ረዥም ሰዓት መሥራት በዓመት የ 745 ሺህ ሰዎችን ህይወት እየነጠቀ ነው-ጥናት

በከፍተኛ ስራ የተጨናነቀች ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ረዥም ሰዓት መሥራት በዓመት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት እየነጠቀ ነው ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ፡፡

በዓይነቱ የመጀመሪያ በሆነው ዓለም አቀፍ ጥናት መሠረት እአአ በ 2016 ከረዥም ሰዓታት ሥራ በሚከሰት ስትሮክ እና የልብ ህመም ምክንያት 745,000 ሰዎች መሞታቸውን ይፋ አደርጓል፡፡

ሪፖርቱ እንዳመለከተው በደቡብ ምስራቅ እስያ እና በምዕራብ ፓስፊክ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በችግሩ በጣም የተጠቁ ናቸው፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ከሆነ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ችግሩ ሊባባስ ይችላል፡፡

ጥናቱ እንዳመለከተው በሳምንት ለ 55 ሰዓታት እና ከዚያ በላይ መሥራት በሳምንት 35 እስከ 40 ሰዓታት በሳምንት ከሚሠሩት ጋር ሲነፃፀር 35 በመቶ በስትሮክ እና 17 በመቶ ደግሞ በልብ ህመም የመሞት ዕድላቸው የጨመረ ነው፡፡

ከዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት (አይኤልኦ) ጋር የተደረገው ጥናቱ እንደሚያሳየው ረዘም ላለ ሰዓት በመሥራታቸው ከሞቱት መካከል ሶስት አራተኛ የሚሆኑት በመካከለኛ ዕድሜ ወይም ዕድሜያቸው የገፋ ወንዶች ናቸው፡፡

ብዙውን ጊዜ በዚህ ምክንያት ህይወታቸውን የሚያጡት ከብዙ አሥርት ዓመታት በኋላ ነው፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ጥናት የተከሰተውን ወረርሽኝ ጊዜ አላካተተም።

የድርጅቱ ባለሥልጣናት በቅርቡ ከቤት መሥራት እና የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል ከረዥም የሥራ ሰዓታት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን ሳይጨምረው አይቀሩም ብለዋል ፡፡

"ሃገራት ወደ ብሄራዊ እንቅስቃሴ ገደብ ሲገቡ የሥራ ሰዓት በ 10 በመቶ ገደማ እንደሚጨምር የሚያሳዩ ጥቂት ማስረጃዎች አሉን" ያሉት የዓለም ጤና ድርጅት የቴክኒክ ባለሙያው ፍራንክ ፔጋ ናቸው።

ሪፖርቱ እንደሚለው ከሥራ ጋር ተያያዥነት ካላቸው ህመሞች አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ከረዥም ሰዓት መሥራት ጋር እንደሚገናኙ ይገመታል፡፡

ተመራማሪዎቹ እንዳሉት ረዥም የሥራ ሰዓታት ለጤንነት መጥፎ ውጤት የሚያስከትሉባቸው ሁለት መንገዶች አሉ።

አንደኛው ለጭንቀት የሚሰጠው ቀጥተኛ የፊዚዮሎጂ ምላሾች ናቸው። ሁለተኛው ደግሞ ረዥም ሰዓት የሚሠሩ ሠራተኞች እንደ ትምባሆ እና አልኮል መጠጣትን፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ካለማድረግ፣ ጤናማ ካልሆነ አመጋገብ እና የመሳሰሉ ጤናን የሚጎዱ ባህሪያትን የመልመድ ዕድላቸው ከፍተኛ በመሆኑ ነው።

የሊድስ ነዋሪ የሆነው የ 32 ዓመቱ መሐንዲስ አንድሪው ፋልስ በቀድሞ ድርጅቱ ያሳለፈው ረዥም የሥራ ሰዓት በአዕምሮው እና በአካላዊ ጤንነቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ይናገራል፡፡

"ከሃምሳ እስከ 55 ሰዓት በሳምንት መሥራት የተለመደ ነበር፡፡ ለሳምንታትም ከቤቴ እርቅ ነበር" ብሏል፡፡

"ጭንቀት እና ድብርት ይመላለሱብኝ ነበር" ብሏል፡፡

"ወደታች በሚወርድበት የማያቋርጥ ሁኔታ ውስጥ ነበርኩ" ሲል ይገልጻል፡፡

ከአምስት ዓመታት በኋላ የሶፍትዌር መሐንዲስ ሆኖ ለመሥራት ሥራውን ለቀቀ፡፡

በዓለም ጤና ድርጅት መረጃ መሠረት ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት ለረጅም ሰዓታት የሚሠሩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን ከጠቅላላው የዓለም ህዝብም ወደ 9 በመቶ ገደማ ናቸው፡፡

የዩኬ በብሔራዊ ስታትስቲክስ ቢሮ እንደሚለው በወረርሽኙ ወቅት ከቤት የሚሠሩ ሰዎች በሳምንት በአማካይ ስድስት ሰዓት ያለክፍያ የትርፍ ሰዓት ሥራዎችን ያከናውኑ ነበር ብሏል፡፡

ከቤታቸው የማይሠሩ ሰዎች በሳምንት በአማካይ በ 3.6 ሰዓታት የትርፍ ሰዓት ሥራ ብቻ ይሠራሉ ሲል ቢሮው አስታውቋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት አሠሪዎች የሠራተኞቻቸውን የሥራ ጤና አደጋዎች ሲገመግሙ ይህንንም ከግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው ይላል፡፡

የቁርጥ ሰዓት ሥራ ምርታማነትን እንደሚያሳድግ በመታየቱ ለአሠሪዎች ጠቃሚ ይሆናል ሲሉ ፒጋ ገልጸዋል፡፡

"በኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ረዥም የሥራ ሰዓቶችን አለመጨመር የብልህ ምርጫ ነው" ብለዋል።