ፍራቻና ኃዘን የተቀላቀለበት የእስራኤል-ጋዛ ሁኔታ በፎቶዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በእስራኤልና በፍልስጥኤም የተነሳው ግጭት የሰላማዊ ዜጎችን ህይወት መቅጠፉን ቀጥሏል፤ ምንም እንኳን በርካታ አገራት የተኩስ አቁም ስምምነቶች ላይ እንዲደረስ ግፊት ቢያደርጉም ፍሬያማ አልሆነም። ግጭቱ ከፍ ወዳለ ጦርነት እንዳያመራም ተሰግቷል።
በባለፉት ቀናት የተሰነዘሩ የአየር ጥቃቶችና ሮኬት መወንጨፎች የበርካቶችን ህይወት ቀጥፈዋል፤ ህንፃዎችን አውድመዋል፤ በርካቶች መኖሪያ አልባ እንዲሆኑና እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆነዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስራኤል የምታደርገው የአየር ጥቃት ኢላማ ያደረገው የፍልስጥኤም ታጣቂዎችን ነው ብትልም በጥቃቱ የኤሌክትሪክ መስመሮች ተቋርጠዋል፤ ዋና ዋና ጎዳናዎች ፍርስርሳቸው ወጥቷል።
ከላይ በሚታየው ምስል ባለፈው ሳምንት እሁድ በእስራኤል አየር ጥቃት ቤቱ የፈረሰበት ፍልስጥኤማዊ እጥፍ ብሎ በሃዘን ተሰብሮ ይታያል።
አንዳንድ የቤተሰቦቹ አባላት በህንፃው ፍርስራሽ ተቀብረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሳምንት በፊት ግጭት የተነሰባት ጋዛ በርካታ ሰዎች የሞቱባት እለት በባለፈው ሳምንት መጨረሻ እሁድ ነው።
እስራኤል ከሌሊት በኋላ ባደረገችው የአየር ጥቃት እንቅስቃሴ የበዛበት ጎዳንን ኢላማ ያደረገች ሲሆን፤ በርካታ ህንፃዎች እንዳልነበሩ ወደሙ። የበርካቶችም ህይወት ተቀጠፈ።
"በጋዛ የፈረሱትን መልሶ ለመገንባት ቢያንስ አስር አመታት ያስፈልገናል" በማለት የህፃናት ዶክተር የሆኑት መሃመብ አቡ ራያ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በግዛቲቱም ለበርካቶች የኃዘን ስነ ስርዓት ተደርጓል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ጋዛን የሚያስተዳድረው ሃማስና ሌሎች የፍልስጥኤም ታጣቂዎች ሮኬቶችን ወደ ደቡባበዊ እስራኤል በማስወንጨፍ ላይ ናቸው።
በዚህም የተነሳ ህንፃዎችና ቤቶች የፈራረሱ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ራሳቸውን ከፍንዳታ ለመከላከል ወደ ቦንብ መጠለያዎች አምርተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የእስራኤል መከላከያ እንዳስታወቀው ወደ ግዛታቸው ከተወነጨፉ ሮኬቶች መካከል 90 በመቶ የሚሆነውን ማክሸፋቸውን ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ሮኬቶች ከጎረቤት አገር ሊባኖስ ወደ ሰሜን እስራኤል ተወንጭፈዋል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ግጭቱ በእስራኤል ቁጥጥር ስር ወዳለችው ዌስት ባንክ ግዛት የተዛመተ ሲሆን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በእስራኤል ወታደሮችና በፍልስጥኤማውያን መካከል ግጭት ተፈጥሯል።
ፍልስጥኤማውያን አረቦች በዌስት ባንክ በእስራኤል ወታደራዊ አገዛዝና በተወሰነላቸው የራስ አገዛዝ ስር ይኖራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ህፃኗ ለሰዓታት ያህል በቤታቸው ፍርስራሽ ውስጥ ተቀብራ የነበረ ሲሆን ከአባቷም ጋር በሆስፒታል እየታከመች ትገኛለች።
"ልጄ ይቅር በይኝ። ወደ አንቺ እንድመጣ እየነገርሸኝ ነበር፤ መምጣት አልቻልኩም" በማለት ከልጁ ጋር ሲገናኝ ፍልስጥኤማዊው ሪያድ ተናግሯል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ግጭቱ ሁለተኛ ሳምንቱን የያዘ ሲሆን የአየር ጥቃቶችና ሮኬት መወንጨፎች ቀጥለዋል።
አሜሪካን ጨምሮ የአለም ኃያል አገራት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲኖር ቢጠይቁም ምንም የተቀየረ ነገር የለም።

የፎቶው ባለመብት, Reuters












