ቤትዎ ውስጥ ያሉ መገልገያዎች ምን ያህል እንደሚጮሁ ያውቃሉ?

ቤትዎ ውስጥ የሚገለገሉባቸው ማሽኖች ምን ያህል እንደሚጮሁ ያውቃሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቴክኖሎጂ እድሜው ይርዘምና ቤታችን በኤሌክትሮኒክስ ከተሞላ ሰነባብቷል። ውሃ የምናሞቀው፣ ቡና የምናፈላው፣ ልብስ የምናጥበው. . . በማሽን ነው።

ሳይንቲስቶች እነዚህ ማሽኖች የሚያወጡት ድምጽ አሳስቧቸዋል። እናም የድምጹን መጠን ለመለካት ምርምር እያደረጉ ነው።

ለንደን ውስጥ የሚገኘው ቤተ ሙከራ ድምጽ ከሚለካበት መካከል ይጠቀሳል።

በቤተ ሙከራው የማይሰማ የማሽን ድምጽ የለም። እናም ከእያንዳንዱ መገልገያ የሚወጣውን ድምጽ እየለካ፣ ልኬቱን በቀለም የሚገልጽ መሣሪያ አለ።

ኳይት ማርክ የሚባለው ተቋም ማሽኖች የሚያወጡትን ድምጽ እየለካ ደረጃ ይመድባል። ሰው የማይረብሹ ጸጉር ማድረቂያዎች፣ ልብስ ማጠቢያዎች ወዘተ "ኪው" [Q] የሚል ደረጃ ይሰጣቸዋል።

ላለፉት 10 ዓመታት በዚህ ሥራ የተሰማራው ድርጅት መስራች ፖፒ ስኪለር ናት። አያቷ እአአ በ1959 ድምጽ ተቆጣጣሪ ማኅበር አቋቁመው ነበር።

በርካቶች በኮሮናቫይረስ ምክንያት ቤት መዋል ካበዙ ወዲህ ከማሽኖች የሚወጣውን ድምጽ ማስተዋል እንደጀመሩ ፖፒ ትናገራለች።

"አብዛኛው ጊዜ የሚያልፈው ቤት ስለሆነ ድምጽ መቀነስ የሚፈልጉ ተበራክተዋል" ትላለች።

ስለዚህም ድርጅቷ አነስተኛ ድምጽ የሚያወጡ ማሽኖች ገበያው ላይ እንዲቀርቡ ይፈልጋል። የማሽኖችን ድምጽ ለክተው ደረጃ የሚሰጡትም ለዚሁ ነው።

ድምጽ እንዴት ይለካል?

ድምጽ የሚለካው በዴሲብልስ (dB) ሲሆን፤ እስከ 40 ዴሲብልስ ድረስ ያለው አይረብሽም።

አሁን ላይ የሚሸጡት ምርቶች ምን ያህል ድምጽ እንደሚያወጡ አይገለጽም። ፖፒ ይህንን መለወጥ ነው ህልሟ።

"ከመገልገያው የሚወጣውን ድምጽ መጠን እና አይነት እየለካን የቱ ምርት የተሻለ እንደሆነ እንጠቁማለን" ትላለች።

ድርጅቷ 'ኳይት ማርክ' በተለያዩ የዩናይትድ ኪንግደም የመገልገያ መደብሮች ተመዝግቧል።

የጆን ልዊስ ቴክኖሎጂ ኃላፊ ሎረንስ ሚሸል እንደሚሉት፤ ማሽን ከመግዛታቸው በፊት ስለ ድምጹ በበይነ መረብ መረጃ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።

በአንድ ወር ውስጥ የተቋማቸው ድረ ገጽ ከ10,000 በላይ ጥያቄዎች ያስተናግዳል።

በተለይም የሻይ እና ልብስ ማጠቢያ ማሽኖች ከመግዛታቸው በፊት ስለ ድምጻቸው የሚጠይቁ ብዙ ናቸው።

ወደፊት ሰዎች ብዙ ገንዘብ የሚያወጡት ድምጻቸው ዝቅተኛ ለሆኑ መገልገያዎች እንደሚሆን ይተነብያሉ።

ድምጽ እና ጤና

አንድ የድምጽ ልኬት ሁሉንም ሰው ላያስማማ ይችላል። አንዳንዱን የሚረብሸው ድምጽ ለሌላው ምንም አይመስለውም። የጤና ባለሙያዎች ከፍተኛ ድምጽ ለልብ ህመም እንደሚያጋልጥ ጠቁመዋል።

የአዕምሮ እድገት ውስንነት ማኅበር ባልደረባው ቶም ፐርሰር እንደሚለው፤ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ሕፃናትም ይሁን አዋቂዎች ድምጽን የሚገነዘቡት በተለየ ሁኔታ ነው።

"ለአንዳንዶች አንዳች አይነት ድምጽ ወይም በተወሰነ ጊዜ ልዩነት በተደጋጋሚ የሚሰማ ድምጽ ይረብሻቸዋል። በተቃራኒው ድምጽ መስማት ደስ የሚላቸውም አሉ" ሲል ያብራራል።

ፖፒ ጸጥ ያለ ቤት ከሚወዱ መካከል ናት። ማሽን አምራቾች የድምጽን ጉዳይ ከግምት እያስገቡ ቢሠሩም ደስ ይላታል።

"ማሽን ሲሠራ ኃይል ቆጣቢነቱ፣ ለረዥም ጊዜ ማገልገሉና ገጽታውም ታሳቢ ይደረጋል። ከእነዚህ በተጨማሪ የድምጽ ጉዳይም ቢታሰብበት መልካም ነው" ትላለች።