የአሜሪካ ጦር በአስተርጓሚነት የሰሩለትን አፍጋኒስታውያንን ሊወስዳቸው ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለአሜሪካ ሰራዊት ይሰሩ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ አፍጋኒስታውያን አስተርጓሚዎችን አሜሪካ ልትወስድ መሆኑን ከፍተኛ ባለስልጣናቷ አስታውቀዋል።
ይህም አሜሪካ በአፍጋኒስታን የነበራትን ሰራዊት ልታስወጣ ካቀደችበት ከመስከረም በፊት እንደሚከናወን አስታውቃለች።
በዚህም እቅድ መሰረት ወደ 50 ሺህ የሚጠጉ አፍጋኒስታውያን አስተርጓሚዎች ከነቤተሰቦቻቸው ወደሌሎች አገራት ይወሰዳሉ ተብሏል።
ለአመታት በአስተርጓሚነት ለአሜሪካ የሰሩ አፍጋኒስታውያን አስተርጓሚዎች የአሜሪካ ወታደሮች ከአፍጋኒስታን ይወጣሉ መባሉን ተከትሎ በታሊባን የበቀል እርምጃ ይወሰድብናል በሚል ስጋት ላይ ናቸው።
ወደ 18 ሺህ የሚሆኑት ወደ አሜሪካ ለመሄድ ቪዛ የጠየቁ ሲሆን ነገር ግን ባለው መዘግየት ምክንያት የጉዟቸው ሂደት ተጓትቷል ተብሏል።
በአሁኑ ወቅትም አሜሪካ የያዘችው እቅድ ከመስከረም በፊት እነዚህን አስተርጓሚዎች ወደሌላ አገራት ወስዳ ከዚያው ሆነው የአሜሪካ የቪዛ ሂደትን እንዲጨርሱ ነው።
በትናንትናው ወቅት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከዋይት ሃውስ ባደረጉት ንግግር "የረዱንን ሁሉ አንረሳቸውም። ትተናቸው አንወጣም። ህይወታቸውን አደጋ ውስጥ ከትተው ሊረዱን የሞከሩ ናቸው። በዚህች አገር እንቀበላቸዋለን" ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ባይደን ከአፍጋኒስታን ፕሬዚዳንት አሽራፍ ጋኒ ጋር ለመወያየት በዋሽንግተን ለዛሬ ቀጠሮ ይዘዋል።
በአፍጋኒስታን ስላለው የፀጥታ ሁኔታና የአሜሪካ ስራዊት አፍጋኒስታንን ለቆ በሚወጣበት ወቅትስ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ምን መምሰል አለበት በሚለውም ላይ ይመክራሉ።
አስተርጓሚዎቹ ወደ አሜሪካ መምጣት አለባቸው በማለት በዋናነት ሲከራከሩ የነበሩት የሪፐብሊካኑ ምክር ቤት አባል ማይክ ማክ ካውል ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት 9 ሺህ የሚሆኑ ለልዩ ቪዛ ያመለከቱ አስተርጓሚዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር በዚህ እቅድ እንደሚካተቱ ነው።
"ምናልባት ወደ 50 ሺህ የሚቆጠሩ ይሆናሉ። የነሱን ሁሉ ቪዛ በአፍጋኒስታን እያሉ በአጭር ጊዜ መጨረስ ከባድ ነው የሚሆነው ስለዚህ ስለ ደህንነታቸው ቅድሚያ ልንሰጥ ይገባል" ብለዋል።
የአሜሪካ ቪዛቸው እስኪጨረስ ድረስ እንዲቆዩባቸው የታሰቡ አገራት ኩዌት፣ ኳታር፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስና ባህሬን መሆናቸውንም የምክር ቤት አባሉ ገልጸዋል።












