ጠቅላይ ሚንስትሩ 'መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ በተገቢው መንገድ ያደርጋል' አሉ

ጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ "መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ በተገቢው መንገድ ያደርጋል" በማለት የትግራይ ኃይሎች ኮረም እና አላማጣን መያዛቸው ከተሰማ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የመንግሥታቸውን አቋም አሳወቁ።

የትግራይ ኃይሎች አላማጣ እና ኮረምን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸው ከተነገረ በኋላ ወልቃይት ጠገዴ እና ሰቲት ሁመራን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ጥረት እያደረጉ መሆኑ የአማራ ክልል መንግሥት ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ዛሬ ረቡዕ በማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር ገጻቸው ላይ ባወጡት ጽሁፍ፤ የፌደራል መንግሥቱ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ እንዲሁም አርሶ አደሩ በክረምቱ ወቅት እንዲያርስ በሚል መንግሥት የተኩስ አቁም ቢያውጅም፤ የትግራይ ኃይሎች ተኩስ ስላላቆሙ "መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ በተገቢው መንገድ ያደርጋል" ብለዋል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የትግራይ ኃይሎች "የእርዳታ መግቢያ መተላለፊያዎች የግጭት ቦታዎች ሲያደርጓቸው የእርዳታ ድርጅቶች አሁንም መንግሥትን ለመውቀስ ይቃጣሉ። እነዚህን ሁሉ ከግምት በማስገባት መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ነገር በተገቢው መንገድ ያደርጋል" ብለዋል።

የፌደራል መንግሥት ከሳምንታት በፊት የተናጠል የተኩስ አቁም ሲያውጅ፤ ህወሓት በበኩሉ የተኩስ አቁሙን ለመቀበል ባለ ሰባት ነጥብ ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጡ ይታወሳል።

ከእነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች መካከል፤ "የአማራና የኤርትራ ኃይሎች በወረራ ከያዙት የትግራይ ግዛቶች በመውጣት ከጦርነቱ በፊት ወደነበረው ቦታ እንዲመለሱ" የሚጠይቅ ነው።

የአማራ ክልል መስተዳድር በበኩሉ፤ "የአማራ ሕዝብ የማንነትና የወሰን ጥያቄ እያነሳ ሲታገልባቸው የቆዩት" የሚላቸው የራያ አላማጣና ኮረም አካባቢዎችን እንዲሁም ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራን እንደሚከላከል በተደጋጋሚ ገልጿል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በዛሬው መልዕክታቸው፤ "ለትግራይ ሕዝብ ያለንን ሐሳብ፤ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያለንን ቦታ ለመጨረሻ ጊዜ አሳይተናል። ግጭት ላለማባባስ፣ ለሕዝቡ የእርሻ ወቅት ፋታ ለመስጠት እንዲሁም የእርዳታ አቅርቦቱ ያለ ሰበብ እንዲከናወን ስንል በሰብዓዊነት ላይ የተመሠረተ የተናጠል የተኩስ አቁም አድርገናል" ብለዋል።

ጨምረውም "ሰላም የተወሰነ ዋጋ እንደሚያስከፍለን ብናውቅም ይህ ግን የመጨረሻ ሰላማዊ ዕድል ነው" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ አያይዘውም "በአንድ በኩል ሰብአዊ ርዳታ እንዲቀላጠፍ እየሠራን በሌላ በኩል የውጭና የውስጥ ጠላቶች ተናበው የከፈቱብንን ጥቃት መክተን እንቀለብሰዋለን" በማለት የፌደራል መንግሥቱን አቋም ገልጸዋል።

"ለሕዝባችን ስንል የከፈልነው ዋጋ ባልገባቸው ደካሞች ምክንያት ውጤት አላመጣም። ጁንታው የኢትዮጵያ ህልውና ቀንደኛ ጠላት መሆኑን ደግሞ እያስመሰከረ ነው። ይሄንንም መላ ሕዝባችንን አስተባብረን እንቀለብሰዋለን" ሲሉም አክልዋል።

line

የህወሓት ኃይሎች የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መሰነንዘራቸውን ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱ የአገር መከላከያ ሠራዊቱን ወደ ትግራይ ካሰማራ በኋላ ከሰባት ወራት በላይ በተካሄደው ጦርነት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ነገር ግን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።

ከስምንት ወራት በኋላ ሰኔ 21/2013 ዓ. ም የፌደራሉ ሠራዊት ከክልሉ መውጣቱን ተከትሎ የትግራይ ኃይሎች የክልሉን መዲና መቀለን ጨምሮ በርካታ የትግራይ ከተሞችን በቁጥጥራቸው ሥር አውለዋል።

የጦርነቱን መጀመር ተከትሎ ትግራይና አማራ ክልል በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች የሚገኙና ለረዥም ጊዜ ከአማራ ክልል ተወስደው ወደ ትግራይ ክልል ተካትተዋል ሲባሉ የቆዩ አካባቢዎችን የአማራ ክልል ኃይሎች ተቆጣጥረውት ቆይተዋል።

ወልቃይት ጠገዴ፣ ሰቲት ሁመራ፣ ጠለምትና ራያ በአማራ እና በትግራይ ክልል የይገባኛል ጥያቄ ከሚነሳባቸው ስፍራዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።