የኬንያ ራስ ተፈሪያኖች ዕፀ ፋርስ ለመንፈሳዊ አገልግሎት እንዲፈቀድላቸው ፍርድ ቤቱን ጠየቁ

የኬንያ ራስ ተፈሪያኖች

የፎቶው ባለመብት, EPA

የኬንያ ራስ ተፈሪያኖች ዕፀ ፋርስን ለመንፈሳዊ አገልግሎት እንዲጠቀሙበት ይቻል ዘንድ ጉዳዪን ወደ ፍርድ ቤት ወስደውታል።

ጥያቄው የቀረበው ዘ ራስ ተፋሪ ሶሳይቲ ኦፍ ኬንያ በሚባለው ማህበር ነው።

ማህበሩ ራሱን እንደ አናሳ አባላት ያሉት የእምነት ቡድን አድርጎ የሚጠራ ሲሆን በአገሪቱ ያሉት ህጎች የሃይማኖታዊ ልምዶቻቸውን በነፃነት እንዳያካሂዱና አባላቱንም በፍራቻ ሸብቦ ይዟቸዋል ብሏል።

የራስ ተፈሪያን እምነት ተከታዮች ማስፈራራቶች፣ ማዋከብ እንደሚደርስባቸው የገለፀው ማህበሩ በቤታቸውና በአምልኮ ቦታቸውም እንዲሁ ተደጋጋሚ ፍተሻዎች እንደሚደረግባቸው አስታውቋል።

ሻድራክ ዋምቡይና አሌክሳንደር ምዌንድዋ የተባሉት ጠበቆች እንደሚከራከሩት ዕፀ ፋርስ "ቅዱስ እንደሆነና" አማኞችንም "ከፈጣሪ ጋር የሚያገናኛቸው" ነው ይላሉ።

ጠበቆቹ የኬንያን ባለስልጣናት የቡድኑ ሃይማኖታዊ መብት ባለማክበርም ወንጅለዋቸዋል።

ከሁለት አመታት በፊት የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የራስ ተፈሪያን እንቅስቃሴ እንደ ማንኛውም የሃይማኖት ቡድን ነው ሲል የበየነ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ እንደ ማንኛውም እምነት መብታቸው እንዲከበርም አዟል።

ፍርድ ቤቱ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው አንድ አባት ልጁ ድሬድ ፀጉሯን እንድትቆረጥ ትምህርት ቤቷ መመለሱን ተከትሎ ነው። አባትየው ልጁ ፀጉሯ ድሬድ የሆነው የራስተፈሪያን እምነት ተከታዮች በመሆናቸው ነው በማለት ትምህርት ቤቱን ከሶ ነበር።