በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ በሁለት ቀናት ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ አዋጡ

ግድቡ የኔ ነው የሚል መፈክር

የፎቶው ባለመብት, AFP

ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ገንዘብ ለማሰባሰብ በተዘረጋውና ባለፈው ቅዳሜ ይፋ በሆነው የበይነ መረብ መድረክ አማካይነት በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በ48 ሰዓታት ውስጥ ብቻ ከ70 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር [በወቅታዊ ምንዛሪ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ] ማዋጣታቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለጸ።

ድጋፍ በማድረጊያ የበይነ መረብ መድረኩ በሰዓት በአማካይ 1,500 የአሜሪካ ዶላር እየተለገሰ መሆኑን ለቢቢሲ የገለጹት የተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን፤ እስካሁን በአህጉር ደረጃ ከፍተኛ ገንዘብ እየተዋጣ ያለው በአፍሪካ፣ በሰሜን አሜሪካና በኦሽኒያ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንደሆነም ጠቁመዋል።

በአፍሪካ ካሉ ለጋሾች ከ50 ሺህ ዶላር በላይ የተገኘ ሲሆን፤ እስካሁን የተዋጣው ገንዘብ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከሚኖሩ ከ600 ከሚልቁ ሰዎች የተገኘ ነው።

ገንዘብ የማሰባሰብ ሂደቱ የጊዜ ገደብ ባይቀመጥለትም "ከስድስት ወር ባነሰ ጊዜ" በአዲሱ የድጋፍ መሰብሰቢያ አማካይነት 1 ሚሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ እንደታሰበ ኃላፊው ተናግረዋል።

አያይዘውም የበይነ መረብ መድረኩ ገና በመተዋወቅ ደረጃ እያለ የተሰበሰበው ገንዘብና የታየው ምላሽ ውጥኑ ከታሰበው ጊዜ ቀድሞ ሊሳካ እንደሚችል ጠቋሚ መሆኑን "አሁን ያለው አዝማሚያ ከዚያም በላይ ሊሰበሰብ እንደሚችል የሚያሳይ ነው" በማለት ገልጸዋል።

"የማይደበዝዝ አሻራችንን በግድቡ ላይ እናሳርፍ" በሚል መሪ ሐሳብና ሐሳቡን ይገልጻል ከተባለ አርማ ጋር ይፋ የሆነው ገንዘብ የማሰባሰቢያ መድረኩ በውጪ አገራት እየኖሩ ለሕዳሴ ግደቡ የገንዘብ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚሹ ሰዎችን ድካም የሚያቀል መሆኑን አቶ ሞገስ ተናግረዋል።

ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ "ቀላልና አስተማማኝ አማራጭ አልነበራቸው። ከዚህ በፊት ድጋፍ ማድረግ ቢፈልጉ እንኳን ረዥም ሰዓታት በማሽከርከር ኤምባሲዎቻችን ወይም ቆንጽላ ጽሕፈት ቤቶች ያሉበት አከባቢ መሄድ ግድ ይላቸው ነበር" ያሉት ኃላፊው፤ መድረኩ ይሄንን እንደሚያስቀርላቸው ያስረዱት "ካሉበት ቦታ ሆነው ዌብሳይታቸውን ብቻ ከፍተው በፈለጉትን የገንዘብ አማራጭ ድጋፍ ማድረግ የሚችሉበትን ዕድል ፈጥሯል" በማለት ነው።

ቀደም ሲል ለግድቡ ድጋፍ የሚውል ቦንድ ለማግዛት እንኳን በአካል ኤምባሲዎች ወይም ቆንጽላ ጽሕፈት ቤቶች መቅረብ ይጠበቅባቸው እንደነበርና አሁን ይፋ የሆነው የድጋፍ ማሰባሰቢያ ዘዴ ግን ይህንን አይነቱን ውጣ ውረድ እንዳስቀረ ጠቅሰዋል።

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ 10 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ አጭር የጽሑፍ መልዕክትንና የቦንድ ሽያጭን ጨምሮ በሌሎች መንገዶች ድጋፍ ሲሰበሰብ ቆይቷል።

በውጪ አገራት ያሉ ሰዎች ድጋፍ የሚያደርጉበት ይህንን ሥርዓት ለመፍጠር "ብዙ ማሰብ ይጠይቅ ነበር" ያሉት ኃላፊው፤ ሥርዓቱ ዘግይቶ ወደ ሥራ ለመግባቱ "አማራጮቹን ማምጣት፣ ከባንክ ጋር ማስተሳሰር፣ የደኅንነት ጉዳዮችን ማለፍ፣ አስተማማኝነቱን ማረጋገጥ" ቅድሚያ እንደተሰጣቸው በመግለጽ በምክንያትነት አስቀምጠዋል።

