ስለዩፎዎች የተደረገው ምርመራ በቂ መልስና ማብራሪያ ሳያስገኝ ቀረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ መንግሥት በወታደራዊ አውሮፕላን አብራሪዎች ታይተዋል ስለተባሉት ምንነታቸው ያልታወቀ በራሪ አካላት ወይም ዩፎዎች ሊሰጠው የሚችለው ማብራሪያ እንደሌለ ገለጸ።
ከአውሮፓውያኑ 2004 ጀምሮ ታይተዋል ስለተባሉት በራሪ አካላት የአሜሪካ የመከላከያ መሥሪያ ቤት ባወጣው 144 ክስተቶችን የተመለከተ ሪፖርት ላይ ስለዩፎዎች ዝርዝር ማብራሪያ ሳይቀርብ ቀርቷል።
ነገር ግን ሪፖርቱ በራሪ አካላቱ ከሌላ ዓለም የመጡ ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚቀርበውን መላምት ውድቅ አላደረገውም።
የአሜሪካ ምክር ቤት በበራሪ አካላቱ ላይ ሪፖርት እንዲቀርብለት የጠየቀው በርካታ በራሪ ነገሮች መደበኛ ባልሆነ ሁኔታ በሰማይ ላይ መታየታቸውን በተመለከተ የአሜሪካ ጦር ሠራዊት ሪፖርት ማድረጉን ተከትሎ ነው።
የመከላከያ መሥሪያ ቤቱ ፔንታገንም ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ስለነዚህ ምንነታቸው ስላልታወቁ በራሪ አካላት የቀረቡ ሪፖርቶችን የሚመረምር ግብረ ኃይል አቋቁሞ ነበር።
የቡድኑ ዋና ሥራም የበራሪ አካላቱን ክስተቶች "እንዲለይ፣ እንዲተነትንና በዝርዝር ለይቶ" እንያቀርብ እንዲሁም የበራሪ አካላቱን "ተፈጥሮና ከየት እንደመጡ" ተጨማሪ መረጃን እንዲያሰባበስብ ነበር።
አርብ ዕለት ይፋ የተደረገው ጊዜያዊ ሪፖርት "ምንነታቸው ያልታወቁ በራሪ ክስተቶች" በሚል የአሜሪካ ባሕር ኃይል ባለፉት ሁለት ዓመታት ባዘጋጀው መደበኛ የማሳወቂያ ዘዴ የተመዘገቡትን 144 ክስተቶችን መሠረት ያደረገ ነው።
ከእነዚህ ውስጥም 143ቱ ክስተቶች "በተመዘገቡት መረጃዎች ላይ ላጋጠሙ ክስተቶች የተለየ ትንታኔ ለመስጠት በቂ የሆነ መረጃዎች አልቀረበባቸውም" ብሏል።
ነገር ግን በራሪ ነገሮቹ ከሌላ ፕላኔት የመጡ አይደሉም ሲል አልደመደመም።
ምንነታቸው ያልታወቁ በራሪ ክስተቶችን በተመለከተ ሪፖርቱ እንዳለው "ግልጽ ያለ አንድ ወጥ ማብራሪያ የለም" ብሏል።
አንዳንዶቹ ምናልባት ቻይናና ሩሲያን ከመሳሰሉ ሌሎች አገራት የተነሱ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ሊሆኑ የሚችሉ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ተፈጥሯዊ ክሰተቶች ሆነው በራዳሮች የተመዘገቡ ሊሆኑ እንደሚችሉ አመልክቷል።
ጨምሮም ቀሪዎቹ ደግሞ ምናልባትም "በግንባታ ላይ ያሉ በአሜሪካ ተቋማት የሚከናወኑ ምስጢራዊ ፕሮግራሞች" ሳይሆኑ አይቀሩም ብሏል።
አንደኛው ሪፖርት የተደረገው ክስተት ደግሞ መርማሪ ቡድኑ በእርግጠኝነት መለየት የቻለው ሲሆን ይህም "በጣም ትልቅ የተነፈሰ ፊኛ" ነው ሲል ገልጾታል።
ሪፖርቱ አክሎም እነዚህ ክስተቶች "በአየር በረራ ላይ ግልጽ የሆነ የደኅንነት ስጋት የሚያስከትሉ እና ምናልባትም ለአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ፈተና ሊሆኑ ይችላሉ" ብሏል።
እስካሁን ግልጽ ማስረጃ ያልተገኘላቸው እነዚህን ያልታወቁ በራሪ አካላት ተመለከትን ሚሉ ሰዎች በተደጋጋሚ እየቀረቡ ነው።
የአሜሪካ የመከላከያ መሥሪያ ቤት ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ በአሜሪካ ባሕር ኃይል የተቀረጸ ነው ያላቸውን ምንነታቸው ያልታወቁ በራሪ ክስተቶችን የሚያሳይ ቪዲዮ ይፋ አድርጎ ነበር።
በሲቢኤስ ቴሌቪዥን ላይ ባለፈው ግንቦት ወር የቀረበ ተከታታይ ዝግጅት ደግሞ ሁለት የባሕር ኃይል አውሮፕላን አብራሪዎች በፓሲፊክ ውቅያኖስ ላይ በራሪ ነገሮቹን እንደተማለከቱ አብራርተው ነበር።














