ናሳ ከጄፍ ቤዞስ የቀረበለትን ጥያቄ ወዲያ ብሎ ከኢላን መስክ ጋር የ2 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት መድረሱ አይዘነጋም።
ወደ ጨረቃ የምትጓዘው የሰማይ ሰማያት መኪና ጠፈርተኞችን ይዛ በፈረንጆቹ 2024 ጉዞዋን ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል።
የአሜሪካው ጠፈር ምርምር ተቋም ናሳ ከዚህ በፊት እንዳቀደው ሥራውን ለሁለት ኩባንያ ሳይሆን ለአንድ ኩባንያ ብቻ ሳይሰጥ አቀይርም እየተባለ ነው።
ተቋሙ የአሜሪካ ኮንግረስ ጨረቃ ላይ የማርፍበት 3.3 ቢሊዮን ዶላር ይስጠኝ ብሎ ቢጠይቅም እስካሁን ማግኘት የቻለው 850 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው።
ለናሳ አስተዳዳሪ ቢል ኔልሰን ደብዳደቤ የፃፈው ቤዞስ "ተቋሜ ብሉ ኦሪጂን ወደ ጨረቃ የሚደረገውን ጉዞ ለማገዝ እስከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ድረስ ለማዋጣት ፈቃደኛ ነው" ብሏል።
ናሳ ወደ ጨረቃ ሊያደርግ ያሰበው ጉዞ በበጀት እጥረት ምክንያት የተንቀራፈፈበት ይመስላል።
ለዚህም ነው ጨረታ ባወጣ ወቅት ዝቅተኛ ገንዘብ ላስገባው የኢላን መስክ ስፔሴክስ ድርጅት ሥራውን የሰጠው።
በውሳኔው መሠረት የኢላን መስክ ድርጅት ስፔሴክስ የሚያመርተው መንኩራኩር ጠፈርተኞችን ይዞ ወደ ጨረቃ ይጓዛል።
የናሳ ዕቅድ ከተሳካ በፈረንጆቹ 1972 ወደ ጨረቃ ከተጓዘችው አፖሎ 17 መንኩራኩር በመቀጠል ሁለተኛው ወደ ጨረቃ የተደረገ የናሳ ጉዞ ይሆናል ማለት ነው።
ወደ ጨረቃ የሚደረገውን ጉዞ ለመቀላቀል ጨረታውን ከተቀላቀሉ መካከል አላባማ የሚገኘው ዳይኔቲክስ የተሰኘው ተቋምም ይገኝበታል።
ነገር ግን ቤዞስም ቢሆን ብቻውን አይደለም ጨረታውን የተቀላቀለው። ጉምቱው የገንዘብ ባለፀጋ ከሌሎች ሶስት የጠፈር ምርምር ተቋማት ጋር በማበር ነው ወደ ፉክክሩ የገባው።
ብሉ ሙን ላንደር የተሰኘው ማሽን በ1969 ኒል አርምስትሮንግ እና ባዝ አልድሪን የተጓዙበትን መንኩራኩር ዓይነት ቅርፅ እንዲመስል ተደርጎ እንደሚሠራ ተሰምቷል።
ቤዞስ ለናሳ በላከው ደብዳቤ "ለ21ኛው ክፍለዘመን የሚመጥን እንዲሁም የአፖሎን ቅርፆች የያዘ ማሽን ሠርተናል። ይህ ማሽን ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ደኅንነት ነው" ብሏል።
ጄፍ አክሎ ብሉ ሙን የተሰኘው ተቋሙ የሃይድሮጅን ኃይልን እንዴት እንደሚጠቀም በደብዳቤው አስረድቷል።
ናሳ በረዥም ጊዜ ዕቅዱ ከጨረቃ ላይ በረዶ አዘል ውሃ ኃይል በማመንጨት የጠፈር መንኩራኩሮችን ለማንቀሳቀስ ያስባል።
የጠፈር ሳይንስ ምርምር ተቋሙ ናሳ ይህንን ጨረታ ሚያዚያ ወር ላይ ባወጣ ጊዜ ስፔክስ የተሰኘው ተቋም አመራርን እጅግ በጣም ጥሩ ሲለው ብሉ ሙንን ደግሞ በጣም ጥሩ ሲል ገምግሞታል።
በኢላን መስክ የተሸነፈው ጄፍ ቤዞስ ለአሜሪካ መንግሥት ቅሬታ ሰሚ ተቋም ናሳ በድሎኛል ሲል ቅሬታ አቅርቦ ነበር።
ይግባኙ አሁንም እየታየ ቢሆንም በዘርፉ ያሉ ሰዎች ግን የናሳ ውሳኔ በተዓምር የሚቀለበስ አይደለም ይላሉ።