የገንዘብ ማሰባሰቢያው ይፋ ሲደረግ የተገኘው ምላሽ "በየትኛው የዓለም ጥግ ያለ ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ለግድቡ ድጋፍ ማድረግ የሚችልበት እድል እስኪፈጠርለት ድረስ ይጠብቅ ነበር ማለት ነው" ያስባለ ነው ብለዋል።

ይህ ሥርዓት በተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ መልክ እየተዘጋጀም ይገኛል። የመተግበሪያው ዝግጅት ተጠናቆ የደኅንነት ፍተሻ እየተደረገለት እንደሆነ አቶ ሞገስ ገልጸው፤ በቅርቡ ሥራ ይጀምራል ብለዋል።

የገንዘብ ድጋፍ የግድቡን ግንባታ እንዴት ያግዘዋል?

በዚህ መድረክ የሚሰበሰበው ድጋፍ አገሪቱ እየተፈተነችበት ባለው የውጪ ምንዛሬ ገቢ የሚሆን ነው። አቶ ሞገስ ይህ የግድቡን ግንባታ ፍጥነት ለመጨመር እንደሚያግዝ ይናገራሉ።

ይህም የራሱ የሆነ "ትርጉም እንዳለው" ሲያስረዱ፤ ግንባታው ላይ የተሳተፉ ዓለም አቀፍ ተቋራጮችን ያነሳሉ - "እነዚህ ተቋራጮች በውጪ ምንዛሬ ነው ክፍያ የሚጠይቁት። በውጪ ምንዛሬ የሚጠየቅ ክፍያን ከእንደዚህ አይነት ልገሳ በሚገኝ ገንዘብ መክፈል ከተቻለ ደግሞ አንደኛ ግድቡ አሁን ከሚሠራው የተሻለ ፍጥነት ኖሮት እንዲጠናቀቅ ማድረግ ይቻላል። ሁለተኛ በውጪ ምንዛሬ እጥረት የተነሳ ምንም አይነት ችግር ሳያጋጥም የተሰበውን ነገር ማሳካት እንደሚችል የሚሳይ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

አሁን የገንዘብ ድጋፉ በአሜሪካ ዶላር እየተደረገ ሲሆን በቀጣይ ዩሮና የዩናይትድ ኪንግደም ፓውንድን ጨምሮ ሌሎች የምንዛሬ አይነቶችን ለማካተት እንደታሰበ ጠቅሰው "ይህንን በአንድ በሁለት ቀን እንጨርሳለን ብዬ አስባለሁ" ብለዋል።

የገንዘብ ማሰባሰቢያ ሥርዓቱ ምን አዲስ ነገር ይዞ መጣ?

የገንዘብ ድጋፍ ማድረጊያ መድረኩ ገንዘብ ከማዋጣት ባሻገር ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ለሕዳሴ ግድቡ ግንባታ ገንዘብ እንዲዋጣ ዘመቻዎችን ማካሄድ ያስችላቸዋል።

እስካሁንም 36 ሰዎች የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻዎችን በመክፍት ወደ ተዘረጋው ሥርዓት ገንዘብ ገቢ እንዲሆን እያደረጉ ነው።

"አንዳንዱ ሰው ካደረገው ልገሳ ውጪ ሌሎች ሰዎችን የሚያነሳሰበት፣ እሱ ድጋፍ ማድረግ ባይችል እንኳን ሌሎች የሚደግፉበትን መንገድ የሚያመቻችበት ዕድል አለ" ነው ያሉት አቶ ሞገስ።

ግለሰቦቹ የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ያድርጉ እንጂ ገንዘቡ በቀጥታ ለዚሁ አላማ በዘመን ባንክ ወደተከፈተው አካውንት የሚገባ ሲሆን፤ ዘመቻውን ወደመራው ግለሰብ የሚሄድበት ዕድል "ሙሉ ለሙሉ የተዘጋ ነው" ብለዋል።

https://mygerd.com/ ላይ በሚገኘው አዲሱ ሥርዓት አማካኝነት ለጋሾች ገንዘብ ገቢ ሲያደርጉ በኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ የተፈረመ ዲጂታል የምስክር ወረቀት የሚደርሳቸው ሲሆን፤ ይህም የመድረኩ ልዩ ገጽታ ነው።

ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ባለፉት 10 ዓመታት ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ በልገሳና በቦንድ ግዢ ተሰብስቧል።

በአገር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ብቻ የቀረበው አጭር የጽሑፍ መልዕክት ገንዘብ የማሰባሰቢያ መንገድ በሦስት ዙር የተከወነ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ከ252 ሚሊዮን ብር በላይ ተገኝቷል።